መቐለ 70 እንደርታዎች አሰልጣኝ ለመሾም ተቃረቡ

መቐለ 70 እንደርታዎች አሰልጣኝ ለመሾም ተቃረቡ

አሰልጣኝ ጌታቸው ዳዊት ለሦስተኛ ጊዜ ወደ ምዓም አናብስቱ ቤት ለመመለስ ከጫፍ ደርሰዋል።

በ2018 የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ላይ ተሳታፊ የሆኑት መቐለ 70 እንደርታዎች አዲስ አሰልጣኝ ለመሾም ከስምምነት ደርሰዋል። ሐምሌ 3 የክለቡ ቦርድ ባስቀመጠው አቅጣጫ መሰረት አዲስ አሰልጣኝ ለመቅጠር በእንቅስቃሴ ላይ የቆዩት ምዓም አናብስቱ በርከት ያሉ አማራጮች በመመከት ላይ ከቆዩ በኋላ በስተመጨረሻ ባለፈው የውድድር ዓመት በስሑል ሽረ ቆይታ የነበራቸው የቀድሞ የክለቡ አሰልጣኝ ጌታቸው ዳዊትን በዋና አሰልጣኝነት ለመቅጠር ከጫፍ ደርሰዋል።

ከዚህ ቀደም ከ2003 እስከ 2006 እንዲሁም በ2009 ምዓም አናብስትን ያሰለጠኑት እና በ2009 ቡድኑን ወደ ፕሪምየር ሊግ ያሳደጉት አሰልጣኙ ክለቡን ዘለግ ላሉ ዓመታት በማሰልጠን ቀዳሚ ሲሆኑ ከዚህ ቀደም አልመዳ ጨርቃጨርቅ፣ ደደቢት ፣ ወልዋሎ፣ አክሱም ከተማ፣ ወሎ ኮምቦልቻ እንዲሁም ስሑል ሽረን ማሰልጠናቸው ይታወቃል። አሁን ደግሞ መስከረም 23፡ 2010 ዓ.ም ከመቐለ 70 እንደርታ ጋር ከተለያዩ ከዓመታት በኋላ በ2018 የውድድር ዓመት መቐለ 70 እንደርታን ለማሰልጠን ከጫፍ ደርሰዋል።