ቅዱስ ጊዮርጊስ ሁለት ተጫዋቾቹን ሲለቅ ብራያን ኡሞኒን ማስፈረሙ እየተነገረ ነው

 

የዓምናው የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ቻምፒዮን ቅዱስ ጊዮርጊስ በክረምቱ የዝውውር መስኮት ያስፈረማቸው ሴኔጋላዊው የመስመር ተጫዋች ኦስማን ኢምቤንጎ እና ኬንያዊውን አጥቂ ጆብ ኦሞስን ማሰናበቱ ተነግሯል፡፡ ኦስማን በደጋፊዎች በኩል ከፍተኛ ተቀባይነትን ያገኘ አግኝቶ የነበረ ሲሆን ፤ በአዲስ አበባ ካስትል ሲቲ ካፕ ላይ ድንቅ ብቃቱን ካሳዩ የቅዱስ ጊዮርጊስ ተጫዋቾች መካከል የሚጠቀስ ነበር፡፡ ኦስማን ለቅዱስ ጊዮርጊስ ለመጨረሻ ጊዜ የተሰለፈው በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ላይ ፈረሰኞቹ ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ጋር 1-1 በሆነ አቻ ውጤት ሲለያዩ ነበር፡፡

ከኦስማን መልቀቅ በተጨማሪ የቀድሞ የዌስተርን ስቲማ አጥቂ ኬኒያዊው ጆብ ኦሞስ በፈረሰኞቹ የስንብት ደብዳቤ ደርሶታል፡፡ ጆብ በቀድሞ የቅዱስ ጊዮርጊስ ተጫዋች ፋራንሲስ ቻንጂሊ ጠቋሚነት ወደ ኢትዮጵያ የመጣ ቢሆንም በፈረሰኞቹ ቤት የረባ እንቅስቃሴ ሳያሳይ ክለቡን ለቋል፡፡

በካፍ ቻምፒየንስ ሊግ የቅድመ ማጣሪያ ዙር ከአልጄሪየው ኤም.ሲ. ኡልማ ጋር የተደለደለው ቅዱስ ጊዮርጊስ ክለቡን ለማጠናከር ከሌሎች ሀገራት ተጫዋቾችን ማሰስ ጀምሯል፡፡ አንድ ካሜሮናዊ አጥቂ በክለቡ የሙከራ ጊዜ እያሳለፈ ሲሆን እንደ አንዳንድ የዩጋንዳ የስፓርት ድህረገፃች መረጃ ደግሞ የቀድሞው የሱፐር ስፓርት አጥቂ ብራያን ኡሞኒ ለቅዱስ ጊዮርጊስ ለመጫወት ለሁለት ዓመት በ35ሺህ የአሜሪካ ዶላር መፈረሙን እየተናገሩ ይገኛል፡፡ ነገር ግን ኡሞኒ ዝውውሩን ሀሰት ሲል ገልፆታል፡፡ “ይሄ ሀሰት ነው ምክንያቱም እኔ አሁንም የካምፓላ ሲቲ (KCCA) ተጫዋች ነኝ፡፡” ሲል ስለ ዝውውሩ ምንም እንደማያውቅ ተናግሯል፡፡ ባሳለፍነው የውድድር ዘመን ከታንዛኒው አዛም ጋር የታንዛንያ ፕሪሚየር ሊግ ቻምፒዮን የሆነው ኡሞኒ በአሰልጣኝ ቦቢ ዊልያምስ ስር ከዩጋንዳ ብሄራዊ ቡድን ጋር የሴካፋ ዋንጫን አሸንፏል፡፡ በ2015 የአፍሪካ ዋንጫ ማጣርያ በአሰልጣኝ ሚቾ ስር ለአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ለዩጋንዳ ብሄራዊ ቡድን ተጫውቷል፡፡

በተያያዘ ዜና የቅዱስ ጊዮርጊስ ስም ከኬንዊው የተስካር የአጥቂ መስመር ተጫዋች ጄስ ዌር ዝውውር ጋር ተያይዞል፡፡ የ32 ዓመቱ አጥቂ ዌር በቅዱስ ጊዮርጊስ ይፈለግ አይፈለግ እስካሁን አልታወቀም፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *