በ7ኛ ሳምንት የምድብ አንድ የመጨረሻ ጨዋታዎች ምድረገነት ሽረ ድሬዳዋ ከተማን 2ለ0 ሲያሸንፍ መቐለ 70 እንደርታ እና ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ 2ለ2 ተለያይተዋል።
ድሬዳዋ ከተማ ከ ምድረገነት ሽረ

07፡00 ሲል በአ/አ ስታዲየም በዋዳ ዳኛ መለሠ ንጉሤ መሪነት በተካሄደው ጨዋታ የመጀመሪያው አጋማሽ ለ 30 ያህል ደቂቃዎች ጠንካራ የማጥቃት እንቅስቃሴ ያልተደረገበት ነበር። ሆኖም ግን ወደ ተጋጣሚ ሳጥን በመድረሱ በኩል የተሻሉ የነበሩት ምድረገነት ሽረዎች ነበሩ።
የጨዋታው የመጀመሪያ ለግብ የቀረበ ሙከራ 30ኛው ደቂቃ ላይ ሲደረግ ዳንኤል ዳርጌ ከሽመክት ጉግሳ በተቀበለው ኳስ ከሳጥኑ የግራ ክፍል ላይ ሆኖ መሬት ለመሬት በመምታት ያደረገው ሙከራ በግቡ የግራ ቋሚ በኩል ለጥቂት ወጥቶበታል። አጥቂው ከአንድ ደቂቃ በኋላ ተመሳሳይ ቦታ ላይ ከሽመክት በድጋሚ የተቀበለውን ኳስ ወደ ግብ ሞክሮም በተመሳሳይ በግቡ የግራ ቋሚ በኩል ለጥቂት ወጥቶበታል። ሽረዎች 42ኛው ደቂቃ ላይ ግብ አስቆጥረው በአንደኛ ረዳት ዳኛው ከጨዋታ ውጪ በሚል ተሽሮባቸዋል። ሽመክት ጉግሳ ወደ ሳጥን የሰነጠቀለትን ኳስ ተጠቅሞ ኳሱን መረቡ ላይ ማሳረፍ የቻለው አቤል ማሙሽ ነበር።

በማጥቃት እንቅስቃሴው ብልጫ የነበራቸው ምድረገነት ሽረዎች 43ኛው ደቂቃ ላይ የመጀመሪያ ጎላቸውን አስቆጥረዋል። ዳንኤል ዳርጌ ተደጋጋሚ ሙከራዎችን ያደረገበት ቦታ ላይ ከሽመክት ጉግሳ የተቀበለውን ኳስ በድንቅ ሁኔታ በግራ እግሩ በመምታት ግብ አድርጎታል። ሽረዎች ጨዋታው ሊጠናቀቅ በተጨመሩ 2 ደቂቃዎች 45+2′ ላይ ተጨማሪ ጎል ለማስቆጠር እጅግ ተቃርበው ነበር። ሬድዋን ሸረፋ በግንባር ገጭቶ ወደኋላ በመመለስ ለግብ ጠባቂው ለማቀበል ሲሞክር በፍጥነት ኳሱን አቋርጦ ያገኘው አቤል ማሙሽ ከፍ አድርጎ (ቺፕ) የሞከረውን ኳስ ግብ ጠባቂው ዐቢዩ ካሣዬ መልሶበታል።
ከዕረፍት መልስም ወደ ተጋጣሚ ሳጥን ተደራጅቶ በመድረሱ በኩል የተሻሉ የነበሩት ሽረዎች ቢሆኑም የመጀመሪያውን ሙከራ ያደረጉት ግን ድሬዳዋዎች ነበሩ። መስዑድ መሐመድ ከቅጣት ምት ያሻገረውን ኳስ ያገኘው መሐመድኑር ናስር ከሳጥኑ የግራ ክፍል ላይ ያደረገው ሙከራ በግቡ አግዳሚ በኩል ለጥቂት ወጥቶበታል።
በፈጣን ሽግግሮች ፈታኝ የነበሩት ሽረዎች 64ኛው ደቂቃ ላይ በዚሁ እንቅስቃሴ ተጨማሪ ግብ አስቆጥረዋል። ሽመክት ጉግሳ በቀኝ መስመር እየገፋ የወሰደውን ኳስ ወደ ውስጥ ሲቀንሰው አቤል ማሙሽ ኳሱን ተቆጣጥሮ በተረጋጋ አጨራረስ መረብ ላይ አሳርፎታል። ከሦስት ደቂቃዎች በኋላም ተቀይሮ የገባው ክብሮም ብርሃነ ከሳጥን ውጪ ጥሩ ሙከራ አድርጎ ግብ ጠባቂው ዐቢዩ ተቆጣጥሮበታል።
ወደ ጨዋታው ለመመለስ ተጭነው ለመጫወት የሞከሩት ድሬዳዋ ከተማዎች ወደ ሦስተኛው የሜዳ ክፍል ተደራጅተው ለመድረስ ሲቸገሩ ተስተውሏል። ጨዋታውም በምድረገነት ሽረ 2ለ0 አሸናፊነት ተጠናቋል።
መቐለ 70 እንደርታ ከ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ
10፡00 ሲል በአ/አ ስታዲየም በዋና ዳኛ መስፍን ዳኜ መሪነት በተካሄደው ጨዋታ በመጀመሪያው አጋማሽ ማራኪ ፉክክር ተደርጓል። የጨዋታው የመጀመሪያ ለግብ የቀረበ ሙከራም 20ኛው ደቂቃ ላይ ሲደረግ ደስታ ዮሐንስ ከቅጣት ምት ባሻገረው ኳስ ኪቲካ ጅማ ያደረገውን ሙከራ ግብ ጠባቂው ጆርጅ ደስታ አግዶበታል። ኢትዮጵያ ንግድ ባንኮችም 23ኛው ደቂቃ ላይ ግብ ለማስቆጠር እጅግ ተቃርበው በዛብህ ካቲሶ ከመሃል የሰነጠቀለትን ኳስ እየገፋ ወስዶ ከግብ ጠባቂው ሶፎንያስ ሰይፈ ጋር የተገናኘው ኤፍሬም ሌዳሞ ሳይጠቀምበት ቀርቷል።
ጨዋታው 30ኛ ደቂቃ ላይ ሲደርስ መቐለዎች ግብ አስቆጥረዋል። ፍጹም ዓለሙ ከግራ መስመር ያቀበለውን ኳስ ያገኘው ኪቲካ ጅማ ከሳጥን ጠርዝ በግሩም አጨራረስ ኳሱን መረብ ላይ አሳርፎታል።
የመጀመሪያው አጋማሽ ሊጠናቀቅ 3 ደቂቃዎች ተጨምረው 45+2ኛው ደቂቃ ላይ ንግድ ባንኮች ግብ አስቆጥረው ወደ ጨዋታው ተመልሰዋል። ሳይመን ፒተር ከቀኝ መስመር ያሻገረውን ኳስ ግብ ጠባቂው ሶፎንያስ ሰይፈ ቢመልሰውም ያንኑ ኳስ ኤፍሬም ሌዳሞ አስቆጥሮት በአቻ ውጤት ወደ ዕረፍት አምርተዋል።

