👉 አዲስ አበባ ስታዲየም ዳግም ወደ ሊጉ ውድድር ይመለሳል
👉 የተመዘገቡ ደጋፊዎች ብቻ ወደ ስታዲየም እንዲገቡ ይደረጋል
👉 የደህንነት ካሜራዎች በስታዲየም ውስጥ ይኖራሉ
የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ በአክስዮን ማህበሩ መመራት ከጀመረ ወዲህ የሊጉ ውድድር በተመረጡ ሜዳዎች ክለቦች በአንድ ከተማ በመሰባሰብ ያለፉትን አምስት ዓመታት ውድድሮች ሲካሄዱ መቆየታቸው ይታወቃል።
ከዚህ ቀደም በአዲስ አበባ ፣ በባህር ዳር ፣ በሀዋሳ ፣ በአዳማ እና በድሬደዋ ስታዲየም ጨዋታዎች ሲደረጉ ሰንብተዋል። ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በተለያዩ ምክንያቶች በሁለቱ ከተሞች በአዲስ አበባ እና በባህር ዳር ከተማ ውድድሮች ሳይደረጉባቸው እንደቀረም የሚታወሳል። አሁን የ2018 የውድድር ዘመን በአራት የተመረጡ ስታዲየሞች ለመደረግ መታቀዱን የሊጉ አክስዮን ማህበር ፕሬዝደንት መቶ አለቃ ፍቃደ ማሞ ዛሬ በኃይሌ ግራንድ ሆቴል በነበረው የውይይት መድረክ ላይ ተናግረዋል።
በዚህም መሠረት አስቀድመው ያለፉትን ሁለት ዓመታት ውድድሮች ሲካሄድባቸው የቆዩት አዳማ ከተማ ፣ ሀዋሳ ከተማ እና ድሬደዋ ከተማ አሁንም ባሉበት የሚቀጥሉ ሲሆን ከአራት ዓመት በኋላ አዲስ አበባ ስታዲየም የሊጉን ውድድር ለማዘጋጀት የተመረጠ አራተኛ ከተማ መሆኑ እርግጥ ሆኗል።
አሁን የሚጠበቀው የሊጉ አክስዮን ማህበር የቦርድ አባላት ውድድሩ በምን ቅርፅ(ፎርማት) ይካሄድ የሚለውን ውይይት አድርገው በቀሩት ቀናቶች የሚወስኑ ይሆናል። እንዳገኘነው መረጃ ከሆነ ውድድሩ በሦስት አማራጮች ሊካሄድ እንደሚችል ነው።
አንደኛ እንደከዚህ ቀደሙ በተመረጡት ስታዲየሞች ክለቦች በአንድ ቦታ ተሰባስበው ውድድራቸውን የሚያደርጉበት ሲሆን ሁለተኛ ደግሞ ሁሉም (20 ክለቦችን) አንድ ቦታ ቢሆኑ ከሚኖረው የልምምድ ሜዳ ዕጥረት አኳያ ሁሉንም በአንድ ቦታ ማድረግ አስቸጋሪ ስለሚሆን በሁለት ተከፍለው በድልድላቸው መሠረት በተመረጠው ከተማ እንዲጫወቱ ማድረግ የሚል ነው። ሦስተኛው አማራጭ በዞን ከፋፍሎ ውድድሩን ማስኬድ የሚለው ነው። ከላይ ከጠቀስናቸው አማራጭ ውጭ የውድድሩ ፎረማት በሜዳው እና ከሜዳው ውጭ (Home and Away) ቅርፅ ሊኖር እንደማይችል ሰምተናል። የሊጉ ውድድር ጥቅምት ስምንት ቀን ለመጀመር ከመታሰቡ አስቀድሞ ሁሉም ነገር እንደሚታወቅ ይጠበቃል።
ከአዲስ አበባ ስታዲየም ጋር ተያይዞ ሊጉ ወደ መዲናው መመለሱ ለብዙዎች መልካም ዜና ሲሆን የተለያዩ ቅድመ ሁኔታዎች ግን እየተሰራባቸው እንደሆነ አውቀናል። ከእነዚህም ውስጥ ምዝገባ እየተከናወነ የተለዩ ደጋፊዎች ብቻ እንደሚገቡና በስታዲየሙ ውስጥ የደህንነት ካሜራዎች እንደሚኖር ተመላክቷል።
የባህር ዳር ዓለም አቀፍ ስታዲየምን በተመለከተ በቀጣይ የግንባታው ሂደት ሲጠናቀቅ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመነጋገር በአምስተኛ ከተማነት የመያዝ ዕድሎች እንደሚኖር ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።