ኤሌክትሪክ ዓመቱን በድል ሲጀምር ነገሌ አርሲ ከ አርባምንጭ ነጥብ ተጋርተዋል

ኤሌክትሪክ ዓመቱን በድል ሲጀምር ነገሌ አርሲ ከ አርባምንጭ ነጥብ ተጋርተዋል

የ2018 የውድድር ዘመን ሲቢኢ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ዛሬ በአዲስ አበባ እና ሀዋሳ ላይ ሲጀመር በአዲስ አበባ ስታዲየም በተደረጉ የመክፈቻ ጨዋታዎች ኢትዮ ኤሌክትሪክ ዓመቱን በድል ጀምሯል። ነገሌ አርሲ እና አርባ ምንጭ ከተማ ደግሞ ነጥብ ተጋርተዋል።

ኢትዮ ኤሌክትሪክ 1-0 ሸገር ከተማ

በቅርቡ ከዚህ ዓለም በሞት ለተለየው ፌደራል ዳኛ ደረጄ አመራ በተደረገው የህሊና ፀሎት የጀመረው የ2018 ሲቢኢ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የመክፈቻ ጨዋታ በመጀመርያው አጋማሽ ላይ ጥቂት የግብ ዕድሎች የተፈጠሩበትና አመርቂ የማጥቃት እንቅስቃሴ ያልተደረገበት ነበር። በአጋማሽ ጥሩ አጀማመር የነበራቸው ሸገር ከተማዎች በአሚር አብዶ ያደረጓት ሙከራ የአጋማሹ ለግብ የቀረበች ሙከራ ስትሆን በሂደት ያገገሙት ኤሌክትሪኮችም በበረከት ወልደ ዮሐንስ የግንባር ሙከራ እና የእዮብ ገብረማርያም የርቀት ሙከራ ግብ ለማስቆጠር ጥረት አድርገዋል።

የተሻለ የማጥቃት ፍላጎት በታየበት ሁለተኛው አጋማሽ ሸገር ከተማዎች በሁለት አጋጣሚዎች በአንተነህ ተፈራ አማካኝነት ግብ ለማስቆጠር ጥረት ብያደርጉም ግብ በማስቆጠር ቀዳሚ የሆኑት ግን ኢትዮ ኤሌክትሪኮች ሆነዋል። በ54′ ደቂቃ ላይ አብነት ተስፋዬ ምንተስኖት የግሌ የሰራው ስህተት ተጠቅሞ ከመረብ ያዋሀዳት ኳስም ኤሌክትሪክን መሪ ማድረግ ችላለች። ኤሌክትሪኮች በቢንያም በቀለ፣ አብነት ተስፋዬ እንዲሁም እዮብ ገብረማርያም አማካኝነት ሙከራዎች ማድረግ ቢችሉም ሦስቱም ሙከራዎች በምንተስኖት የግሌ ተመልሰዋል። ሸገር ከተማዎችም በቡልቻ ሹራ አማካኝነት ለግብ የቀረቡ ሁለት ሙከራዎች ማድረግ ቢችሉም ግብ ማስቆጠር ባለመቻላቸው በሊጉ መክፈቻ ጨዋታ ኢትዮ ኤሌክትሪክ ባለ ድል ሆኗል።

ነገሌ አርሲ 1-1 አርባ ምንጭ ከተማ

በዚህ ሳምንት ከዚህ ዓለም በሞት ለተለየው ፌደራል ዳኛ ደረጄ አመራ በተደረገው የህሊና ፀሎት የጀመረው የዕለቱ ሁለተኛ ጨዋታ ጥሩ እንቅስቃሴ የተደረገበት ነበር። ጥሩ ፉክክር በተደረገበት ጨዋታ ግብ የተቆጠረውም ገና በመጀመርያው ደቂቃ ነበር። ሐቢብ ከማል በራሱ ጥረት ተጫዋቾች አታሎ ያስቆጠረው ግብም አዲስ አዳጊዎችን መሪ ያደረገች ግብ ነበረች። ከግቧ መቆጠር በኋላ አዞዎቹ የተሻለ እንቅስቃሴ ማድረግ የቻሉ ሲሆን በኤፍሬም ታምራት ካደረጉት ሙከራ በኋላ በ32′ ደቂቃ ላይ ኤፍሬም ታምራት ከመስመር አሻግሯት ታምራት እያሱ በግንባር ባስቆጠራት ግብ አቻ መሆን ችለዋል።

የኃይል አጨዋወቶች በተስተዋለበት ሁለተኛው አጋማሽ ነገሌ አርሲዎች የተሻለ ተንቀሳቅሰው ሙከራዎችንም አድርገዋል። ሮንቦት ሶላሎ በግንባር ያደረጋት ሙከራ እንዲሁም በረከት ወልዴ ከቆመ ኳስ በቀጥታ ያደረጋት ኳስም ለግብነት የቀረቡ ነበሩ። በተጨማሪም በረከት ወልዴ ያመከናት ወርቃማ ዕድል ነገሌ አርሲዎችን መሪ ለማድረግ የምታስችል ሙከራ ነበረች።

በመገባደጃ ደቂቃዎች ብልጫ የወሰዱት አዞዎቹም በታምራት እያሱ መሪ የሚሆኑበትን ወርቃማ ዕድል አግኝተው የነበረ ቢሆንም ኢድሪሱ አብዱላሂ አድኖባቸዋል። በአጋማሹ የነገሌ አርሲው ተጫዋች ሀቢብ ከማል ከባድ ጉዳት አስተናግዶ ከሜዳ የወጣ ሲሆን ጨዋታውም ጥሩ ፉክክር ተደርጎበት በአቻ ውጤት ፍፃሜውን አግኝቷል።