ቅድመ ጨዋታ መረጃዎች| የሲቢኢ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር የስድስተኛ ሳምንት ሁለተኛ ቀን ጨዋታዎች ዛሬም ቀጥለው ይካሄዳሉ

ቅድመ ጨዋታ መረጃዎች| የሲቢኢ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር የስድስተኛ ሳምንት ሁለተኛ ቀን ጨዋታዎች ዛሬም ቀጥለው ይካሄዳሉ

የሲቢኢ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የ6ኛው ሳምንት የሁለተኛ ቀን ጨዋታዎች የተመለከቱ መረጃዎች እነሆ!

ወልዋሎ ዓ/ዩ ከ ሀዋሳ ከተማ

በኢትዮጵያ ዋንጫ ምክንያት ለቀናት ተቋርጦ የቆየው የሲቢኢ ኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ጨዋታዎች ከቀናት ዕረፍት በኋላ የተመለሱ ሲሆን የስድስተኛ ሳምንት ሁለተኛ ቀን ጨዋታዎች ዛሬ ሲካሄዱ ቀን 7:00 ሲል ወልዋሎ ዓ/ዩን ከ ሀዋሳ ከተማ ያገናኛል። በአምስተኛው ሳምንት በድሬዳዋ ከተማ 2-1 የተሸነፉት ወልዋሎዎች የመጀመሪያ ሶስት ነጥባቸውን ለማሳካት ብርቱ ፉክክር ይጠብቃቸዋል። ባሳለፍነው የጨዋታ ሳምንት ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ጋር ነጥብ የተጋሩት ሀዋሳ ከተማዎች ወደ ቀድሞ አሸናፊነታቸው ለመመለስ ከ ወልዋሎ ጋር ይገናኛሉ።

ወልዋሎዎች በጉዳትም ሆነ በቅጣት የሚያጡት ተጫዋች የለም፤ በሀዋሳ ከተማ በኩል እስራኤል እሸቱ የዛሬው ጨምሮ ቀጣይ ጨዋታዎች በጉዳት ከሜዳ ይርቃል። እንዲሁም በኢትዮጵያ ዋንጫ ከጨዋታው መጠናቀቅ በኋላ በተፈጠረው የሰነ-ምግባር ግድፈት አራት ጨዋታዎችን የተቀጣው ሽመልስ በቀለ ከዛሬው ጨዋታ ውጭ ነው።

ሁለቱ ቡድኖች ስድስት ጊዜ ተገናኝተው በእኩሌታ
ሁለት ሁለት ጊዜ ሲሸናነፉ፣ በሁለት ጨዋታዎች አቻ ተለያይተዋል። በጨዋታዎቹ 8 ጎሎች ሲቆጠሩ ወልዋሎ 3፤ ሀዋሳ 5አስቆጥረዋል። (የተሰረዘው የ2012 ጨዋታ አልተካተተም)

ኢትዮጵያ ቡና ከ ኢትዮጵያ መድን

ሁለቱን ከሽንፈት የተመለሱ አንጋፋ ቡድኖች የሚያገናኘው ጨዋታ ከሳምንቱ ተጠባቂ መርሐግብሮች መካከል አንዱ ነው።

በሊጉ የመጨረሻ ሁለት መርሐግብሮች በኢትዮ ኤሌክትሪክ እና በአዳማ ከተማ ሽንፈት ያስተናገዱት ቡናማዎቹ ካለፉት ሦስት ጨዋታዎች ማሳካት የቻሉት ነጥብ አንድ ብቻ ነው። ቡድኑ በበርካታ ታዳጊ ተጫዋቾች እንደ መዋቀሩ ለውህደት መጠነኛ ጊዜ እንደሚያስፈልገው እሙን ቢሆንም ከነበረው ተጠባቂነት አንጻር ግን የፈጠረው ጫና እጅግ ከፍተኛ ነው። በእርግጥ ቡድኑ ለመጨረሻ ጊዜ ባደረገው የኢትዮጵያ ዋንጫ ሁለተኛ ዙር ጨዋታ አዳማ ከተማን ከመመራት ተነስቶ 2ለ1 መርታቱ የሚፈጥርለት መነሳሳት ቀላል የሚባል አይደለም። ባለፉት ሦስት የፕሪሚየር ሊግ ጨዋታዎች ምንም ጎል ላላስቆጠረው የአጥቂ መስመር ፈጣን መፍትሔ ለሚሹት አሰልጣኝ ዐቢይ ካሣሁን የናይጄሪያዊው አማካይ ዲቫይን ዋቹኩዋ ከጉዳት ማገገም እፎይታን እንደሚሰጣቸው ይጠበቃል።

እንደተጋጣሚያቸው ሁሉ ከሽንፈት የተመለሱት መድኖች ባለፉት ሁለት የሊግ ጨዋታዎች አንድ ነጥብ ብቻ ያስመዘገቡ ሲሆን በእነዚህ ጨዋታዎችም ምንም ጎል አለማስቆጠራቸው ዋነኛ ድክመታቸው ነው። በተመሳሳይ በኢትዮጵያ ዋንጫ ሁለተኛ ዙር ጨዋታ ኤሌክትሪክን አሸንፎ ወደ ዛሬው ጨዋታ የሚቀርበው ቡድኑ በዚሁ የአሸናፊነት ስነ-ልቦና ለመቀጠል በዛሬው ጨዋታ የፊት መስመሩን አሻሽሎ መግባት ግድ ይለዋል።