ከዕረፍት መልስ ጨዋታው በጀመረ በ20 ሴኮንዶች ውስጥ ባንኮች ጎል ለማስቆጠር እጅግ ተቃርበው በዛብህ ካቲሶ ከመሃል ሜዳ የሰነጠቀውን ኳስ ተጠቅሞ አዲስ ግደይ ግብ ጠባቂውን ሶንፎያስ ለማለፍ ሞክሮ ግብ ጠባቂው ሲመልስበት ያንኑ ኳስ ያገኘው ኤፍሬም ሌዳሞም ያደረገውን ሙከራ ግብ ጠባቂው በድጋሚ አድኖበታል። ጨዋታው 48ኛ ደቂቃ ላይ ሲደርስ ንግድ ባንኮች ጨዋታውን መምራት ጀምረዋል። ሳይመን ፒተር ከመሃል ሜዳ ያሻገረውን ኳስ ያገኘው አዲስ ግደይ ከሳጥኑ የግራ ጠርዝ ላይ ሆኖ በድንቅ አጨራረስ ግብ አድርጎታል።

በሁለቱም በኩል ቶሎ ቶሎ ወደ ሳጥን የመድረስ ፍላጎት ባስተዋልንበት ጨዋታ መቐለዎች 61ኛው ደቂቃ ላይ በብርሃኑ አዳሙ አማካኝነት ሙከራ ካደረጉ በኋላ ግብ ጠባቂያቸው ሶፎንያስ ሰይፈ በመሐመድ ዘጉኤ ተቀይሮ ተወጥቷል። ሆኖም በውድድሩ የመጀመሪያ ጨዋታውን ለማድረግ ተቀይሮ የገባው ግብ ጠባቂው መሐመድ ዘጉኤ ተቀይሮ በገባበት ቅጽበት ከሳጥን ውጪ በተስፋዬ ታምራት የተደረገበትን ፈታኝ ሙከራ መመለስ ችሏል።
መቐለ 70 እንደርታዎች 80ኛው ደቂቃ ላይ የመስመር ተከላካያቸውን አሰጋኸኝ ጴጥሮስን በቀይ ካርድ አጥተዋል። ተጫዋቹ የኤፍሬም ሌዳሞን አንገት ከኋላ በመምታቱ ነው ከሜዳ የተሰናበተው። ሆኖም ግን ጨዋታው ሊጠናቀቅ 6 ደቂቃዎች ተጨምረው 90+5′ ላይ ሱሌይማን ሐሚድ ከቅጣት ምት የመታው ኳስ የናትናኤል ዳንኤልን ጭንቅላት ጨርፎ መረቡ ላይ አርፎ ጨዋታውም 2-2 ተጠናቋል።

