በብዙ ሲያነጋግር ከነበረው የትላንቱ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ጨዋታ ጋር ተያይዞ ብዙም ልብ ያልተባለው አዲሱ የብሔራዊ ቡድናችን መለያ ጉዳይ ላይ የተወሰኑ ነጥቦችን ለማንሳት ወደድን።
ቅዳሜ ለእሁድ አጥቢያ በአውዲ ፊልዲ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን “ዲሲ ዩናይትድ” ገጥሞ 3-0 ማሸነፍ ችሏል ፤ በጨዋታውም በሜዳ ላይ ከነበሩ ብዙ አነጋጋሪ ጉዳዮች ባለፈ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በጣሊያኑ የትጥቅ አምራች ማክሮን የተመረተውን አዲሱን መለያ ለመጀመሪያ ጊዜ የተጠቀመበት ጨዋታ ሆኖ አልፏል።
በእርግጥ ማክሮን የብሔራዊ ቡድኑ ይፋዊ የትጥቅ አቅራቢ ስለመሆኑ እስካሁን በይፋ የተገለፀ ጉዳይ ባይኖርም ይፋዊ ባልሆኑ መንገዶች ግን ሁለቱ ተቋማት አብረው መስራት በሚችሉባቸው ጉዳዮች ዙርያ ስራዎች ስለመሰራታቸው እንዲሁም አዲሱን ትጥቅ የሚያስዋውቁ ስራዎች እየተሰሩ ስለመሆኑ በተለያዩ የማህበራዊ ትስስር ገፆች ስንመለከት ቆይተናል።
ታድያ ብሔራዊ ፌደሬሽኑ በስምምነቱ እና ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች ላይ ይፋዊ የሆነ መግለጫን ባልሰጠበት ሁኔታ ብሔራዊ ቡድን የማክሮን ትጥቅን ለብሶ ጨዋታውን የማድረጉ ጉዳይ ቀዳሚው የግልፀኝነት ጥያቄን የሚያስነሳው ጉዳይ ነው።
ሌላው ጉዳይ የትላንቱ ጨዋታ ማክሮንን ባለፉት አስር ዓመታት ብቻ የኢትዮጵያ ወንዶች ብሔራዊ ቡድን ይፋዊ የመጫወቻ ትጥቅ አቅራቢ የሆነ ስድስተኛ ተቋም ያደርገዋል ፤ ይህም በአማካይ ብሔራዊ ፌደሬሽኑ በአንድ ዓመት ከግማሽ አካባቢ የትጥቅ አቅራቢ ይቀይራል እንደማለት ነው ይህም ምናልባት በዓለም አቀፍ ደረጃ በዚህ ፍጥነት የትጥቅ አቅራቢ የቀየረ ተቋም ፈልጎ ማግኘት የሚቻል አይመስልም።
በእግር ኳሱ የተሻለ በተራመዱት ሀገራት ለአብነት የጀርመን ብሔራዊ ፌደሬሽን ከጀርመኑ አዲዳስ ጋር ለ70 ዓመታት የዘለቀ እንዲሁም ናይኪ እና የብራዚል ብሔራዊ ፌደሬሽን ለ30 ዓመታት የተሻገረ አብሮ የመስራት አይነት ታሪኮች የተለመዱ በሆኑበት ዓለም እኛ ጋር ያለው ልምምድ ግን ፍፁም ተቃራኒ ነው።
በፈርጀ ብዙ የሜዳ እና የሜዳ ውጭ ጉዳዮች እግር ከወርች ለተያዘው እግር ኳሳችን ምናልባት የትጥቅ ጉዳዮችን በዚህ ልክ ትኩረት ሰጥቶ ማንሳት ቅንጦት ቢመስልም ከላይ የቀረበው ማሳያ እግር ኳሳችን ውስጥ ስለገነገነገው የዕለተ ተዕለቷን ብቻ የማሰብ መጥፎ አባዜ ጋር በጉልህ የሚታይ ነው።
እርግጥ ብሔራዊ ፌደሬሽኑ ከቀደሙት ዓመታት አንፃር በርካታ አዎንታዊ ስራዎች በተለይ በእግር ኳስ ልማት ላይ እየሰራ ስለመሆኑ የማይካድ ሀቅ ቢሆንም አሁንም ግን ያልተሻገራቸው ውስንነቶች ስለመኖራቸው ይህ የትጥቅ አቅርቦት ጉዳይ አይነተኛ ማሳያ ነው።
በተለይ ከአስር ዓመት ባነሰ ጊዜ ውስጥ ፌደሬሽኑ ወደ ስድስተኛ ትጥቅ አቅራቢ ፊቱን ለማዞር የመወሰኑ ጉዳይ በተለያዩ አውዶች እንኳን ለመመልከት ብንሞክር ትክክለኛ ነው ለማለት የሚያበቃ አመክንዮ ለማግኘት ከባድ ይመስላል ፤ በተለይም በእያንዳንዱ የትጥቅ ስምምነቶች ላይ ሁሌም ስለሰፋፊ ውጥኖች ሲነሳ ላደመጠ “ሩቅ አሳቢ ቅርባ አዳሪ” እንዲል የሀገሬው ሰው ነው ነገሩ።
ተፎካካሪ ብሔራዊ ቡድን የመገንባቱ ጉዳይ የረጅም ጊዜ ትልም ውጤት እንደሆነ እሙን ነው ፤ ታድያ ብሔራዊ ቡድናችን ከትጥቅ መለዋወጥ ባለፈ በብዙ መልኩ የረጅም ጊዜ ውጥን አልባ ስለመሆኑ ብዙ ማሳያዎችን ማንሳት ይቻላል።
እንደው ከትጥቅ አንፃር ነገሩን ጠበብ ስናደርገው ከአቅራቢዎቹ መፈራረቅ በስተጀርባ ከእያንዳንዱ ተቋማት ጋር የሚደረጉት ስምምነቶች ዘለቄታዊ ጠቀሜታቸው እና ተያያዥ ጉዳዮች ላይ በቂ ጥናት እና ትንተና ሳይደረጉ የመፈፀማቸው ጉዳይ ስምምነቶቹን ላይ ጥያቄ እንድናነሳ ያደርጉናል፡።
ለአብነትም ከማክሮን በፊት ፌደሬሽኑ ረዘም ላለ ጊዜ ጥናቶችን አከናውኖ ከፍተኛ መዋዕለ ነዋይ በማፍሰስ ወደ ተግባር እንደገባበት የተናገረው የራሱ የሆነው የ”ሀገሬ ስፖርት ትጥቅ ብራንድ” ጉዳይን ማንሳት ተገቢ ነው ፤ በርከት ያሉ የአፍሪካ የእግር ኳስ ፌደሬሽኖች የራሳቸው የሆነ የትጥቅ ብራንድ ይዘው መምጣት ፋሽን እየሆነ በመጣበት በዚህ ወቅት ፌደሬሽናችንም ባሳለፍነው ዓመት ግንቦት ወር ላይ ይህን ብራንድ ይፋ ያደረገው ታድያ ይህ ትጥቅ ይፋ ከተደረገ ከአንድ ዓመት ከሁለት ወር ባነሰ ጊዜ ብሔራዊ ቡድኑን በሌላ ተቋም መለያ ተመልክተናል።
በተለይ ከፍተኛ ገቢ ለፌደሬሽኑ እንደሚፍጥር ይጠበቅ በነበረው እና ከዚህ ቀደም የብሔራዊ ቡድኑ ትጥቅ አቅራቢዎች ይወቀሱበት የነበረው የብሔራዊ ቡድኑ ትጥቆችን(merchandise) ሰፊ ፍላጎት ላለው የሀገር ውስጥ እና የውጭ ገበያ በማቅረብ አንፃር እስካሁን ይህ ነው የሚባል ስራ ሳይሰራ በሌላ አቅራቢ የመተካቱ ጉዳይ ነው።
ሌላኛው ትኩረት የሚሻው ጉዳይ እንደ ኢትዮጵያ ላለ ከፍተኛ የውጭ እና ገቢ ንግድ ምጣኔ መፋለስ (Macro Economic imbalance) ክፉኛ የታመመውን ኢኮኖሚያችንን ለማከም በመንግስት ደረጃ በተዘጋጀው እና ለትግበራው ልዩ ትኩረት በተሰጠው የሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ ውስጥ በጉልህ እንደተቀመጠው የሀገር ውስጥ ምርትን በማሳደግ በሂደት ከገቢ ንግድ አንፃር ያለውን ድርሻ ለማሳደግ ከተቀመጠው አካሄድ አንፃር የአሁኑ የፌደሬሽኑ ውሳኔ የተጣረሰ ይመስላል።
ምክንያቱም ምንም እንኳን ከምርት ጥራት እና ትዕዛዞችን በተባለው ጊዜ ከማቅረብ አንፃር በሀገር በቀል ትጥቅ አቅራቢዎች ዘንድ ውስንነቶች እንዳሉ ቢሰማም ይህን መንግስታዊ ፖሊሲ ወደ መሬት በማውረድ ረገድ የአንበሳውን ድርሻ መውሰድ ይገባው የነበረው ብሔራዊ ፌደሬሽኑ ፊቱን የማዞሩ ጉዳይ ካለብን የውጭ ምንዛሬ እጥረት ጋር ተዳምሮ በትልቁ ጥያቄ የሚያስነሳ ነው።
ከዚህ ባለፈም ሌሎች የአፍሪካ ሀገራት የኢትዮጵያ ምርቶችን መጠቀም በጀመሩበት በዚህ ወቅት የፌደሬሽኑ ውሳኔ እጅጉን እየተነቃቃ ለሚገኘው የሀገር ውስጥ የስፖርት ትጥቅ አምራች ኢንደስትሪው የሚያስተላልፈው አሉታዊ መልዕክት ሌላኛው ጉዳይ ነው።
ሌላኛው ትኩረት የሚፈልገው መጠን ፌደሬሽኑ ከዚህ ቀደም አብረውት ይሰሩ ከነበሩት የትጥቅ አቅራቢዎች በተለይ ባለፉት ጥቂት ዓመታት ከኤርያ እስከ ኡምብሮ ድርጅቶች ላይ ፌደሬሽኑ በተለይ ምርቶች ከውጭ አጓጉዞ ወደ ሀገር ማስገባት ላይ ይስተዋሉ የነበሩ ክፍተቶችም እንዲሁ መልስን ይሻሉ።
በመጨረሻም ከትጥቅ አቅራቢዎች መለዋወጥ ባለፈ የሁሉም ኢትዮጵያዊ ፍላጎት የእኔ የሚለው ብሔራዊ ቡድኑ ውጤታማ እንዲሆን ይሻል ይህን ለማድረግ ደግሞ ሁለንተናዊ የሆነ የረጅም ጊዜ ትልም እጅግ አስፈላጊ ነው በመሆኑ ልክ እንደ “Road to 2029” አይነት የተጀመረ መሰል ውጥኖች ማጠናከር እንዲሁም በትጥቅ እና ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች ላይ የሚስተዋሉ ጥቃቅን የሚመስሉ ነገርግን ወሳኝ የሆኑ ጎታች እሳቤዎችን ወደ ጎን በማድረግ የሁላችንም የዘወትር ምኞት የሆነውን ውጤታማ ቡድን እውን ለማድረግ መትጋት ይኖርበታል።