ሲዳማ ቡና በጭማሪ ደቂቃ ግብ ከፋሲል ከነማ ጋር ነጥብ በመጋራት ውድድር ዓመቱን ጨርሷል።
ፋሲል ከነማ በመጨረሻ ጨዋታቸው ላይ ከአዳማ ከተማ ጋር ነጥብ ተጋርተው ሲወጡ ይዘው ከገቡት ቋሚ አሰላለፍ የሁለት ተጫዋቾች ለውጥ አድርገው ሲገቡ ሲዳማ ቡና በበኩላቸው ከአርባምንጭ ከተማ ጋር 0ለ0 ሲለያዩ ይዘው ከገቡት መጀመሪያ ቋሚ ስብስብ የስድስት ተጫዋች ለውጦችን አድርገው ገብተዋል።
መጥፎ ውድድር አመት አሳልፈው በመጨረሻ ሰዓት የአዳማ ከተማን ሽንፈት ተከትሎ በሊጉ መቆየታቸውን ያወጁትን ፋሲል ከነማዎችን ደረጃቸውን ለማሻሻል የመጨረሻ ጨዋታቸውን ከሚያደርጉት ከሲዳማ ቡናዎች ያገናኘው የእለቱ ሁለተኛው መርሃግብር 12 ሰዓት ሲል ጅማሮውን አድርጓል። በተመጣጣኝ እንቅስቃሴ ጨዋታው ሲቀጥል ፋሲል ከነማ በአንፃራዊነት የኳስ ቁጥጥርም ሆነ በሽግግር ሳጥን ውስጥ ኳሰ ይዘው በመግባት ረገድ የተሻለ የነበሩ ቢሆንም የጠራ ሙከራ ማድረግ በመጀመሪያዎቹ አስር ደቂቃዎች አልቻሉም። አስቆጪ አጋጣሚዎችን እየፈጠሩ የሲዳማ ቡናን ተከላከይ መስመር በተደጋጋሚ ሲፈትኑ የነበሩት አፄዎቹ በተለይም 13ኛው ደቂቃ ላይ በረጅሙ የተጣለ ኳስ ቢኒያም ጌታቸው በፍጥነት ሊደርስ ሲል ግብ ጠባቂው ቀድሞ የተቆጣጠረባቸው አጋጣሚ ቀዳሚ ሊያደርጋቸው የቀረበ ወርቃማው እድል ቢሆንም ሳይደርስበት ቀርቷል። የ20ኛው ደቂቃ ላይ በቆመ ኳስ ጌታነህ ከበደ ያደረገው ሙከራ ሲጠቀስ ቀጥታ ወደ ግብ የመታው ኳስ ከግቡ ቋሚ ብረት ለትንሽ ርቆ አልፎበታል።
የግብ ማግባት ሙከራዎች ብልጫ የነበራቸው አፄዎቹ ጨዋታው 36ኛ ደቂቃ ላይ ሲደርስ እጅግ ለግብ የቀረቡበትን እድል ፈጥረዋል፤ በተጠቀሰው ደቂቃ ከራሳቸው ሜዳ ክፍል በረጅሙ የተጣለውን ኳስ አማኑኤል ገብረሚካኤል በደረቱ አቁሞ ወደ ግብ ቢመታም ኳሱ እንዳሰበው ጠንካራ ሳይሆንለት ይቅር እንጂ ሌላኛው ተጠቃሽ ሙከራ ነበር። ሲዳማ ቡናዎች በመልሶ ማጥቃት ወደ ግብ ለመግባት ጥረት ያደርጉ እንጂ መረጋጋት ተስኗቸው በአመዛኙ ሁለተኛው ሜዳ ክፍል ላይ ሲደርሱ ኳሶች እየተቆራረጠባቸው ተቸግረው አንድም ለግብ የቀረበ ሙከራ ሳያደርጉ ለረጅም ደቂቃ ቆይተዋል። እንዲሁም በኳስ ቁጥጥር በወጥ እንቅስቃሴ መቀጠል ያልቻሉ ሲሆን አልፈው አልፈው ኳሶችን ይዘው ወደ ፊት ይሂዱ እንጂ ወደ ሳጥን ደርሰው ይሄ ነው ተብሎ ሊጠቀስ የሚችል አደገኛ አጋጣሚ መፍጠር ባለመቻላቸው እጅግ ደካማ የሆኑበትን የመጀመሪያ አጋማሽ ሲያሳልፉ እየተመለከትን የመጀመሪያው አጋማሽ ወደ መገባደጃው ተቃርቧል።
