የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ በትናንትናው ዕለት ያወጣውን ውሳኔ በተመለከተ ዝርዝር ማብራሪያ እየተሰጠ ይገኛል።
የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት አቶ ኢሳይያስ ጂራ እና የፌዴሬሽኑ ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ ባህሩ ጥላሁን በወቅታዊ የኢትዮጵያ እግርኳስ ጉዳይ ዙሪያ ማብራሪያ እየሰጡ ይገኛሉ። በቅድሚያ መድረኩን የጀመሩት አቶ ኢሳያስ ጂራ ተከታዩን ማብራሪያ መስጠት ጀምረዋል።
“በመጀመሪያ ውሳኔዎቹ በፍትህ አካላት የተወሰኑ ናቸው። ይህ ውሳኔ ነው በመደበኛ ፍርድ ቤት እንዲቆም የተደረገው። የፋይናንስ ደንቡ ሲፀድቅ ከሊግ ካምፓኒው ጋር ተነጋግረን ነው። ማንም ሰው ከፍርድ ቤት ትዕዛዝ ውጪ መሆን አይችልም። እነሱ ጉዳዩን ወደ ፍርድ ቤት ሲወስዱ እኛ ወደ ፊፋ ነው ጉዳዩን የወሰድነው። ፊፋም ጥያቄያችንን ተመልክቶ የፍርድ ቤት እገዳውን እንዲያስነሱ ውሳኔ ሰጠ።
“ከሊግ ካምፓኒው ጋር በተደጋጋሚ አውርተን አራት ክለቦች ብቻ ናቸው የተያዙት። ስለዚህ ሌሎቹ ላይ ምርመራው እኩል አልሆነም። ከ18 ክለቦች 4 ክለቦች ብቻ ናቸው የተገኘባቸው። የ14 ክለቦች ገና ነው። ስለዚህ የፍትሀዊነት ጥያቄ አለ።
“እገዳው እንዲነሳ ጠየቅን። ክለቦቹም እገዳውን አስነስተው አመጡ። ከዛ በኋላ ውሳኔውን አወጣን። የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን የፍትህ አካል የወሰነውን ነው እኛ ያየነው። እኛ እንደ አመራር ውሳኔው የሚያመጣው ነገር የመመርመር ሀላፊነት አለብን። ስለዚህ ውሳኔው ሌሎቹን 14 ክለቦች ያማካለ ስላልሆነ ይህንን ውሳኔ ወስነናል።
“የሊጉን ተሳታፊዎች ቁጥር የመወሰን ስልጣን ያለው የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ስልጣን ነው። ይሄ ውሳኔ ያለውን ነገር ባላንስ ስለሚያረግ ነው ትናንት ያወጣነውን ውሳኔ ያወጣነው።
አሁን አስራ አራቱ ክለቦችን በተመለከተ ማጣራቱ እንዲፋጠን ከሚመለከተው አካል ጋር እየሰራን ነው። እኩል ሰርቀው በጊዜ የተደረሰበት ተጎድቶ በጊዜ ያልተደረሰበት ተጠቃሚ መሆን የለበትም።” ብለዋል።
መግለጫው አሁንም የቀጠለ ሲሆን በአሁኑ ሰዓት በስፍራው የተገኙ የብዙሃን መገናኛ አባላት ጥያቄዎችን እየጠየቁ ይገኛሉ።