ኢትዮጵያዊ ተጫዋች በአህጉራዊ ውድድር ወሳኝ ግብ አስቆጥሯል
በኦማኑ ክለብ አል ሸባብ እየተጫወተ የሚገኘው የዋልያዎቹ የፊት መስመር ተጫዋች ከንአን ማርክነህ ለክለቡ ወሳኝ ግብ አስቆጥሯል። ዛሬ አል ሸባብ ከ ፓሮ ጋር ባደረጉት በኤስያ ሦስተኛው አህጉራዊ ውድድር በሆነው ኤስያ ቻሌንጅ ሊግ የመጀመርያ የምድብ ጨዋታ በሀያ ስድስተኛው ደቂቃ በፍፁም ቅጣት ምት ወሳኝ የማሸነፍያ ግብ ያስቆጠረው ተጫዋቹ ቡድኑ ምድቡን እንዲመራ አስችሏል።

ኢትዮጵያዊው አጥቂ ከንዓን ማርክነህ ባሳለፍነው ዓመት ከአል መዲና እና ሸባብ አልጋሀር ጋር በሊቢያ ፕሪምየር ሊግ ካደረገው መልካም ቆይታ በኋላ ዘንድሮም በኦማኑ ክለብ አል ሸባብ ጥሩ አጀማመር እያደረገ የሚገኝ ሲሆን በመጨረሻዎቹ ሁለት ጨዋታዎች ያስቆጠራቸው ሦስት ግቦች ጨምሮ በኦማኑ ክለብ መለያ ያስቆጠራቸው ግቦች አራት አድርሷል።



