በጣና ሞገዶቹ ቆይታ የነበረው ተጫዋች ወደ ምዓም አናብስት ለመቀላቀል ተቃርቧል።
ለ2018 የውድድር ዓመት ቡድናቸውን ለማጠናቀር በእንቅስቃሴ ላይ ያሉትና ቀደም ብለው ሱሌይማን ሐሚድ፣ መሐሪ አመሀ፣ አሰጋኽኝ ጴጥሮስ፣ አብዲ ዋበላ፣ ብሩክ እንዳለና ብርሀኑ አዳሙን ለማስፈረም የተስማሙት መቐለ 70 እንደርታዎች አሁን ደግሞ አማካዩ ፍፁም ዓለሙን ለማስፈረም ከጫፍ ደርሰዋል። በተጠናቀቀው ዓመት የጣና ሞገዶቹ ቆይታው በሰላሣ አራቱም ጨዋታዎች ተሳትፎ 2618′ ደቂቃዎች ቡድኑን በማገልገል አምስት ግቦች ያስቆጠረው አማካዩ አሁን ደግሞ ወደ ምዓም አናብስቱ ቤት ለማምራት ተስማምቷል።
ከዚህ ቀደም ለጥቁር አባይ፣ ደብረማርቆስ ዩኒቨርስቲ ፣ ፋሲል ከነማ እንዲሁም በሁለት አጋጣሚዎች በባህርዳር ከተማ መጫወት የቻለው አማካዩ የሕክምና ምርመራውን አጠናቆ ወደ መቐለ 70 እንደርታ ለማምራት መስማማቱን ተከትሎ በክረምቱ የዝውውር መስኮት ክለቡን ለመቀላቀል የተስማማ ሰባተኛ ተጫዋች ሆኗል።