በሲቢኢ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ አራተኛ ሳምንት በመጀመሪያ ቀን የሚደረጉ ጨዋታዎችን የተመለከቱ መረጃዎች እነሆ !
ኢትዮጵያ ቡና ከ ኢትዮ ኤሌክትሪክ
የሊጉን ዋንጫ ካነሱ ክለቦች መካከል የሆኑት ሁለቱ አንጋፋ ክለቦች ዛሬ 07፡00 ሲል ይፋለማሉ።
በሳምንቱ ተጠባቂ ጨዋታ ከባህር ዳር ከተማ ጋር 0-0 የተለያዩት ኢትዮጵያ ቡናዎች የውድድር ዓመቱን ሁለተኛ ድል ፍለጋ በጥሩ ወቅታዊ ላይ ከሚገኘው ኤሌክትሪክ ጋር ከፍተኛ ፉክክር ይጠብቃቸዋል። ቡድኑ የግብ ዕድሎችን የመፍጠር ብቃቱን እያሻሻለ ቢመጣም ከአጨራረስ ጋር ተያይዞ ባለፈው ጨዋታ ላይ የታዩ ክፍተቶችን ግን አርመው መቅረብ ይኖርባቸዋል።
ከመመራት ተነስተው አርባምንጭ ከተማን 3ለ1 አሸንፈው በጥሩ መነቃቃት ላይ የሚገኙት ኢትዮ ኤሌክትሪኮች ከከተማ ተቀናቃኛቸው ጋር ብርቱ ፍልሚያ ይጠብቃቸዋል። ካለፉት ሦስት ጨዋታዎች 7 ነጥቦችን መሰብሰብ የቻለው በአሰልጣኝ ዘሪሁን የሚመራው ቡድን ለዚህ ጨዋታ የሚሰጠው ግምት ከፍተኛ ሲሆን ድል መቀዳጀት የሚሰጠውን በራስ መተማመን እያሰበ ወደ ሜዳ ይገባል።
ሁለቱ ቡድኖች በሊጉ ለ44 ጊዜያት ተገናኝተው ቡና 24 በማሸነፍ ከፍተኛ የበላይነት ይዟል። 10 ጨዋታ ኤሌክትሪክ ሲያሸንፍ 10 ጊዜ አቻ ተለያይተዋል። ቡና 74 ሲያስቆጥር ኤሌክትሪክ 45 አስቆጥሯል።
በበርካታ ደጋፊዎች ታጅቦ በሁለት ከሽንፈት የተመለሱ ቡድኖች መካከል የሚደረገው ፍልሚያ በብዙዎች ዘንድ በጉጉት የሚጠበቅ ነው።
ተከታታይ ሁለት ድል አሳክተው በደረጃ ሰንጠረዡ አናት ላይ የነበሩት ሲዳማ ቡናዎች ባለፈው ሳምንት በፋሲል ከነማ 1ለ0 ተሸንፈዋል። በዚሁ ጨዋታ ላይ ከኋላ መስመር ቅብብል ላይ በሠሩት ስህተት ጎል ያስተናገዱ ቢሆንም ከዛ በኋላ የፈጠሯቸውን የግብ ዕድሎች ግን በአግባቡ የመጠቀም ችግር ተስተውሎባቸዋል። ሆኖም የዛሬ ተጋጣሚያቸው ካለበት የውጤት ማጣት ቀውስ ውስጥ ለመውጣት እያለመ የሚገባ መሆኑ ጨዋታውን ከባድ ያደርግባቸዋል።
ተከታታይ ሦስት ጨዋታዎችን የተሸነፉት ወላይታ ድቻዎች የውድድሩን የመጀመሪያ ነጥብ ፍለጋ አራተኛ ጨዋታቸው ላይ ተገኝተዋል። በአሰልጣኝ ገብረክርስቶስ ቢራራ የሚመራው ቡድን ባለፈው ሳምንት ሀዋሳ ከተማን እየመራ 2ለ1 መሸነፉ ይበልጥ ጫናውን ከፍ አድርጎበታል። ሆኖም ከዚህ ስሜት ለመውጣት ነጥብ ያስፈልጋቸዋል እና በዛሬው ጨዋታ የሞት ሽረት ትግል ያደርጋሉ ተብሎ ይጠበቃል።
ሁለቱ ቡድኖች በሊጉ እስካሁን 22 ጊዜ ተገናኝተው ወላይታ ድቻ 2 ጨዋታ ሲያሸንፍ 8 ጨዋታዎች አቻ ተለያይተው ሲዳማ ቡና 12 ጊዜ አሸንፏል። በሁለቱ ግንኙነት እስካሁን 33 ጎሎች ሲቆጠሩ ወላይታ ድቻ 11 ፣ ሲዳማ ቡና 25 ጎሎች ማስቆጠር ችለዋል።
