በሀዋሳ የመክፈቻ ጨዋታዎች ሲዳማ ቡና እና ሀዋሳ ከተማ አሸንፈዋል

በሀዋሳ የመክፈቻ ጨዋታዎች ሲዳማ ቡና እና ሀዋሳ ከተማ አሸንፈዋል

የ2018 የውድድር ዘመን ሲቢኢ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም የመክፈቻ ቀን ጨዋታዎች ባለሜዳዎቹ ሲዳማ ቡና እና ሀዋሳ ከተማ አሸንፈዋል።

ወልዋሎ ዓ/ዩ 1-4 ሲዳማ ቡና

ቢጫዎቹ ብልጫ በወሰዱባቸው የመጀመሪያ ደቂቃዎች ተደጋጋሚ የማጥቃት እንቅስቃሴ ሲያደርጉ 21ኛ ደቂቃ ላይ ብሩክ እንዳለ በመስመር በኩል ይዞት ገብቶ ከግብ ጠባቂ ጋር ተገናኝቶ ሳይጠቀምበት የቀረው ኳስ ተጠቃሽ ነበር። ሆኖም በመጠኑ እየተቀዛቀዘ በሄደው ጨዋታ 36ኛ ደቂቃ ላይ ሰመረ ሀፍታይ ባስቆጠረው ጎል ወልዋሎዎች መሪ መሆን ችለዋል። ተጫዋቹ ከመስመር የተቀበለውን ኳስ ይዞ ገብቶ ነው በቀላሉ ማስቆጠር የቻለው።

ከዕረፍት መልስ እጅግ ተጠናክረው የገቡት ሲዳማ ቡናዎች ጌታሁን ባፋ ራሱ ላይ ባስቆጠረው ጎል አቻ መሆን ሲችሉ በክረምቱ የዝውውር መስኮት ከደብረብርሃን ሲዳማ ቡናን የተቀላቀለው ተመስገን መንገሻ 54ኛ ደቂቃ ላይ አሻምቶት ጌታሁን ባፋ ዕድለኛ ሳይሆን ቀርቶ ራሱ ላይ ያስቆጠረው ጎል በውድድር ዓመቱ የመጀመሪያ በራስ ላይ የተቆጠረ ጎል ሆኗል።

ቶሎ ቶሎ ወደ ተጋጣሚ ቡድን ሲደርሱ የነበሩት ሲዳማዎች 61ኛው ደቂቃ ላይ መሪ የሆኑበትን ጎል አግኝተዋል። ኳስ ከመስመር በኩል ይዞ የገባው አበባየሁ ሀጂሶ አጋጣሚውን በአግባቡ በመጠቀም ቡድኑን መሪ አድርጓል። ከጥቂት ደቂቃዎች በኋላ አስቻለው ሙሴ ከመስመር በኩል ይዞት ገብቶ የመታው ኳስ በወልዋሎ ተከላካዮች ተጨርፎ ሦስተኛ ጎል ሲሆን 71ኛ ደቂቃ ላይ ሲዳማዎች አራተኛ ጎል አስቆጥረዋል። ተመስገን በጅሮንድ ከመስመር በኩል ያሻገረውን ኳስ ተመስገን መንገሻ በግንባሩ በመግጨት ኳሱን መረብ ላይ አሳርፎታል። የጨዋታው መገባደጃ ደቂቃ ላይ ብሩክ እንዳለ በቀይ (በሁለት ቢጫ) ካርድ ከሜዳ ወጥቷል ፤ ጨዋታውም በሲዳማ ቡና 4-1 አሸናፊነት ተጠናቋል።


ድሬዳዋ ከተማ 0-2 ሀዋሳ ከተማ

በዕለቱ ሁለተኛ ጨዋታ ድሬዳዋ ከተማዎች በተሻለ የኳስ ቁጥጥር ጨዋታውን ቢጀምሩም ሀዋሳዎች የመጀመሪያውን ጎል አስቆጥረዋል። 10ኛው ደቂቃ ላይ ሐይቆቹ በጥሩ ቅብብል የወሰዱትን ኳስ ቸርነት አውሽ እየገፋ ወስዶ አስቆጥሮታል። ሆኖም ፈጣን ምላሽ ለመስጠት ከፍተኛ መነቃቃት ያሳዩት ብርቱካናማዎቹ ሳጥን ውስጥ በተሠራባቸው ጥፋት ፍጹም ቅጣት ምት ቢያገኙም መሐመድኑር ናስር የመታውን ኳስ ሰይድ ሀብታሙ አግዶበታል። ሐይቆቹ በአንጻሩ 25ኛ ደቂቃ ላይ ተጨማሪ ግብ ለማስቆጠር እጅግ ተቃርበው አብነት ደምሴ ያደረገውን ሙከራ ግብ ጠባቂው ፍሬው ጌታሁን እንደምንም አስወጥቶበታል።

ከዕረፍት መልስ በተሻለ የራስ መተማመን የተመለሱት ሀዋሳዎች 57ኛ ደቂቃ ላይ መሪነታቸውን በጌታነህ ከበደ አማካኝነት አጠናክረዋል። አጥቂው ከመሃል የተሰጠነቀለትን ኳስ ተቀብሎ ነው ኳሱን መረቡ ላይ ያሳረፈው።

ድሬዳዋ ከተማዎች በተደጋጋሚ ሳጥን ውስጥ መግባት ቢችሉም ያለቀለት የግብ ዕድል ለመፍጠር ተቸግረው ጨዋታውም በሀዋሳ ከተማ 2-0 አሸናፊነት ተጠናቋል።