በሲቢኢ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም የሁለተኛ ቀን ጨዋታዎች ዐፄዎቹ እና ሀምራዊ ለባሾቹ ነጥብ ሲጋሩ ጦሩ በኢሞሮ መናፍ አስደናቂ የመጨረሻ ደቂቃ ግብ ጣፋጭ ድል ተጎናፅፏል።
ፋሲል ከነማ ከ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ
ኃይል የቀላቀሉ አጨዋወቶች የተስተዋለበት የዕለቱ ቀዳሚ ጨዋታ ጥቂት ሙከራዎች የተደረጉበት ነበር። በ9ኛው ደቂቃም በረከት ግዛው ከሳጥኑ የቀኝ ጠርዝ አክርሮ በመምታት ዐፄዎቹን መሪ ማድረግ ችሏል። ሆኖም መሪነታቸው የቀጠለው ለሦስት ደቂቃዎች ነበር፤ በ12ኛው ደቂቃም አዲስ ግደይ ከመዓዝን ያሻገራትን ኳስ ዘላለም አበበ በግንባር በማስቆጠር ንግድ ባንኮችን አቻ ማድረግ ችሏል። አጋማሹ ሊገባደድ ደቂቃዎች ሲቀሩትም ዘላለም አባተ ከከባድ ጉዳት በማስተናገዱ ተቀይሮ ወጥቷል።

ዐፄዎቹ በአንፃራዊነት የተሻሉ ሙከራዎች ባደረጉበት ሁለተኛው አጋማሽ ላይ ቃልኪዳን ዘላለም በመልሶ ማጥቃት አፈትልኮ ግብ ጠባቂው አልፎ መቷት ካሌብ አማንካዋህ ከመስመር የመለሳት ወርቃማ ዕድልም ዐፄዎቹን መሪ ለማድረግ የተቃረበች ዕድል ስትሆን ያሬድ ብርሀኑ በግንባር ያደረጋት ሙከራም ተጠቃሽ ናት። በሀምራዊ ለባሾቹ በኩልም መስፍን ዋሼ በሁለት አጋጣሚዎች ያደረጋቸው ሙከራዎች ይጠቀሳሉ፤ በተለይም ከሳጥኑ ጠርዝ አክርሮ መቷት ለጥቂት ወደ ውጭ የወጣችው የተሻለ ለግብ የቀረበች ነበረች። ሀይል በቀላቀሉ አጨዋወቶች ታጅቦ የተካሄደው ጨዋታም በአቻ ውጤት ፍፃሜውን አግኝቷል።
መቻል 1-0 ወላይታ ድቻ
ጦሩ ከ ጦና ንቦች ያገናኘው የዕለቱ ሁለተኛ ጨዋታ ጥሩ ፉክክር የተደረገበት ቢሆንም በሙከራዎች የታጀበ አልነበረም። በመጀመርያው አጋማሽ በረዣዥም ኳሶች ዕድሎች ለመፍጠር ጥረት ባደረጉት ወላይታ ድቻዎች በኩል አዛርያስ አቤል ከመዓዝን ምት የተሻማችን ኳስ ተጠቅሞ በግንባሩ ያደረጋት ሙከራ እንዲሁም የተሻለ የኳስ ቁጥጥር በነበራቸው መቻሎች በኩል ብሩክ ማርቆስ በሁለት አጋጣሚዎች ያደረጋቸው ሙከራዎች ይጠቀሳሉ፤ በተለይም አማካዩ አክርሮ መቷት ግብ ጠባቂው ወደ ውጭ ያወጣት ሙከራ ለግብ የቀረበች ነበረች።

ሁለተኛው አጋማሽ በሁሉም ረገድ የመቻሎች ብልጫ የታየበት ሲሆን በረከት ደስታ እና ብሩክ ማርቆስ ከርቀት ባደረጉት ሙከራ እንዲሁም ቸርነት ጉግሳ ባልተጠቀመባት ወርቃማ ዕድል መሪ መሆን የሚችሉበት ዕድል አግኝተው ነበር። በአጋማሹ በአመዛኙ መከላከል ላይ ተጠምደው ያመሹት የጦና ንቦችም ቴዎድሮስ ታፈሰ አክርሮ መቷት አልዮንዜ ናፍያን ወደ ውጭ ባወጣት ሙከራ ግብ ለማግኘት ጥረት አድርገዋል። መደበኛ ደቂቃ ተጠናቆ በተሰጠው ተጨማሪ ደቂቃ ላይ ግን ኢሞሮ መናፍ ከሳጥን ውጭ ማራኪ ግብ አስቆጥሮ የማታ ማታ ጦሩን ባለ ድል አድርጓል።



