ሪፖርት | አዳማ ከተማ ከፕሪምየር ሊጉ መውረዱ ተረጋግጧል

ሪፖርት | አዳማ ከተማ ከፕሪምየር ሊጉ መውረዱ ተረጋግጧል

አሰልጣኝ ሙሉጌታ ምህረት ከሀዋሳ ከተማ ጋር በአስገራሚ ግስጋሴያቸው ዓመቱን በድል ሲቋጩት አዳማ ከተማ ደግሞ ለሁለተኛ ጊዜ ከሊጉ መውረዱን አረጋግጧል።።

ካለፈው የጨዋታ ሳምንት ሀዋሳ ከተማ ከባህርዳሩ ድል የሦስት ተጫዋቾችን ለውጥ ሲያደርጉ ወንድማገኝ ማዕረግን በፀጋአብ ዮሐንስ ፣ ብሩክ ኤልያስን በአቤኔዘር ዮሐንስ ፣ ዓሊ ሱለይማንን በምንተስኖት እንድሪያስ ፋሲል ከነማን ሲመሩ ቆይተው በመጨረሻም 2ለ2 ማጠናቀቅ የቻሉት አዳማዎች በበኩላቸው ናትናኤል ተፈራን በዳግም ተፈራ ፣ መላኩ ኤልያስን በቻላቸው መንበሩ በመተካት ወደ ሜዳ ገብተዋል።

በፈጣን ሽግግሮች የጀመረ ቢመስልም በይበልጥ ጥንቃቄዎች የበዙበት የመጀመሪያዎቹ ሀያ ደቂቃዎች ተመጣጣኝ እንቅስቃሴዎች ቢኖሩትም ከተጠቀሰው ደቂቃ በኋላ አዳማዎች ወደ መስመር በማዘንበል መንቀሳቀስን በጀመሩበት ቅፅበት በመጀመሪያው የአጋማሹ ሙከራ ጎልን አስመልክተውናል። በ21ኛው ደቂቃ ከነቢል ኑሪ ያገኘውን ኳስ ቢኒያም ዐይተን የግል ጥረቱን ተጠቅሞ የሀዋሳን ተጫዋቾች በማለፍ ወደ ሳጥን ይዞ የገባትን ኳስ መረብ ላይ በማሳረፍ አዳማን መሪ ማድረግ ችሏል።

ጎሏን ካስቆጠሩ በኋላ መጠነኛ መነሳሳት ያሳዩት በሊጉ ለመቆየት ተዓምርን የሚፈልጉን ባለሜዳዎቹ ቻላቸው መንበሩ በግቡ የቀኝ ቋሚ ብረት ከተመለሰባቸው ሙከራ በኋላ በፈጣን መልሶ ማጥቃት መጫወት በጀመሩት ሀዋሳዎች ብልጫው ተወስዶባቸዋል። 32ኛው ደቂቃ ሬድዋን ሸረፋ ተባረክ ሔፋሞ ላይ ጥፋት በመስራቱ ብሩክ ታደለ የተገኘውን ቅጣት ምት ወደ ጎል ሞክሮ ዳግም ተፈራ ካዳናት ሙከራ አራት ደቂቃዎች መቆጠር መልስ አዳማዎች በአቤኔዘር ሲሳይ ካደረጉት ደካማ ሙከራ እና ፂሆን መርዕድ በቀላሉ ከያዛት አጋጣሚ በኋላ ሀዋሳዎች በጭማሪው 45+1 ላይ ቢኒያም በላይ በጥሩ ዕይታ በተከላካይ መሐል አሾልኮ የሰጠውን ኳስ አቤኔዘር ዮሐንስ በድንቅ አጨራረስ ወደ ጎልነት ለውጧት ሀዋሳን 1ለ1 ማድረግ ችሏል።

ከዕረፍት መልስ ሁለቱም ቡድኖች የተጫዋቾችን ቅያሪ በማድረግ መመለስ ቢችሉም የተሻለውን እንቅስቃሴ በአጋማሹ ያደረጉት ግን ሀዋሳ ከተማዎች ነበሩ። ተመጣጣኝ አጀማመር ቢኖረውም በአንፃራዊነት የሀዋሳ ከተማ የተሻለ የሽግግር አጨዋወት ያየለበት ቢሆንም በሙከራዎች ረገድ ግን ፍፁም ደካማ ነበር ይሁን እንጂ በተሻለ አጋማሹን መቆጣጠር የቻሉት የአሰልጣኝ ሙሉጌታ ምህረቱ ሐይቆቹ 65ኛው ደቂቃ ላይ በቀኝ የሜዳው ክፍል ሳጥን ውስጥ ፍቅሩ አለማየሁ ፍቃደስላሴ ደሳለኝ ላይ በሰራው ጥፋት የዕለቱ ዋና ዳኛ ሔኖክ አበበ የሰጡትን የፍፁም ቅጣት ምት ተከላካዩ በረከት ሳሙኤል ዳግም ተፈራ መረብ ላይ በማሳረፍ ጨዋታው 2ለ1 በሀዋሳ አሸናፊነት መጠናቀቅ ችሏል። ሀዋሳ ከተማ በአሰልጣኝ ሙሉጌታ ምህረት መመራት ከጀመረ በኋላ አስራ አራተኛውን ያለ መሸነፍ ጉዞውን በማስመዝገብ ሦስተኛ ደረጃ ላይ በመቀመጥ ሲፈፅም አዳማ ከተማ ለሁለተኛ ጊዜ በታሪኩ ከሊጉ መውረዱን አረጋግጧል።