👉” ከመሄዴ በፊት ባለፈው ገልጫለው መደጋገም እንዳይሆን”
👉”ለወጣቶች ዕድል መስጠት ያስፈልጋል”
👉 “ሌሎች ሀገሮች ተጠቃሚ የሆኑት በዚህ ነው” አሰልጣኝ መሳይ ተፈሪ
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በ2026 የዓለም ዋንጫ ማጣርያ ከጊኒ ቢሳው እና ቡርኪና ፋሶ ጋር ጨዋታዎች በማድረግ በውድድሩ የነበረውን ተሳትፎ ከግርጌው የጅቡቲን ቡድን በደረጃ ብቻ በልጦ ማገባደዱ ይታወሳል። በእነዚህ ሁለት ጨዋታዎች የነበረውን ቆይታ አስመልክቶ በአሁን ሰዓት በኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የመሰብሰብያ አዳራሽ የዋልያዎቹ አለቃ አሰልጣኝ መሳይ ተፈሪ ጋዜጣዊ መግለጫ እየሰጡ ይገኛል። ከቀረበላቸው ጥያቄ መካል የዋልያዎቹ አለቃ አሰልጣኝ መሳይ ተፈሪ ከተመዘገበው ውጤቱ ደካማነት አንፃር ራስህን ከአሰልጣኝነት ታሰናብታለህ ተብለው ለተጠየቁት ጥያቄ ምላሽ ሲሰጡ
“ከመሄዴ በፊት ባለፈው ገልጫለው መደጋገም እንዳይሆን ተናገሬያለው ፤ በዚህ ጉዳይ ምላሽ የለኝም” በማለት ጥያቄውን በአጭሩ ሲያልፉት ከሩዋንዳ ጋር በነበረው ጨዋታ ከመጫወቻ ሜዳው ፣ የተወሰኑ ኢትዮጵያውያን ደጋፊዎች መኖራቸው፣ የጉዞው ሁኔታ አጭር መሆኑ እና የጨዋታው ሰዓት ጥሩ መሆኑን ገልፀው በመቀጠል አፅዕኖት የሰጡት ተከታዩን ጉዳይ እንደሚከተለው ብለዋል።
“አሰቸጋሪ ጊዜ ነው ጨዋታዎችን ያደረግነው ይህን ከግንዛቤ ማስገባት ያስፈልጋል ከአስርሩ ጨዋታዎች አምስቱን በሜዳችን ማድረግ የነበረብን ጨዋታ ነው። ይህን ሜዳችን ላይ ብናደርግ ኖሮ ከነበረን ነጥብ የበለጠ የመሰብሰብ ዕድሎች ነበሩ። በድልም በሽንፈትም የተማርናቸው ነገሮች አሉ ይህን ለቀጣይ መውሰድ ያስፈልጋል” ያሉት አሰልጣኙ ለአዳዲስ፣ ለወጣት ተጫዋቾች የተሰጠው ዕድል ጥሩ መሆኑን እና አራት ተጫዋቾች ለነገ ብሔራዊ ቡድን መጥቀም የሚችሉ ልጆች መገኛታቸው ገልፀው በቀጣይነትም ለወጣቶች ዕድል መስጠቱ መቀጠል አለበት ብለዋል።
ከጨዋታ መንገድ ጋር በተያያዘ ስለሚከተሉት ሀሳብ ሲያወሩ “ተጭኖ መጫወትን ስፔን፣ ማንችስተር ሲቲ ጋር ይተገብሩታል። እነርሱ በተወሰነ መልኩ ከእኛ ጋር የሚያመሳስላቸው ነገር አላቸው። ይሄን እነርሱ ያደረጉት ካላቸው ነገር ተነስተው ነው። እኛም በተደራጀ መልኩ ብናደርገው ያዋጣናል። በተለይ መከላከሉም በማጥቃቱም ተጭኖ መጫወት ላይ በደንብ አተኩረን ብንሰራ ያዋጣናል ብዬ አስባለው” ብለዋል።
ትውልደ ኢትዮጵያውያን በመጠቀም ዙርያ ሲናገሩ “ሌሎች ሀገሮች ተጠቃሚ የሆኑት በዚህ ነው። አብዛኛው ወደ ዓለም ዋንጫ ያለፉ ሀገራት ከአውሮፓ እያመጡ ነው። ስለዚህ በዚህ ጉዳይ ሂደት ላይ እንደሆነ አውቃለ እኔ ይህ ጉዳይ የበለጠ ተገፍቶበት መሄድ አለበት”።