በካፍ የሴቶች ቻምፒየንስ ሊግ የሴካፋ ዞን የቅድመ ማጣሪያ ጨዋታ የሚጠብቀው ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በሦስት የተለያዩ ቦታዎች የሚጫወቱ ሦስት ናይጄሪያዊ ተጫዋቾችን በትናንትናው ዕለት ወደ ሀገራችን አምጥቷል።
በኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ ላይ የበላይ መሆን የቻለው ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የተጠናቀቀውን የውድድር ዘመን የሊግ ሻምፒዮን መሆኑን ተከትሎ ኢትዮጵያን በመወከል ባለፈው ዓመት አሸናፊ መሆን በቻለበት የካፍ ቻምፒየንስ ሊግ የሴካፋ ዞን የማጣሪያ ጨዋታ ላይ ለተከታታይ አምስተኛ ጊዜ ኢትዮጵያን ወክሎ ኬኒያ በሚሰናዳው ውድድር ላይ ከሀያ ስምንት ቀናቶች በኋላ ተካፋይ የሚሆን ይሆናል።
በአሰልጣኝ ብርሀኑ ግዛው የሚመራው ቡድኑ ራሱን ለማጠናከር ከሀገር ውስጥ ክለቦች ከሀዋሳ ከተማ እሙሽ ዳንኤል ፣ እፀገነት ግርማ ፣ ቤቴልሔም ግዛቸው እና ትዕግሥት አዳነን ከቂርቆስ ደግሞ ምርቃት ፈለቀን ወደ ስብስባቸው በመቀላቀል ውላቸው የተጠናቀቁ ተጫዋቾችን ኮንትራት ደግሞ በማራዘም በሀዋሳ ከተማ ከሐምሌ 20 ጀምሮ የቅድመ ውድድር ዝግጅታቸውን መከወን የጀመሩ ሲሆን በዛሬው ዕለት ደግሞ በኢትዮጵያ ሴቶች እግር ኳስ ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ ከሀገር ውጪ የናይጄሪያ ዜግነት ያላቸውን ሦስት ተጫዋቾች ወደ ቡድኑ ለመቀላቀል ሀገር ውስጥ አመሻሹን መድረሳቸውን ሶከር ኢትዮጵያ አውቃለች።
የናይጄሪያን የሴቶች ፕሪሚየር ሺፕ የዓመቱ ኮከብ ጎል አግቢ ማረፊያዋን የኢትዮጵያውን ክለብ አድርጋለች። በቅርቡ በተሰናዳው የካፍ የሴቶች የአፍሪካ ዋንጫ ላይ ሀገሯን ወክላ አለመካፈሏ ቅሬታን እንዳስነሳ የሚነገርላት የ22 ዓመቷ የቀድሞዋ የሰንሻይንስ ኪዊን አጥቂ ቦላጂ ኦላሚንዴ በተጠናቀቀው ዓመት በሀገሯ ሊግ ለሪዮ ስታርስ ሌዲ ቡድን ተሰልፋ አስራ አምስት ጎሎችን በማስቆጠር የሊጉ ከፍተኛ ጎል አስቆጣሪ ሆና ማጠናቀቋ ይታወሳል።
ሌላኛዋ ፈራሚ አንድ ሜትር ከሰባ አምስት ሴንቲ ሜትር የምትረዝመው የሀያ አመቷ ግብ ጠባቂ ፌይዝ ኦሚላና ነች። ሀገሯን ወክላ ከ17 እና ከ20 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድኖች ውስጥ ያገለገለችው እና ለሀገሯ ክለቦች ቪክትሪ ፣ ሌጎስ ፣ ድሪም እና ናይጃ ሬተልስ ተጫዋች የነበረችው ሁለተኛዋ የንግድ ባንክ አዲሷ የውጪ ዜጋ ተጫዋች ሆናለች።
ሦስተኛዋ ፈራሚ የ27 ዓመቷ ኦፔይሚ ሳንደይ ሆናለች። ሀገሯን ከዚህ ቀደም በዕድሜ ዕርከን እና በዋናው ቡድንም ጭምር ያገለገለችው እና በሀገሯ ክለቦች ሰንሻይን ኪዊንስ ፣ ኢዶ ኪዊንስ እና በመጨረሻም በሪሞ ስታርስ በመጫወት ያሳለፈችው የመሐል ተከላካዩዋ ቀጣዩ መዳረሻዋ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሆኗል።