👉 “በኢትዮጵያ የሚገኝ አንድ ትልቅ ሕልም ያለው ቡድን ወደ ፊት አሰለጥናለሁ ብዬ አስባለሁ።”
👉 “በቅዱስ ጊዮርጊስ ለስድስት ዓመታት ትልቅ ልምድ በትልቅ ክለብ አግኝቻለሁ።”
👉 “አዛም ጋር በአፍሪካ ውድድሮች ላይ በተቻለ መጠን የተሻለ ጉዞ ማድረግ ነው እቅዳችን።”
የታንዛንያው አዛም ኢትዮጵያዊውን አዲስ ወርቁ ምክትል አሰልጣኝ አድርጎ መሾሙ ይታወቃል። ባለፈው የውድድር ዓመት ከዋና አሰልጣኝ ፍሎረንት ኢቤንጌ ስር በሱዳኑ አል ሂላል ስኬታማ ቆይታ የነበረው ወጣቱ አሰልጣኝ አሁንም ከአሰልጣኙ ጋር አብሮ ለመስራት ወደ አዛም ያቀና ሲሆን ከሶከር ኢትዮጵያ ጋር ያደረገውን አጭር ቆይታው እንደሚከተለው አቅርበንላችኋል።
ስለ ባለፉት ዓመታት ጉዞው ?
“ባለፉት አስር ዓመታት በግሌ በተቻለ መጠን ራሴን ለማሳደግ ሞክርያለሁ። በዚህም ሰሜን አየርላንድ ድረስ ሄጄ የ ዩኤፋ ‘C’ እና ዩኤፋ ‘B’ ትምህርቶችን ወስጃለው፤ እንዲሁም በባርሰሎና ሁለት አጫጭር ኮርሶች ለመውሰድ ችያለሁ። ከዛ በበለጠ ግን ራሴን መደበኛ ባልሆኑ ሁኔታዎች በባለፉት አስራ አምስት ዓመታት በላይ ራሴን ሳዘጋጅ እና ሳስተምር ቆይቻለሁ። በየ ዕለቱ እንግዲህ እግር ኳስ ተለዋዋጭ ነው፤ ከትናንት ዛሬ ከዛሬ ነገ የሚቀየር ተለዋዋጭ የሆነ ነገር ስለሆነ ሁልጊዜም የምትማርበት ነው፤ ያንንም አድርጌያለሁ። በዩጋንዳ ፣ በዛምቢያ፣ በሂላል እንዲሁም አሁን ደግሞ ከአዛም ጋር ለመስራት ተስማምቻለው። ከዛ በፊት ደግሞ በቅዱስ ጊዮርጊስ ለስድስት ዓመታት ትልቅ ልምድ በትልቅ ክለብ አግኝቻለሁ። ስለዚህ በእነዚህ መንገዶች ራሴን እያሻሻልኩ እየተማርኩ እገኛለሁ።
ከአዛም ጋር ስላለው ስምምነት ?
“ከአዛም ጋር ያለው ስምምነት አብሬ ለመስራት የተሾምኩት ከዋና አሰልጣኝ ፍሎረንት ኢቤንጌ ጋር ነው፤ በአል ሂላልም አብረን ሰርተናል ትልቅ የሆነ ሀሳብ እና ‘ፕሮጀክት’ ነበር። ከክለቡ ጋር በአፍሪካ ውድድሮች ላይ በተቻለ መጠን የተሻለ ጉዞ ማድረግ ነው እቅዳችን። ባለፉት ዓመታት በምድብ ድልድልም መግባት አልቻሉም ነበር አንዱ ይሄ ነው፤ በአጠቃላይ ግን በሦስት ዓመታት ውስጥ በአፍሪካ ትልቁ ተፋካካሪ ቡድን ማድረግ ነው እንደ ሀሳብ ያለው።”
ወደ ኢትዮጵያ እግር ኳስ የመመለሱን ጉዳይ ?
“እነዚህን የኢንተርናሽናል ልምዶች ካገኘሁ በኋላ አንድ ቀን እግዚአብሔር ሲፈቅድ ወደ ኢትዮጵያ መጥቼ ማሰልጠኔ አይቀርም። በኢትዮጵያ የሚገኝ አንድ ትልቅ ሕልም ያለው ቡድን ወደ ፊት አሰለጥናለሁ ብዬ አስባለሁ። ያ ደግሞ የጊዜ ጉዳይ ነው እንጂ ይሳካል ይሆናል ብዬ አምናለሁ። ትልቅ ኃላፊነት ያለው ትልቅ ቡድን፤ መቼ እንደሚሆን አላውቅም ግን እግዚአብሔር ሲፈቅድ የሚሆን ነገር ነው።”