በዘጠነኛ ሳምንት የመጨረሻ ቀን የተደረጉ የምድብ አንድ ተጠባቂ ጨዋታዎች በተመሳሳይ የ1ለ1 ውጤት ተጠናቅቀዋል።
ሀዋሳ ከተማ ከ መቻል
07፡00 ሲል በኢንተርናሽናል ዋና ዳኛ በላይ ታደሰ መሪነት በተጀመረው ጨዋታ መቻሎች ገና በመጀመሪያው ደቂቃ ጠንካራ ሙከራ አድርገዋል። ቻርለስ ሙሴጌ ከሳጥን ውጪ አክርሮ የመታው ኳስ በግቡ የግራ ቋሚ በኩል ለጥቂት ወጥቶበታል።
በማጥቃት እንቅስቃሴው በኩል የተሻሉ የነበሩት መቻሎች 16ኛው ደቂቃ ላይ በኮሊንስ ኮፊ አማካኝነት ከረጅም ርቀት ዒላማውን የጠበቀ ሙከራ ማድረግ የቻሉ ሲሆን 38ኛው ደቂቃ ላይ ጨዋታውን መምራት ጀምረዋል።
ቻርለስ ሙሴጌ ከሳጥኑ የቀኝ ጠርዝ ወደ ውስጥ ኳስ ሲያሻግር ወንድማገኝ ማዕረግ በእጁ በመንካቱ የተሰጠውን የፍጹም ቅጣት ምት ኮሊንስ ኮፊ ማስቆጠር ችሏል።

ከዕረፍት መልስ ጨዋታው ተሻሽሎ ሲቀጥል በተለይም በማጥቃት እንቅስቃሴው በኩል ተሻሽለው የቀረቡት ሐይቆቹ ነበሩ። ጌታነህ ከበደ 62ኛ ደቂቃ ላይ በግንባር ገጭቶ ሙከራ ካደረገ ከ6 ደቂቃዎች በኋላ ጎል አስቆጥሮም አቻ አድርጓቸዋል። የአብሥራ ደግፌ ከቀኝ መስመር ያሻገለትን ኳስ ከሳጥን ጠርዝ ላይ የተቆጣጠረው አጥቂው በድንቅ አጨራረስ ነበር ኳሱን መረብ ላይ ያሳረፈው።
የጨዋታ ብልጫው ወደ ሀዋሳዎች እያጋደለ በመጣባቸው የመጨረሻ ደቂቃዎች ሐይቆቹ 84ኛው ደቂቃ ላይ ተጨማሪ ጎል ለማስቆጠር እጅግ ተቃርበው የአብሥራ ደግፌ ያቀበለውን ኳስ ያገኘው ጌታነህ ከበደ በግራ እግሩ ያደረገውን ሙከራ ፈቱዲን ጀማል አግዶበታል። ከሦስት ደቂቃዎች በኋላም ተጨማሪ ለጎል የቀረበ ሙከራ ካደረጉ በኋላ ጨዋታው 1ለ1 ተጠናቋል።

መቐለ 70 እንደርታ ከ ፋሲል ከነማ
10፡00 ሲል በኢንተርናሽናል ዋና ዳኛ ኤፍሬም ደበሌ መሪነት በተደረገው ጨዋታ በመጀመሪያው አጋማሽ በሁለቱም በኩል ረጃጅም ኳሶችን በብዛት የተመለከትንበት ነበር።
የመጀመሪያው ለግብ የቀረበ ሙከራ 11ኛው ደቂቃ ላይ በመቐለዎች አማካኝነት ሲደረግ ሱሌይማን ሐሚድ ከቀኝ መስመር ያሻገረውን ኳስ ያገኘው ስንታየሁ መንግሥቱ በግንባር ገጭቶ ያደረገው ሙከራ ለጥቂት ወጥቶበታል።
በማጥቃት እንቅስቃሴው በኩል የተሻሉ የነበሩት መቐለዎች 19ኛው ደቂቃ ላይም በፍጹም ዓለሙ አማካኝነት ከርቀት ሙከራ ቢያደርጉም ግብ ጠባቂው ሞይስ ፖዎቲ ይዞበታል።
የጨዋታው ትኩረት ሳቢ ትዕይንት 36ኛው ደቂቃ ላይ ሲፈጠር የፋሲል ከነማው ያሬድ ብርሃኑ ከዋሳዋ ጄኦፍሪ በተሻገረለት ኳስ ወደ ሳጥን ጠርዝ ሲደርስ ፍሬዘር ካሳ ከጀርባው ቢጥለውም ለዋና ዳኛ ኤፍሬም ደበሌ አሳማኝ አልነበረም።

ከዕረፍት መልስ ጨዋታው በተሻለ ፉክክር ሲቀጥል 51ኛው ደቂቃ ላይ የመቐለው ስንታየሁ መንግሥቱ ከሳጥን ውጪ ሙከራ ካደረገ በኋላ ፋሲሎች 59ኛው ደቂቃ ላይ ጎል ለማስቆጠር ተቃርበው ነበር። በረከት ግዛው ወደ ሳጥን የላከውን ኳስ ግብ ጠባቂው በግንባር ገጭቶ ለመራቅ ሲሞክር ኳሱን ያገኘው አቤኔዘር ዮሐንስ ከፍ አድርጎ የመታው ኳስ በግቡ አግዳሚ በኩል ዒላማውን ሳይጠብቅ ቀርቷል።
ድራማዊ ትዕይንቶች በነበሩበት የመጨረሻ ደቂቃዎች 89ኛው ደቂቃ ላይ ፋሲሎች ጎል አስቆጥረዋል። ዳግም አወቀ በግራ መስመር ከተገኘ የማዕዘን ምት ያሻገረውን ኳስ ተቀይሮ የገባው ናትናኤል ማስረሻ በግንባሩ በመግጨት ማስቆጠር ችሏል።
ጨዋታው በዐፄዎቹ አሸናፊነት የተጠናቀቀ ቢመስልም 90+2′ ላይ ብርሃኑ አዳሙ ከግራ መስመር ያሻገረውን ኳስ ስንታየሁ መንግሥቱ በግንባሩ ከገጨው በኋላ ኳሱን ያገኘው ፍጹም ዓለሙ የቀድሞ ቡድኑ ላይ ጎል አስቆጥሮ ምዓም አናብስትን አቻ አድርጓል። ጨዋታውም 1ለ1 ተጠናቋል።


