ቅድመ ጨዋታ መረጃዎች| የሁለተኛው ሳምንት የመጨረሻ ቀን ጨዋታ

ቅድመ ጨዋታ መረጃዎች| የሁለተኛው ሳምንት የመጨረሻ ቀን ጨዋታ

በሁለተኛው የጨዋታ ሳምንት መጠናቀቂያ ቀን ላይ ሲዳማ ቡና ከ ሀዋሳ ከተማ የሚያገናኘውን ሮድዋ ደርቢን የተመለከቱ መረጃዎች

ሁለት ከድል መልስ የሚገናኙ ክለቦች የሚያገናኘው ጨዋታው በብዙዎች ዘንድ እጅግ ተጠባቂ ነው።
መቀመጫቸውን ሀዋሳ ላይ ያደረጉት ሁለቱም ቡድኖች በዛሬው ጨዋታ የደርቢው የበላይ ለመሆን እንደ ወትሮው በብዙ ደጋፊዎቻቸው ታጅበው ተጠባቂውን ፍልሚያ ያከናውናሉ።

ከወልዋሎ ጋር ባደረጉት የመጀመርያው ሳምንት ጨዋታ ከመመራት ተነስተው አራት ጎል በማስቆጠር ድል ያደረጉት ሲዳማ ቡናዎች በጨዋታው የነበራቸው የማጥቃት አጨዋወት ዋነኛ ጠንካራው ጎናቸው ነበር። በዛሬው ጨዋታም የሲዳማ ቡና የፊት መስመር ተጫዋቾች ለተጋጣሚያቸው ተከላካዮች ፈተና መሆናቸው አይቀሪ ይመስላል።

በአንደኛ ሳምንት የሲቢኢ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ወላይታ ድቻን በመርታት የውድድር ዓመቱን በድል መጀመር የቻሉት ሀዋሳ ከተማዎች እንደ ተጋጣሚያቸው ሁሉ የአሸናፊነት መንገዳቸውን ለማስቀጠል ወደ ሜዳ ይገባሉ። ሀይቆቹ በመከላከሉ ረገድ ጠንከር ያለ ፈተና ይጠብቃቸዋል ተብሎ የሚገመት ሲሆን በመጀመርያው ጨዋታ ተስፋ ሰጪ እንቅስቃሴ ያደረገው የቡድኑ የፊት ጥምረትም ቀላል ግምት አይሰጠውም። ከዚህ በተጨማሪ ቡድኑ የአጥቂው ኢስራኤል እሸቱ ግልጋሎት ማግኘቱም የፊት መስመሩ ይበልጥ ያጠናክርለታል።

ሁለቱ ክለቦች ከዚህ ቀደም በ30 ጨዋታዎች ተገናኝተው ሁለቱም 10 ጨዋታዎች በእኩሌታ ስያሸነፉ  ቀሪዎቹ 10 ጨዋታዎች በአቻ ውጤት ተጠናቀዋል። በጨዋታዎቹ በድምሩ 63 ኳሶች መረብ ላይ ሲያርፉ ሲዳማ 33 ሀዋሳ ደግሞ 30 ጎሎች አስቆጥረዋል።