ከደቂቃ ደቂቃ እየተሻሻሉ ወደ ማጥቃቱ ገብተው የተጋጣሚ ቡድን ሜዳ ላይ ማዘወተራቸውን ያጠናከሩት አፄዎቹ 43ኛው ደቂቃ ላይ ሌላኛውን ኢላማውን የጠበቀ ሙከራ አድርገዋል፤ የቆሙ ኳሶችን በተደጋጋሚ ሲመታ የነበረው ጌታነህ ከበደ ርቀት ላይ የተገኘውን ኳስ ወደ ግብ ሲመታ መስፍን ሙዜ ሲቆጣጠርበት እንዲሁም መደበኛው የጨዋታ ክፍለጊዜ ተጠናቆ ጭማሪ በታየው ላይ አማኑኤል ገብረሚካኤል ሳጥን ውስጥ ሆኖ ወደ ግብ የመታው ኳስ ለጥቂት ከግቡ አናት የወጣበት ሌላኛው ፈታኝ ሙከራ ይጠቀሳል። አጋማሹም በፋሲል ከነማዎች ሳጥን ውስጥ ብልጫ ጋር ታጅቦ በሲዳማ ቡናዎች ቀዝቃዛ ግብ ማግባት እንቅስቃሴ ልዩነት ሳይፈጠር ያለ ግብ ተጠናቆ ወደ መልበሻ ክፍል ገብተዋል።
ጨዋታው ከእረፍት ተመልሶ ልክ እንደመጀመሪያው አጋማሽ ማጥቃት ላይ ትኩረት አድርገው የተመለሱት ፋሲሎች መሪ የሆኑበትን ግብ አጋማሹ በተጀመረ በአራተኛው ደቂቃ አስቆጥረዋል፤ 49ኛው ደቂቃ ላይ በቀኝ መስመር በኩል የቆመ ኳስ ቃልኪዳን ዘላለም ወደ ሳጥን ያሻማውን ኳስ ምኞት ደበበ በግንባሩ ገጭቶ ከመረብ ጋር አገናኝቶታል።
አፄዎቹ ተጨማሪ ግብ አስቆጥረው ልዩነታቸውን ማስፋት የሚችሉበትን አጋጣሚ 57ኛው ደቂቃ ላይ ፍፁም ያለቀ ኳስ አግኝተው አምክነዋል፤ ከተከላካዮች መሃል መሬት ለመሬት የተሾለከ ኳስ ቢኒያም ጌታቸው ብቻውን ሆኖ አግኝተው እየገፋ ሳጥን ውስጥ ገብቶ ከግብ ጠባቂው ጋር ተገናኝቶ ኳሱ መረብ ውስጥ ሲጠበቅ ለግብ ጠባቂው ያሳቀፈበት እጅግ አስቆጪው እና ወርቃማው እድል ወደ ግብነት ቢቀየር ኖሮ ምናልባትም በእፎይታ ጨዋታውን እንዲጨርሱ ይረዳቸው የነበረ ቢሆንም ሳይጠቀሙበት ቀርተዋል።
ከግቡ መቆጠር በኋላ ተነቃቅተው ወደ ሳጥን መድረስ የጀመሩት ሲዳማ ቡናዎች በቁጥር በርከት ብለው የተቃራኒ ሜዳ ክፍል እየደረሱ የፋሲሎችን ተከላካይ ሲፈትኑ አስተውለና። ካደረጓቸው ፈታኝ ሙከራዎች መካከል ጨዋታው 58ኛው ደቂቃ ላይ ሲደርስ የቆመ ኳስ ተሻምቶ ፍቅረኢየሱስ ተወልደብርሃን በግንባሩ ገጭቶ ወደ ግብ ቢያሻግርም ፋሲል ገብረሚካኤል የተቆጣጠረባቸው እንዲሁም ተቀይሮ ሜዳ የገባው ሬድዋን ናስር በረጅሙ በግራ መስመር በኩል ለነበረው ደስታ ዮሐንስ ያሻገረውን ኳስ በጥሩ ንክኪ ወደ ሳጥን ያሻማውን ኳስ ምኞች ደበበ እንዴትም ጨርፎ ያወጣባቸው ሌላኛው ለግብ የቀረበ አጋጣሚ ይጠቀሳል።
የሲዳማ ቡናዎች ጫና ቀጥሎ ፋሲሎች በመልሶ ማጥቃት ተጨማሪ ግብ ፍለጋ እየገቡ ግለቱን ጨምሮ በቀጠለው በጨዋታው አፄዎቹ ያሳለፉትን መጥፎ የውድድር አመት ለመርሳት የመጨረሻውን ሙሉ ሶስት ነጥብ ይዘው ለመውጣት በከፍተኛ ጥንቃቄ እየተጫወቱ ጨዋታው ወደ መጨረሻዎቹ አስር ደቂቃዎች ሲደርስ ሲዳማ ቡናዎች በበኩላቸው ቢያንስ አቻ ሆኖ ነጥብ ተጋርተው ለመውጣት በሙሉ ሀይላቸው ወደ ሳጥን እየደረሱ ለግብ የቀረቡ ሙከራውችን ሲያደርጉ አስተውለናል። 83ኛው ደቂቃ ላይ የቆመ ኳስ ደስታ ዮሐንስ ወደ ሳጥን አሻምቶ ተጨራርፎ የወጣውን ኳስ ሳጥን ውስጥ ይገዙ ቦጋለ አግኝቶ ወደ ግብ ሲመታ ፋሲል ገብረሚካኤል እንዴትም አግዶበት እራሱን ኳስ ተቀይሮ የገባው ሳሙኤል ባራሳ ከሳጥን ውጭ ሆኖ አክርሮ መትቶ ኳስ በግቡ አናት ወጥቶባቸዋል።
በጨዋታው መደበኛው የጨዋታ ክፍለጊዜ ተጠናቆ በምኞት ደበበ ብቸኛ ግብ ለአፄዎቹ ሙሉ ሶስት ነጥብ አስገኘ ተብሎ ሲጠበቅ ሲዳማ ቡናዎች የአቻነት ግብ አስቆጥረዋል፤ ከሳጥን ውጪ ርቀት ላይ ኳስ ያገኘው ሳሙኤል በራሳ ጠንከር ያለ ኳስ አክርሮ ወደ ግብ መትቶ ግብ ጠባቂው ፋሲል ገብረሚካኤል በቀላሉ ለመቆጣጠር ጥረት ሲያደርግ ጠንካራው ኳስ በእጆቹ መካከል ሾልኮ ከመረብ ጋር ተገናኝቶ ሙሉ የጨዋታ ክፍለጊዜ ነጥብ ተጋርተው እንዲወጡ ሆኗል።
ከጨዋታ መጠናቀቅ በኋላ የፋሲል ከነማ አሰልጣኝ ውበቱ አባተ የአስራ ሰባት የአሰልጣኝነት አመታትን ልምድ በአንድ ላይ ጨምቀው ብዙ የተጋሉበት በጣም የተፈተኑበት አመት እንደሆነ ገልፀው በደጋፊዎች ድጋፍ ይሄንን አስቸጋሪ ጊዜ እንዳለፉ ተናግረዋል። የሲዳማ ቡና አሰልጣኝ አዲሴ ካሳ በሰጡት አስተያየት የሚጎልባቸው ነገር እንዳለና ዋንጫ ለማግኘት ተጠብቀው እሱ ግን እንዳልሆነ አንስተው በሚቀጥሉት ጊዜያት እንደሚያስተካክሉና ብዙ የቤት ስራ እንዳለባቸው ገልፀዋል።