ሪፖርት | ባህር ዳር ከተማ ሊጉን ሦስተኛ ደረጃ ላይ ሆኖ ቋጭቷል

ሪፖርት | ባህር ዳር ከተማ ሊጉን ሦስተኛ ደረጃ ላይ ሆኖ ቋጭቷል

የጣና ሞገዶቹ ቢጫዎቹን 3ለ0 በመርታት የውድድር ዘመኑን የሦስተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠው ፈፅመዋል።

ባለፈው ባህር ዳር በሀዋሳ ሲሸነፉ ከተጠቀሙት ቋሚ አሰላለፍ ውስጥ በሦስቱ ላይ ባደረጉት ለውጥ አላዛር ማርቆስን በይገርማል መኳንንት ፣ አምሳሉ ጥላሁንን በፍጹም ፍትሕአለው ፣ ቸርነት ጉግሳን በአቤል ማሙሽ በአንፃሩ በመቐለ በተመሳሳይ የተሸነፉት ወልዋሎች በበኩላቸው የአብስራ ሙሉጌታን በሳምሶን ተካ እና ስምዖን ማሩን በቡልቻ ሹራ ተክተው ለጨዋታው ቀርበዋል።

በደረጃ ሰንጠረዡ ሦስተኛ ላይ ለመቀመጥ ለባህርዳር ከተማ ከተጋጣሚው በበለጠ አስፈላጊ በነበረው የሳምንቱ የአራተኛ ቀን የመጀመሪያ ጨዋታ በመጀመሪያው አጋማሽ አስራ አምስቱን ደቂቃዎች ተመጣጣኝ እና በመስመሮች በኩል የሚደረጉ እንቅስቃሴዎችን የተመለከትንበት ቢሆንም በቀጣዮቹ ደቂቃዎች ግን የወልዋሎ ተጫዋቾች በግል የሰሯቸው ስህተቶች በተከታታይ ጎሎችን ለማስተናገድ እንዲገደዱ አድርጓቸዋል።

በ18ኛው ደቂቃ ፍሬው ሠለሞን ወደ ቀኝ ካዘነበለ ቦታ ከቅጣት ምት ያሻማውን ግብ ጠባቂው ናትናኤል ኪዳኔ ለማውጣት ጥረት ሲያደርግ የጨረፋት ኳስን ከጀርባ ሆኖ ያገኘው ሙጂብ ቃሲም ወደ ጎልነት በቀላሉ በመለወጥ ባህር ዳሮችን ቀዳሚ ማድረግ ችሏል።

መሪ መሆን ከቻሉ በኋላ ፈጣን በሆኑ ሽግግሮች ተጨማሪ ጎል ፍለጋ ብልጫውን የወሰዱት የጣና ሞገዶቹ 23ኛው ደቂቃ ፍሬው ሠለሞን ከማዕዘን ሲያሻማ ግርማ ዲሳሳ ላይ በሳጥን ውስጥ ናሆም ሀይለማርያም በሰራው ጥፋት የተገኘውን የፍፁም ቅጣት ምት በረከት ጥጋቡ ከመረብ አገናኝቶ የቡድኑን የጎል መጠን ወደ ሁለት ከፍም አድርጓል። በመጨረሻዎቹ የአጋማሹ አስር ደቂቃዎች ውስጥ አቤል ማሙሽ ጎል ለባህርዳር ጎል አስቆጥሮ ከጨዋታ ውጪ ተብላ ከተሻረችዋ አጋጣሚ በኋላ ጨዋታው ወደ መልበሻ ክፍል አምርቷል።

ወልዋሎን በይበልጥ አሻሽሎ የተመለሠው ሁለተኛው አጋማሽ በጎል ሙከራዎች ብዙም ያልደመቀ ቢሆንም ሜዳ ላይ ጥሩ ፉክክሮችን አስተውለንበታል። በ53ኛው ደቂቃ ላይ ከቅጣት ምት ናትናኤል ሠለሞን መቶ ይገርማል መኳንንት በያዘባቸው አጋጣሚ ሙከራን ያደረጉት ቢጫዎቹ በሽግግር ቶሎ ቶሎ ሳጥን አካባቢ ቢገኙም ህይወት የሚዘሩ ሙከራዎችን ግን በመሰንዘሩ  ደካሞች ነበሩ።

በተጋጣሚያቸው የእንቅስቃሴ ብልጫው ተወስዶባቸው የነበሩት እና ጥንቃቄ ላይ አመዝነው በመልሶ ማጥቃት የተጫወቱት ባህርዳሮች በመጨረሻዎቹ አስራ አምስት ደቂቃዎች በፈጠሯቸው ጫናዎች 78ኛው ደቂቃ ከማዕዘን ተቀይሮ የገባው ኪዳነማርያም ተስፋዬ አሻምቶ ፍቅረሚካኤል ዓለሙ በግንባር ገጭቶ ናትናኤል የያዘበት ከአንድ ደቂቃዎች መልስ ደግሞ ኪዳነማርያም አሾልኮ ያቀበለውን ኳስ አቤል ማሙሽ ከግብ ጠባቂው ናትናኤል ጋር አንድ ለአንድ ተገናኝቶ የተመከተበት ከቅጣት ምት ደግሞ ኪዳነማርያም በቀጥታ መቶ ናትናኤል ከያዘባቸው በኋላ ጨዋው 90ኛው ደቂቃ ጎል ተመልክተንበታል። ሔኖክ ይበልጣል በጥሩ ዕይታ የሰጠውን በቀኝ ሳጥን ይሄነው የማታ በድንቅ አጨራረስ ጎል አድርጎት ጨዋታው በመጨረሻም በባህርዳር ከተማ 3ለ0 አሸናፊነት ተጠናቋል። ይህንን ውጤት ተከትሎ ባህርዳር ዓመቱን ሦስተኛ ደረጃ ላይ በመቀመጥ ዓመቱን አጠናቋል።

ከጨዋታው መቋጫ በኋላ በተሰጡ አስተያየቶች የወልዋሎ አዲግራቱ አሰልጣኝ አታኽልቲ በርኸ ጨዋታው አሪፍ እንደነበር በመግለፅ በመጀመሪያው አጋማሽ ተጋጣሚያቸው በሁለተኛው ደግሞ ቡድናቸው ጥሩ እንደነበር በመዘናጋትም ጎል እንዳስተናገዱ ጠቁመው ዕድል ያላገኙ ተጫዋቾችን ቡድናቸው በመጨረሻ ሳምንታት ማሳየት እንደቻለ እንዲሁም እንደ አሰልጣኝ በሊጉ ጥሩም መጥፎም ነገሮችን ተምረው እንዳለፉበት ጠቁመዋል። የባህርዳር ከተማው ረዳት አሰልጣኝ ደረጀ መንግስቱ በበኩላቸው የሚፈልጉትን በጨዋታው ያገኙት ከዕረፍት በፊት መሆኑን ፣ አስበው የመጡትንም ነገር እንዳሳኩ ጠቁመው ከነበራቸው ጠባብ ስኳድ አንፃር ውጤቱ ደጋፊውን ባይመጥንም ሦስተኛ ደረጃን ይዘው መፈፀማቸው ትልቅ ነገር መሆኑን ገልፀዋል።