ቀደም ብለው በርከት ያሉ ዝውውሮች ያገባደዱት ወልዋሎዎች ቡድናቸውን ማጠናከር ቀጥለውበታል
በዝውውር ንቁ ተሳታፊ በመሆን ቡድናቸውን በማጠናከር ላይ ያሉትና ቀደም ብለው ስድስት ተጫዋቾችን ያስፈረሙት ወልዋሎዎች አሁን ደግሞ ሁለገቡ ነፃነት ገብረመድህን አስፈርመዋል።
በተጠናቀቀው የውድድር ዓመት ከአራት ዓመታት በኋላ ወደ ስሑል ሽረ ተመልሶ ከክለቡ ጋር ቆይታ ያደረገው ተጫዋቹ ቡድኑን በአምበልነት በመራበት ውድድር ዓመት በ24 ጨዋታዎች ተሳትፎ 2160′ ቡድኑን ያገለገለ ሲሆን አሁን ደግሞ የክረምቱ የዝውውር መስኮት የወልዋሎ ሰባተኛ ፈራሚ በመሆን ቡድኑን ተቀላቅሏል።
ከስሑል ሽረ ታዳጊ ቡድን ተገኝቶ አሳዳጊ ክለቡን እስከ 2012 ዓ.ም ድረስ በማገልገል በወላይታ ድቻ፣ ኢትዮ ኤሌክትሪክ እንዲሁም በ2017 የውድድር ዓመት ዳግም ወደ ስሑል ሽረ ተመልሶ ዓመቱን ያጠናቀቀው ነፃነት በመሀል ተከላካይነት እንዲሁም በአማካይ ተከላካይነት መጫወት የሚችል ሁለገብ ተጫዋች ነው።