ሸገር ከተማ ፊቱን ወደ አዲስ አሰልጣኝ አዙሯል

ሸገር ከተማ ፊቱን ወደ አዲስ አሰልጣኝ አዙሯል

ከከፍተኛ ሊጉ ካሳደገው አሰልጣኝ ጋር በአዲሱ የላይሰንስ ፍቃድ ምክንያት መቀጠል ያልቻለው ሸገር ከተማ አዲስ አሰልጣኝ ለመሾም ስምምነት ላይ መድረሱን ሶከር ኢትዮጵያ ያገኘችው መረጃ ጠቁሟል።

ከተመሠረተ በሁለተኛ ዓመቱ ከከፍተኛ ሊጉ በማደግ በ2018 የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ላይ ተካፋይ የሆነው ሸገር ከተማ ከፊቱ ለሚጠብቀው የሊጉ ውድድር ከከፍተኛ ሊጉ ባሳደገው አሰልጣኝ በሽር አብደላ እንደሚመራ እና አሰልጣኙም ለሁለት ዓመታት ከክለቡ ጋር ለመዝለቅ ቅድመ ስምምነትን የፈፀሙ ቢሆንም የኋላ ኋላ ግን የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌድሬሽን ባወጣው የአሰልጣኞች ፍቃድ መመሪያ መሠረት መቀጠል ባለመቻላቸው አዲስ አሰልጣኝ ለመቅጠር ከሰሞኑ እንቅስቃሴ ሲያደርግ ክለቡ ቆይቷል። በዚህም የተነሳ ሦስት አሰልጣኞችን ለመቅጠር ሲያፎካክር ከሰነበተ በኋላ በመጨረሻም አሸናፊ በቀለን ምርጫው ስለማድረጉ ሶከር ኢትዮጵያ ያገኘችው መረጃ አመላክቷል።

የቀድሞው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ፣ መቻል ፣ ኢትዮ ኤሌክትሪክ ፣ ሲዳማ ቡና ፣ አዳማ ከተማ ፣ ወላይታ ድቻ ፣ ሀድያ ሆሳዕና እና ጅማ አባጅፋር አሰልጣኝ የነበሩት አሸናፊ በቀለ ፋሲል ከነማን ከለቀቁ በኋላ የተጠናቀቀውን የውድድር ዘመን ወልዋሎን በመያዝ በጥቂት ጨዋታዎች ቡድኑን ከመሩ በኋላ በመጨረሻም ለመለያየት መገደዳቸው የሚታወስ ሲሆን አሁን ደግሞ ለቀጣዩ ዓመት በአዲስ አዳጊው ሸገር ከተማ የምንመለከታቸው ይሆናል።

ከክለቡ ጋር በተያያዘ ባሳለፍነው የውድድር ዘመን በሁለቱም ፆታ ወደ ፕሪምየር ሊጉ ላሳደጉ የቡድኑ አባላት የፊታችን ማክሰኞ የሽልማት ስነ ስርዓት እንደሚደረግላቸውም ሰምተናል። የአሠልጣኝ አሸናፊ በቀለ ሹመትም ከማክሰኞው መርሐ-ግብር በኋላ ይፋ እንደሚሆን ይጠበቃል።