ከጥቂት ቀናት በፊት አዳማ ከተማ ለመቀላቀል ተስማምቶ ከቡድኑ ጋር የቅድመ ውድድር ዝግጅት ይጀምራል ተብሎ ሲጠበቅ የነበረው አማካይ ወደ ቀድሞ ክለቡ ተመለሰ።
ያለፉትን ሁለት የውድድር ዓመታት በሲዳማ ቡና ቆይታ ካደረገ በኋላ ከቡድኑ ጋር ያለው ውል መጠናቀቁን ተከትሎ ወደ አዳማ ለማምራት ተስማምቶ የነበረው ፍቅረየሱስ ተወልደብርሀን ከአዳማ ከተማ ጋር የቅድመ ውድድር ዝግጅት ይጀምራል ተብሎ ሲጠበቅ የነበረ ቢሆንም በስተመጨረሻ ከሲዳማ ቡና ጋር ለተጨማሪ አንድ ዓመት ለመቆየት ከስምምነት ደርሷል።
ያለፉትን ሁለት ቀናት ወደ ሲዳማ ቡና ስብስብ ተቀላቅሎ ልምምድ የጀመረው አማካዩ በተጠናቀቀው የውድድር ዓመት በ30 ጨዋታዎች ተሳትፎ 2253′ ደቂቃዎችን ቡድኑን በማገልገል በፕሪምየር ሊጉ 4 ግቦች በማስቆጠር እንዲሁም ቡድኑ በኢትዮጵያ ዋንጫ እስከ ፍፃሜው እንዲጓዝ ጉልህ አስተዋጾ ማበርከቱ የሚታወስ ነው። በተጠናቀቀው የውድድር ዓመት ጥሩ እንቅስቃሴ ያደረገው አማካዩ ከዚህ በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ፣ ሀዋሳ ከተማ፣ ኢትዮጵያ ቡና፣ ሀድያ ሆሳዕና እንዲሁም ያለፉትን ሁለት የውድድር ዓመታት በሲድማ ቡና ቆይታ ማድረጉም ይታወሳል።