ወደ አሜሪካ ከሚያቀናው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን አባላት ውስጥ ስምንት ተጫዋቾች ከስብስብ ውጭ ሲሆኑ በእነርሱ ምትክ ሌሎች ተጫዋቾችን ለመጥራት መታሰቡን አውቀናል።
ከሁለት ቀን በፊት ወደ አሜሪካ በማቅናት ከዲሲ ዩናይትድ ጋር ላለበት ጨዋታ አሰልጣኝ መሳይ ተፈሪ ለ23 ተጫዋቾች ጥሪ በማድረግ ልምምዳቸውን በአዲስ አበባ ስታዲየም መጀመራቸው ይታወቃል።
ዛሬ ወደ አሜሪካ የሚያቀናው ቡድን አባላት የቪዛ ፍቃድ ለማግኘት ኤምባሲ መግባታቸውን እና ስምንት ተጫዋቾች እና ሁለት የአሰልጣኞች ቡድን አባላት ወደ አሜሪካ ማቅናት የሚችሉበትን ቪዛ መከልከላቸው እና ያረፉበትን ሆቴል ለቀው እንደሚወጡ መዘገባችን ይታወሳል።
በመሆኑም ስምንቱ ተጫዋቾች ግብ ጠባቂው ቢኒያም ገነቱ፣ ወገኔ ገዛኸኝ ፣ መሐመድ አበራ ፣ ያሬድ ካሳየ ፣ አህመድ ሁሴን ፣ ቢንያም ዐይተን፣ በረከት ደስታ እና አብዱልከሪም ወርቁ አሁን ቡድኑ በአዲስ አበባ ስታዲየም በሚያደርገው ልምምድ ላይ ሳይገኙ ቀርተዋል።
የስብስቡ ቁጥር ከ23 ወደ 15 ዝቅ ያለበት ብሔራዊ ቡድኑ ሌሎች የቪዛ ፍቃድ ያላቸውን ተጫዋቾችን ለመጥራት እንቅስቃሴ እየተደረገ መሆኑን እና ነገ ቡድኑን ሊቀላቀሉ እንደሚችሉ አውቀናል።