ቢጫዎቹ ተከላካይ አማካዩን አስፈርመዋል

ቢጫዎቹ ተከላካይ አማካዩን አስፈርመዋል

ቀደም ብሎ መቐለ 70 እንደርታን ለመቀላቀል ተስማምቶ የነበረው ተጫዋች ወደ ወልዋሎ አምርቷል።

በአሰልጣኝ ግርማ ታደሰ መሪነት ለ2018 የውድድር ዓመት ቡድናቸውን ለማጠናከር በእንቅስቃሴ ላይ ያሉትና ቀደም ብለው ፍሬው ሰለሞን፣ በየነ ባንጃው፣ ኢብራሂም መሐመድ፣ ሰመረ ሃፍታይ፣ ጌትነት ተስፋዬ ፣ ፍቃዱ መኮንን፣ ነፃነት ገብረመድህን፣ ሙሉዓለም መስፍን እና ኮንኮኒ ሀፊዝን ለማስፈረም ተስማምተው  የሰባት ነባር ተጫዋቾች ውል ያራዘሙት ወልዋሎዎች አሁን ደግሞ ባለፉት ዓመታት በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ቆይታ የነበረው እና ከሳምንታት በፊት መቐለ 70 እንደርታን ለመቀላቀል ተስማምቶ የነበረውን አማካዩ ብሩክ እንዳለን ለማስፈረም ተስማምተዋል።

ከዚህ ቀደም በለገጣፎ ለገዳዲ፣ ገላን ከተማ፣ እንዲሁም ከ2015 ጀምሮ በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ  ቆይታ የነበረውና ሀምራዊ ለባሾቹ ወደ ፕሪምየር ሊጉ ሲያድጉም ሆነ የሊጉ ሻምፕዮን ሲሆኑ ጉልህ ድርሻ ከነበራቸው ተጫዋቾች የሚጠቀሰው ተጫዋቹ በተጠናቀቀው የውድድር ዓመት በ28 ጨዋታዎች ተሳትፎ 2346′ ደቂቃዎች ቡድኑን ማገልገሉ የሚታወስ ሲሆን አሁን ደግሞ ወደ ቢጫዎች ለማምራት ፊርማውን አኑሯል።