የኢትዮጵያ መድን ተጋጣሚ ማነው ?

የኢትዮጵያ መድን ተጋጣሚ ማነው ?

በቶታል ኢነርጂስ ካፍ ቻምፒየንስ ሊግ ኢትዮጵያ መድን የሚገጥመው የአል-ቃሄራ አል-ገዲዳው ክለብ ማነው ?

በ2017 ውድድር ዓመት በታሪኩ ለመጀመርያ ጊዜ
የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግን በማሸነፍ በታላቁ አህጉራዊ ውድድር ለመሳተፍ የበቃው እና በመጀመርያው የማጣርያ ጨዋታ የዛንዚባሩ ምላንዴግን በድምር ውጤት አራት ለሦስት ያሸነፈው ኢትዮጵያ መድን በነገው ዕለት የግብፁ ፒራሚድን ይገጥማል።

ፒራሚድ እግር ኳስ ክለብ ማነው ?

በግሪጎርያን አቆጣጠር በ2008 ከግብፅ ጥንታዊ ከተሞች አንዷ በሆነችው አስዩት ከተማ፤ አል አስዩቲ በሚል ስያሜ የተቋቋመው እና በ2018 የ’Saudi Sports Authority’ ሊቀ መንበር በነበሩት ቱርኪ ቢን አብዱል ሞህሰን አል ሼክ ከተገዛ በኋላ ስሙን ወደ ፒራሚድ የቀየረው ክለቡ በአሁኑ ወቅት በምድረ አፍሪካ ሀብታም ከሚባሉ ክለቦች በቀዳሚነት ይጠቀሳል። በ2018 ከተመሰረተበት አስዩት ከተማ በመዲናይቱ ካይሮ ምስራቃዊ ክፍል ወደ ምትገኘው የአል-ቃሄራ አል-ገዲዳ ሜትሮፖሊታን ከተማ የተዘዋወረውና እንደ አዲስ ከተዋቀረ ሰባት ዓመታትን ያስቆጠረው ክለቡ በኤሚራቱ ባለ ፀጋ ነጋዴ ሳሌም አል ሻምሲ የሚተዳደር ሲሆን ፈርጣማው ገንዘባዊ አቅሙም ከአንጋፎቹ ግብፅ ክለቦችን በላይ አድርጎታል።

የአህጉራዊ ውድድር ስኬት ?

ፒራሚዶች በ2019/20 የመጀመርያው የአህጉራዊ ውድድር ተሳትፎ አድርገዋል። በውድድር ዓመቱ በካፍ ኮንፌዴሬሽን ዋንጫ ተሳትፎ የነበረው ቡድኑ እስከ ፍፃሜ ድረስ ተጉዞም በራባት በተካሄደው የፍፃሜ ጨዋታ በሞሮኮው ክለብ ቤርካኔ ሽንፈት አስተናግደዋል። በ2024-25 ግን በታሪካቸው ለመጀመርያ ጊዜ የካፍ ቶታል ቻምፒዮንስ ሊግ ዋንጫ ማሸነፍ የቻሉ ሲሆን ከቀናት በፊትም የካፍ ሱፐር ካፕን ማሸነፍ ችለዋል።

የክለቡ አሰልጣኝ

የፒራሚድ አሰልጣኝ የክሮሺያ ዜግነት ያላቸው ዋና አሰልጣኝ ክሩኖስላቭ ጁርቺች ናቸው። ከዚህ ቀደም የሳውዲው አል ናስር፣ የሳውዲ ዓረብያ ብሔራዊ ቡድን እንዲሁም ዳይናሞ ዛግሬብን ያሰለጠኑት ክሮአቱ ከክለቡ ጋር የካፍ ሱፐር ካፕን ከማሸነፍ በዘለለ ክለቡን በብዙ ረገድ አሻሽለውታል።

የቡድኑ ወሳኝ ተጫዋች ?

በክለቡ ውስጥ ሙስጠፋ ፈትሒ፣ ረመዳን ሶብሒ እንዲሁም ኢብራሂም ብላቲ ቱሬ የመሳሰሉ ቁልፍ ተጫዋቾች ቢኖሩም ከሁሉም የላቀ አበርክቶ ያለው ጎንጓዊ የ31 ዓመት አጥቂ ፊስቶን ማዬሌ ግን የቡድኑ ወሳኝ ተጫዋች ነው። በፒራሚድ መለያ በሁሉም ውድድሮች ባደረጋቸው 95 ጨዋታዎች 48 ግቦች አስቆጥሮ 8 ግብ የሆኑ ኳሶች አመቻችቶ ያቀበለው ይህ ተጫዋች በወሳኝ ጨዋታዎች ያለው ጉልህ አበርክቶ የቡድኑ ቁልፍ ተጫዋች ያደርገዋል።

ክለቡ የሚጫወትበት ስቴድየም ?

የክለቡ ዋና ስቴድየም በካይሮ የሚገኘው የሀገሪቱ አየር ኃይል ያስገነባው 30,000 ደጋፊዎች የመያዝ አቅም ያለው 30 June Stadium ነው። የነገው የካፍ ቶታል ቻምፕዮንስ ሊግ ጨዋታ በስቴድየሙ የሚከናወን ይሆናል። ይህ ስታዲየም በ2023 ግብጽ ከ ኢትዮጵያ ያደረጉትን የአፍሪካ ዋንጫ ማጣርያ ማስተናገዱም ይታወሳል።