ኢትዮጵያዊው የአጥቂ መስመር ተጫዋች ፉአድ ኢብራሂም በሰርቢያ ሱፐር ሊግ ለሚወዳደረው ኤፍኬ ቮቮዲና ለመቀላቀል ከጫፍ መድረሱ ተነግሯል፡፡ ፉአድ ከዚህ ቀደም ለፊንላንዱ የ2ኛ ዲቪዚዮን ክለብ ኤሲ ካያኒ የተጫወተ ሲሆን ከካያኒ ጋር ከተለያየ በኃላ ያለፉትን ረጅም ወራት ክለብ አልባ ሆኖ ቆይቷል፡፡ የቀድሞ የቶሮንቶ እና የሜንሶታ ስታርስ የ23 ዓመት አጥቂ ቮቮዲናን የሚቀላቀለው ለሙከራ አልያም በቋሚ ኮንትራት ያልተረጋገጠ ሲሆን አዲሱን ክለቡን ታህሳስ 30 ላይ የሚቀላቀል ይሆናል፡፡
ቮቮዲና በሰርቢያ ሱፐር ሊግ ባሳለፍነው የውድድር ዘመን 4ኛ ሆኖ ያጠናቀቀ ሲሆን በሰርቢያ እግርኳስ ውስጥ ከሬድ ስታር ቤልግሬድ እና ፓርቲዛን ቤልግሬድ ቀጥሎ ሶስተኛው ስኬታማ ክለብ ነው፡፡ ከዚህ ቀደም ኢትዮጵያዊው የአልሃሊ አጥቂ ሳላዲን ሰይድ በሰርቢያው ፓርቲዛን ቤልግሬድ የሙከራ ጊዜ ያሳለፈ ሲሆን የአለማቀፉ የፕሮፌሽናል እግርኳስ ተጫዋቾች ፌድሬሽን (FIFAPro) የእግርኳስ ተጫዋቾች በከፍተኛ የፋይናንስ ችግር ውስጥ ወደመገኙት የሰርቢያ ክለቦች እንዳይጓዙ ማስጠንቀቁ አይረሳም፡፡
ፉአድ ማርያኖ ባሬቶ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድንን ከያዙ ጀምሮ አንድ ጊዜ የተጠራ ሲሆን፣ ከዩጋንዳ ጋር ለነበረው የወዳጅነት ጨዋታ የብሄራዊ ቡድኑ አባል ሆኖ ወደ ካምፓላ ማቅናቱ ይታወሳል፡፡