ኢትዮጵያ ንግድ ባንኮች የመጀመሪያ ሶስት ነጥባቸውን ሲያገኙ መቻሎች የሊጉ መሪ መሆን የቻሉበትን ድል አስመዝግበዋል።
ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከ ድሬዳዋ ከተማ

10:00 ሲል በሀዋሳ ስታዲየም በተደረገው ጨዋታ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክን ከ ድሬዳዋ ከተማ ጋር አገናኝቷል። ከጨዋታው ጅማሮ አንስቶ ወደ ግብ በመድረስ ረገድ ሁለቱም ቡድኖች ጥሩ የሚባል እንቅስቃሴን ያደረጉ ሲሆን 6ተኛው ደቂቃ ላይ የንግድ ባንኩ ተጫዋች የሆነው ብሩክ ብፁአምላክ ሳጥን ውስጥ የመታው ኳስ የግቡን ቋሚ ገጭቶ ወደ ውጭ ወጥቷል። በተመሳሳይ 21ኛው ደቂቃ ላይ ድሬዎች ሙከራ ማድረግ የቻሉ ሲሆን ያሬድ ታደሰ በረጅም ኳስ ያቀበለውን ኳስ አብዱልሰላም የሱፍ ከግብጠባቂው ጋር ቢገናኝም በፓላክ ቾል ጥረት ግብ ከመሆን ድኗል። የ27ኛው ደቂቃ ላይ በማይታመን መልኩ የግብ ዕድል ያመከነው ሳይመን ፒተር 43ኛው ደቂቃ ላይ በድንቅ ሁኔታ ከብሩክ ብፁአምላክ የተቀበለውን ኳስ ግብጠባቂውን በማለፍ ኳስን ከመረብ ጋር ማገናኘት ችሏል።

ከዕረፍት መልስ ሁለተኛው አጋማሽ ይበልጥ ራሳቸውን አሻሽለው የቀረቡት ኢትዮጵያ ንግድ ባንኮች 57ኛው ደቂቃ ላይ ከሳጥኑ ጠርዝ ላይ የተሰጠውን የቅጣት ምት ወደ ግብ ሞክሮ የግቡ አግዳሚ ገጭቶ የተመለሰበት ኳስ ለንግድ ባንኮች እጅጉን አስቆጪ ነበር። አሁንም ተጨማሪ ግብ ፍለጋ ጫና ፈጥረው መጫወት የቻሉት ለንግድ ባንኮች 77ኛው ደቂቃ ግብ አስቆጥረዋል። ሳይመን ፒተር ከሜዳው የቀኝ ክፍል ለማሻመት የሞከውን ኳስ ተቀይሮ የገባው የድሬዳዋው ተከላካይ ድልአዲስ ገብሬ በራሱ ላይ ግብ በማስቆር ኢትዮጵያ ንግድ ባንክን 2-0 እንዲያሸንፍ በማድረግ የመጀመሪያውን 3 ነጥብ ማሳካት ችሏል።
ወልዋሎ ዓ/ዩ ከ መቻል

የአራተኛ ሳምንት የመጨረሻ ሳምንት የመጨረሻ በነበረው ጨዋታ ወልዋሎ ዓ/ዩ ከ መቻል ጋር የተገናኙ ሲሆን ግብ በማግባቱ ረገድ መቻሎች ቀዳሚ በነበሩበት ጨዋታ ከተጀመረ 10 ያክል ደቂቃዎች በኋላ መነሻውን ከማዕዘን ምት ያደረገውን ኳስ ያገኘው ግሩም ሀጎስ ወደ ግብ የሞከረው ሲሆን ከግቡ በቅርብ ርቀት ላይ የነበረው መሐመድ አበራ በቄንጠኛ ምት ወደ ግብነት ቀይሮ ቡድኑን ገና በጨዋታው ጅማሮ መሪ ማድረግ ችሏል። ብልጫ ወስደው መጫወት የቻሉት መቻሎች በቆሙ ኳሶች የተካኑ መሆናቸውን ያስመሰከሩበትን ግብ 36ኛው ደቂቃ ላይ ማስቆጠር ችለዋል፤ በረከት ደስታ ከማዕዘን ምት የተገኘውን ኳስ መልሶ ያሻማው ሲሆን የተሻማውን ኳስ ብሩክ ማርቆስ በግንባሩ ገጭቶ ኳስ እና መረብን አገናኝቷል። ወልዋሎዎች 40ኛው ደቂቃ ላይ በእንዳልካቸው ጥበቡ አማካኝነት ለግብነት የቀረበ ሙከራ ቢያደርጉም በግብጠባቂው ጥረት ግብ ከመሆን ድኗል።

ከዕረፍት መልስ ሁለተኛው አጋማሽ ላይ ወልዋሎዎች ራሳቸውን አሻሽለው ወደ ሜዳ የተመለሱ ሲሆን በተደጋጋሚ ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል በመድረስ 66ኛው ደቂቃ ላይ ከሜዳው የቀኝ ክፍል ዳዊት ገብሩ ያሻማውን ኳስ ተቀይሮ የገባው ኮንኮኒ ሀፍዝ በግንባሩ ገጭቶ የሞከረውን ኳስ ለጥቂት የግቡን ቋሚ ታኮ ወጥቷል:: ቢጫ ለባሾቹ በአጋማሹ ጥሩ መንቀሳቀስ ቢችሉም ግብ ማስቆጠር ተስኗቸው 2-0 በሆነ ውጤት ሽንፈት አስተናግደዋል። ውጤቱንም ተከትሎ ጦሩ በ10 ነጥብ ሊጉን መምራት ጀምሯል።