ሁለቱ ቡድኖች በሊጉ 31 ጊዜ ተገናኝተው ኢትዮጵያ ቡና 14 ጨዋታ በማሸነፍ ቀዳሚ ሲሆን መድን 8 ጊዜ አሸንፏል ፤ 9 ጊዜ ደግሞ አቻ ተለያይተዋል። ኢትዮጵያ ቡና 49 ጎሎች ሲያስቆጥር ኢትዮጵያ መድን 33 ጎሎች አስቆጥሯል።

ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከ ወላይታ ድቻ

ባሳለፍነው የጨዋታ ሳምንት ከሀዋሳ ከተማ ጋር 1-1 በሆነ ውጤት ነጥብ የተጋሩት ኢትዮጵያ ንግድ ባንኮች ከተከታታይ ነጥብ መጣል በኋላ አራተኛ ሳምንት ድሬዳዋ ከተማ ላይ ያሳካውን ድል ለመድገም አስከፊን ጅማሮ እያደረገ የሚገኘውን ወላይታ ድቻ 10:00 ሲል በአዲስ አበባ ስታዲየም ያስተናግዳል። አጀማመራቸው እንደ ታሰበው መልካም ያልሆነላቸው ወላይታ ድቻዎች ካደረጓቸው አምስት ጨዋታዎች አንድ ነጥብ ብቻ በመያዝ የሊጉ ሰንጠረዥ ግርጌ ላይ የተቀመጡ ሲሆን የመጀመሪያ ሶስት ነጥባቸውን ለማግኘት ብርቱ የሆነ ፉክክርን ያደርጋሉ ተብሎ ይጠበቃል::

በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በኩል ሁሉም ተጫዋቾች ለጨዋታው ዝግጁ ሲሆኑ በወላይታ ድቻ በኩል መረጃ ለማግኘት ያደረግነው ጥረት አልተሳካም።

ሁለቱ ቡድኖች በሊጉ 12 ጊዜ የግንኙነት ታሪክ ያላቸው ሲሆን ንግድ ባንክ አራት ድቻ ደግሞ ሦስት ጨዋታዎች ሲረቱ ቀሪዎቹ 5 ጨዋታዎች ደግሞ በአቻ ውጤት ተቋጭተዋል። ወላይታ ድቻ 13 ሲያስቆጥር ንግድ ባንክ በአንፃሩ 16 አስቆጥሯል።


ቅዱስ ጊዮርጊስ ከ ሀዲያ ሆሳዕና

ዛሬ ድል ማድረግ የሚችሉ ከሆነ የሊጉን አናት የሚቆናጠጡት ፈረሰኞቹ ከ ነብሮቹ ጋር የሚያደርጉት ጨዋታ ምሽት 12፡00 ይጀመራል።

ካደረጋቸው አምስት የሊግ ጨዋታዎች አራቱን አሸንፎ ከሊጉ መሪ ሲዳማ ቡና በአንድ ነጥብ ብቻ ዝቅ ብሎ ሁለተኛ ደረጃ ላይ የተቀመጠው ቅዱስ ጊዮርጊስ ዛሬ ማሸነፍ የሚችል ከሆነ ሊጉን መምራት ይጀምራል። ቡድኑ በብዙ ረገድ እየተሻሻለና ከጨዋታ ጨዋታ እድገት እያሳየ መሄዱ በጥሩ ጎኑ የሚጠቀስለት ነጥብ ቢሆንም የቡድኑ የግብ ማስቆጠር ኃላፊነት በሁለት ተጫዋቾች ጫንቃ መውደቁ ግን ምናልባትም አሰልጣኝ ፋሲል ተካልኝን ከወዲሁ አማራጭ የማጥቃያ መንገዶችን እንዲፈልጉ የሚያስገድድ ነው።

በሊጉ ምንም ጨዋታ ካላሸነፉ አምስት ቡድኖች መካከል አንዱ የሆነው ሀዲያ ሆሳዕና ከአምስት ጨዋታዎች ሁለት ሽንፈት እና ሦስት የአቻ ውጤቶችን ብቻ አስመዝግቦ ካለፈው ዓመት አጀማመሩ በተቃራኒው እየተጓዘ ይገኛል። ቡድኑ ምንም እንኳ ውስን እድገቶች እያሳየ ቢዘልቅም እያሳየ ያለውን መሻሻል ወደ ውጤት መመንዘር አልቻለም። በዛሬው ጨዋታም ለግለ-ሰባዊ ስህተቶች ተጋላጭ የሆነው የኋላ መስመር ማሻሻል እንዲሁም በቅርብ ጨዋታዎች የሚታይ ለውጥ ያሳየው የፊት መስመር እድገት ማስቀጠል ግድ ይላቸዋል።

በቅዱስ ጊዮርጊስ በኩል ጳውሎስ ከንቲባ፣ ሻይዱ ሙስጠፋ እና ፉዐድ አብደላ በጉዳት ምክንያት ከዛሬው ጨዋታ ውጭ ናቸው። በሀዲያ በኩል ሔኖክ አርፊጮ እና ጄይላን ከማል በጉዳት ምክንያት በዛሬው ጨዋታ አይኖሩም።

ቡድኖቹ እስካሁን አስራ ሁለት ጊዜ ተገናኝተዋል። ቅዱስ ጊዮርጊስ አራት፤ ሀዲያ ሆሳዕና ሦስት ድሎችን አሳክተው አምስት ጊዜ ደግሞ ነጥብ ተጋርተዋል። በጨዋታዎቹ ቅዱስ ጊዮርጊስ አስር ሀዲያ ሆሳዕና ደግሞ አምስት ግቦች አስቆጥረዋል።