“ዋናው ዓላማችን ፕሪሚየር ሊግ የሚሳተፉ ክለቦቻችን በመዲናችን እንዲጫወቱ ማድረግ ነው” ኢንጅነር ኃይለኢየሱስ ፍስሃ

“ዋናው ዓላማችን ፕሪሚየር ሊግ የሚሳተፉ ክለቦቻችን በመዲናችን እንዲጫወቱ ማድረግ ነው” ኢንጅነር ኃይለኢየሱስ ፍስሃ

የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግን በ2018 የውድድር ዘመን ወደ አዲስ አበባ ከተማ ከአራት ዓመታት በኋላ ለመመለስ እየተደረጉ ስለሚገኙ ጥረቶች የከተማው እግር ኳስ ፌዴሬሽን ከክለብ ስራ አስኪያጆች ጋር ውይይት አድርጓል።

በሀገሪቱ ከፍተኛ የሚባለው የእግር ኳስ ውድድር የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ መካሄድ ከጀመረ እነሆ ሀያ ሰባት ዓመታትን አስቆጥሯል ፣ በእነኚህም ዓመታቶች ውስጥ መዲናችን አዲስ አበባ ሀያ ሦስቱን የውድድር ዘመናት ስታከናውን ብትቆይም ላለፉት አራት ዓመታት ግን ይህንን ውድድር ማሰናዳቷን አቁማለች። የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ አክሲዮን ማህበር ሲቋቋም የመጀመሪያውን ዓመት ብቻ ያስተናገደው የአዲስ አበባ ስታዲየም በኮቪድ እና ሌሎች ጉዳዮችም ተደማምረው የከተማው ቡድኖች በሜዳቸው ማድረግ የሚችሏቸውን ጨዋታዎች በተለያዩ ከተሞች እያደረጉ ቆይተዋል። ላለፉት ሁለት ዓመታት ሊጉን ወደ  ከተማይቱ ለመመለስ በተለያዩ ጊዜያቶች እግር ኳሱን በሚመሩ ሰዎች ጥረቶች የነበሩ ቢሆንም የኋላ ኋላ ግን መሳካት ሳይችሉ የተጠናቀቀው የውድድር ዘመንን ጨምሮ ሳይካሄድ ሲጠናቀቅ ግድ ሲል አስተውለናል።

ነገር ግን በ2018 በሀያ ቡድኖች መካከል እንደሚካሄድ የሚጠበቀውን የሊግ ውድድር በድጋሚ ወደ መዲናይቱ ለመመለስ በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ ከሰሞኑ በፕሪምየር ሊጉ የሚሳተፉት ስድስቱ ክለቦች ማለትም ቅዱስ ጊዮርጊስ ፣ ኢትዮጵያ ቡና ፣ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ፣ ኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ፣ መቻል እና ኢትዮጵያ መድን በስራ አስኪያጆቻቸው አማካኝነት ከሰሞኑ ከአዲስ አበባ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የስራ አስፈፃሚ አባላት ጋር ሊጉን ወደ ወደ መዲናው በሚመጣበት ጉዳይ ላይ ከተወካዮቹ ጋር ሰፋ ያለ ውይይቶችን አድርጓል። በጉዳዩ ላይ የአዲስአበባ ከተማ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት ኢንጅነር ኃይለኢየሱስ ፍሰሃ በዋናነት ስለተነሱ ሀሳቦች ጠይቀናቸው ለሶከር ኢትዮጵያ ተከታዩን አጭር ማብራሪያ ሰጥተውናል።

“እንደማንኛውም ተመልካች አዲስ አበባ ላይ ውድድሩ አለመደረጉ ይቆጨናል። ምንድነው ባለመደረጉ ክለቦች የተጎዱት ከሚል ተነስተን ነው ይሄንን ለመስራት የፈለግነው ፤ ከሱም ተነስተን ወደ መዲናችን እግር ኳሱን መመለስ ነው። ዓላማችን ምንድነው ክለቦቻችን በገንዘብ በወጪም በገቢም ተጎድተዋል ፤ ስለዚህ ዋናው ዐላማችን ፕሪምየር ሊግ የሚሳተፉ ክለቦቻችን በመዲናችን እንዲጫወቱ ማድረግ ነው። ሁለተኛ እኛ ፀጥታውን መያዝ ነው እና ክለቦቻችን እና የከተማው መስተዳድር እንዲሁም ፌዴሬሽኑ ተቀራርበው እንዲሰሩ ማስቻል ነው። ምክንያቱም ተራርቀን ነበር። አንዱ እዛው ስብሰባ ላይ የተወቀስንበት ‘ነበራችሁ እንዴ? ምነው ዘገያችሁ’ ነው ያሉን ከተወካዮቹ አንዱ ስራ አስኪያጅ ‘አራት አመት ሙሉ አምስት አመት ሙሉ የት ነበራችሁ’ ተብለናል ፤ በዕርግጥ ከመቅረት ይሻላል ተብለናል። ክለቦች በሜዳቸው ሲጫወቱ ከተመልካች የትኬት ሽያጭ ገቢን ማስገኘት ነው። ሌላው ደግሞ ስነ ልቦናን ያገኛሉ። ምክንያቱም በሜዳ መጫወት ማለት አንዱ ጥቅሙ አሸናፊነትን መፍጠር ነው ደጋፊን ይዘህ ስትጫወት ይሄን ዐላማ ብለን ይዘናል። ሌላም ብዙ ጠቀሜታ አለው ኢኮኖሚካል ፣ ማህበራዊ ግንኙነት ጠቀሜታን ያመጣል እዚሁ መደረጉ ፤ ምክንያቱም ተጫዋቾቹን ታሳድጋለህ የህብረተሰብ አንድነት የስፖርቱን ተነሳሽነት ታመጣለህ ፣ ከስፖርት ሜዳ የራቀው በአብዛኛው የአዲስ አበባ ሰው ወደ ስታዲየም ማምጣት ትችላለህ የበፊቱን ድባብም መፍጠር ይቻላል።” ሲሉ የተደመጡት ፕሬዝዳንቱ የሸገር ደርቢን እንደ ከተማ ማጣታቸውም ጉዳቱ ከፍ ያለ መሆኑን ገልፀው በከተማው ፕሪምየር ሊጉ እንዲመለስ ከወጣቶች እና ስፖርት ቢሮ ጋር በጣምራ በመሆን የሚመለከተውን የበላይ አካል በመጠየቅ ተግባራዊ ለማድረግ ቁርጠኛ መሆናቸውን ጭምር አያይዘው ለዝግጅት ክፍላችን ተናግረዋል።