ነገሌ አርሲ ከ ባህር ዳር ከተማ
ከሽንፈት እና አቻ መልስ የተቀመጡ ቡድኖችን የሚያገናኘው ጨዋታ 10፡00 ሲል ይደረጋል።
ከተጋጣሚያቸው በላይ ራሳቸው የሚሠሯቸው ስህተቶች ፈታኝ የሆኑባቸው ሰጎኖቹ በእንቅስቃሴያቸው እየተጠናከሩ ቢመጡም በተከታታይ ጨዋታዎች በተከላካዮች ስህተት ጎል እያስተናገዱ ተሸንፈዋል። ባለፈው ሳምንት ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር ባደረጉት ጨዋታ ጫናውን ተቋቁመው አንድ ነጥብ ለማሳካት ተቃርበው የኋላ ኋላ እጅ ሰጥተው መሸነፋቸው በሦስቱ ጨዋታዎች አንድ ነጥብ ብቻ እንዲይዙ አድርጓል።

በተከታታይ ዓመታት ሲታይባቸው የነበረውን የወጥነት ችግር ዘንድሮም ሊደግሙት ዳር ዳር እያሉ የሚመስሉት ባህር ዳር ከተማዎች እንደ ጠንካራ እና የተደራጀ ጨዋታቸው ሁሉ አልፎ አልፎ የሚታይባቸው መዘናጋት ከዋንጫ እያራቃቸው ቆይቷል። ቡድኑ በዘንድሮው የውድድር ዓመትም ሀዲያን አሸንፎ ጥሩ ጅማሮ ቢያደርግም በተፈተነባቸው የአርባምንጭ እና የኢትዮጵያ ቡና ጨዋታዎች አንድ ነጥብ ተጋርቶ ወጥቷል። ሆኖም አሰልጣኝ ደግአረገ የውድድር ዓመቱን ሁለተኛ ድል ለማሳካት በተለይም በማጥቃት እንቅስቃሴያቸው ላይ ማሻሻያ ያደርጋሉ ተብሎ ይጠበቃል።
ፋሲል ከነማ ከ ምድረገነት ሽረ
ባለፉት ሁለት ጨዋታዎቻቸው ጎል ያልተቆጠረባቸውን ቡድኖች የሚያገናኘው ጨዋታ የዕለቱ የመጨረሻ መርሐግብር ነው።
ከንግድ ባንክ ጋር አቻ ከተለያዩ በኋላ ወልዋሎ ዓ/ዩን እና ሲዳማ ቡናን ያሸነፉት ዐፄዎቹ በተለይም በውድድር ዓመቱ ያስቆጠሯቸው አራት ግቦች በአማካዮች መገኘታቸው የቡድኑ የማጥቃት አማራጭ ላይ ትልቅ አስተዋጽኦ አለው። ቡድኑ በተለይም በመከላከሉ ረገድ እያሳየው ያለው መሻሻል ትልቅ ትኩረት የሚሰጠው ሲሆን በሦስት ጨዋታም አንድ ጎል ብቻ ተቆጥሮበታል።
መቐለን አሸንፈው የውድድር ዓመቱን የጀመሩት ሽረዎች ቀጥለው ከወልዋሎ እና ንግድ ባንክ ጋር ባደረጓቸው ጨዋታዎች 0-0 ተለያይተው የመከላከል ጥንካሬያቸውን ቢያሳዩም በማጥቃት እንቅስቃሴው በኩል ግን ፈጣን መልስ ያስፈልጋቸዋል። ዛሬም በወቅታዊ ጥሩ ብቃት ላይ ከሚገኘው ፋሲል ጋር የሚያደርጉት ጨዋታ ላይ ብርቱ ፉክክር ማድረግ ይጠበቅባቸዋል።
የተሰረዘው የ2012 የውድድር ዓመት ጨዋታ ሳይጨምር በታሪካቸው አራት ጊዜ የተገናኙት ክለቦቹ ፋሲል ከነማ አንድ ጨዋታ ሲያሸንፍ ሦስት ጨዋታዎች በአቻ ውጤት ተጠናቀዋል። ፋሲል ከነማ አምስት ግቦች ሲያስቆጥር ስሑል ሽረ ሁለት ግቦች አስቆጥሯል።


