ካርሎስ ዳምጠው በጦና ንቦቹ ቤት ለመቆየት ተስማማ

ካርሎስ ዳምጠው በጦና ንቦቹ ቤት ለመቆየት ተስማማ

ግዙፉ አጥቂ ከጦና ንቦቹ ጋር ለመቀጠል ተስማምቷል።

ሀገራችን ወክለው በካፍ ኮንፌዴሬሽን ዋንጫ የሚሳተፉት እና ቀደም ብለው የቢኒያም ገነቱ፣ መሳይ ሰለሞን፣ ያሬድ ዳርዛ ፣ ኬኔዲ ከበደ ፣ አብነት ይስሃቅ፣ ዮናታን ኤልያስ እና መልካሙ ቦጋለን ውል አራዝመው በፍቃዱ ሕዝቅኤልን ያስፈረሙት ወላይታ ድቻዎች አሁን ደግሞ ካርሎስ ዳምጠውን ለተጫማሪ ሁለት ዓመታት በቡድናቸው ለማቆየት ከስምምነት ደርሰዋል።

ባለፈው የውድድር ዓመት በ32 ጨዋታዎች ተሳትፎ 2524′ ደቂቃዎች ቡድኑን ያገለገለው እና በውድድር ዓመቱ ሰባት ግቦች በማስቆጠር የጦና ንቦቹ ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪ የነበረው አጥቂው ስሙ ከበርካታ ክለቦች ጋር እየተያያዘ ቢቆይም በስተመጨረሻ ከክለቡ ጋር ለመቆየት ተስማምቷል።

ከዚህ ቀደም በመቻል፣ አውስኮድ፣ መቐለ 70 እንደርታ፣ ወልዋሎ፣ ኢትዮ ኤሌክትሪክ፣ ድሬዳዋ ከተማ እንዲሁም ከባለፈው የውድድር ዓመት ጀምሮ በጦና ንቦቹ ቤት ቆይታ በማድረግ ላይ የሚገኘው ካርሎስ ዛሬ ውሉን ለማራዘም መስማማቱን ተከትሎ በቀጣይ ቀናት ለቅድመ ውድድር ዝግጅት ቡድኑን ይቀላቀላል ተብሎም ይጠበቃል።