የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ያወጣው መግለጫ እንደሚከተለው ተቀምጧል።
የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ አክሲዮን ማህበር የፋይናንስ አሰራር ተቆጣጣሪ ኮሚቴ በክለቦች እና ተጫዋቾች ላይ ባደረገው ምርመራ የፋይናንስ መመሪያውን ተላልፈው የተገኙ ክለቦች ላይ የቅጣት ውሳኔ መወሰኑ፤ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የይግባኝ ሰሚ ኮሚቴም ጉዳዩን ከተመለከተ በኋላ ውሳኔው እንዲፀና ማድረጉ ይታወሳል።
ይህንን ተከትሎ ቅጣቱ ከተጣለባቸው አራት ክለቦች ውስጥ ሲዳማ ቡና፣ ሀዋሳ ከተማ እና መቻል ስፖርት ክለብ ጉዳዩን ወደ መደበኛ ፍርድ ቤት በመውሰድ እና ከዓለም ዓቀፍ ስፖርታዊ አሰራር ውጪ እንዲታይ በማድረግ “የተጫዋቾችን ዕግድ አስነስተናል” በሚል የኢትዮጵያ ዋንጫ የፍፃሜ ጨዋታን ጨምሮ በተከታታይ ጨዋታዎች ላይ ከፌዴሬሽኑ ፈቃድ ውጪ ተጫዋቾቹን ሲጠቀሙ እንደቆዩ ይታወቃል።
የፊፋን ስፖርታዊ ኮንቬንሽን በመጣስ ጉዳዩን ወደ መደበኛ ፍርድ ቤት የወሰዱ ክለቦቹ ምዝገባ በፊፋ እንዲታገድ የተጀመረውን ሂደት ተከትሎም ክለቦቹ የፍርድ ቤት ሂደቱን ያቋረጡ ሲሆን የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ክለቦቹ ያልተገቡ ተጫዋቾችን ባሰለፉባቸው ጨዋታዎች በሙሉ በፎርፌ ተሸናፊ እንዲሆኑ ውሳኔ ማሳለፉ ይታወሳል።
ይህንን ተከትሎ የሲዳማ ቡና እግር ኳስ ክለብ ጉዳዩን ወደ ዓለምአቀፉ የስፖርት ገላጋይ ፍርድቤት (CAS) በመውሰድ ይግባኝ የጠየቀ ሲሆን የይግባኝ ሂደቱም በቁጥር “CAS 2025/A/11595 Sidama Bunna Football Club Vs Ethiopian Football Federation” ተመዝግቦ እየታየ ቆይቷል።
ሲዳማ ቡና እግር ኳስ ክለብ የክስ ሂደቱ በሚታይበት ወቅት የፌዴሬሽኑ ውሳኔ በጊዜያዊነት እንዲታገድ ያቀረበውን ጥያቄ የዓለም አቀፉ የስፖርት ገላጋይ ፍርድ ቤት (CAS) የይግባኝ ግልግል ክፍል ተመልክቶ በምክትል ፕሬዘዳንቱ አማካኝነት በወጣ ደብዳቤ ጥያቄውን ውድቅ እንዳደረገ አሳውቋል።
በመጨረሻም የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ሲዳማ ቡና ስፖርታዊ ግጭቶች የሚፈቱበትን የፊፋ እና የዓለም አቀፉ ኦሎምፒክ ኮሚቴ መመሪያዎች በመከተል ጉዳዩን ወደ ዓለም አቀፉ የስፖርት ገላጋይ ፍርድ ቤት (CAS) መላኩ የሚበረታታ ትክክለኛ አሰራር መሆኑን ይገልፃል።