ዐበይት ጉዳዮች 1 | የሁለት ዓለም ሳጥኖች

ዐበይት ጉዳዮች 1 | የሁለት ዓለም ሳጥኖች

መረቡን የማያስደፍረው የተጋጣሚ መረብም እምብዛም የማይደፍረው አዳማ ከተማ …

ከውድድር ዓመቱ ጅማሮ በፊት ለዋንጫ ከታጩት ቡድኖች አንዱ የሆነው በአሰልጣኝ ስዩም ከበደ የሚመራው አዳማ ከተማ በሲቢኢ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ባደረጋቸው 9 ጨዋታዎች 4 ድል፣ 4 አቻ እንዲሁም 1 ሽንፈት አስመዝግቦ 16 ነጥቦች በመሰብሰብ 4ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል። ቡድኑ በሁለቱም ሳጥኖች ያለው የአፈፃፀም ደረጃም በ 9 ሳምንታት ጉዞ ውስጥ ትኩረት ሳቢ ከሆኑ ጉዳዮች አንዱ ነው። በብዙዎች የተጠበቀው እና አመራጨ ብዙው የፊት መስመር ፍሬአማ መሆን አቅቶት የኋላ መስመሩ ግን ከብዙዎች ግምት ውጭ የሊጉ ምርጡ ጥምረት ሆኗል።

የተጋጣሚ መረብ እምብዛም የማይደፍረው የፊት መስመር !

አዳማ ከተማ በሊጉ ባላቸው የፊት መስመር ስብስብ ጥራት እና ጥልቀት ቀዳሚ ከሆኑ ክለቦች አንዱ ነው። ሆኖም የፊት መስመሩ የዘጠኝ ሳምንታት ጉዞ ሲመዘን አጥጋቢ ለማለት ያዳግድታል፤ የተጠበቀው እና ሜዳ ላይ የታየው እንቅስቃሴም ለየቅል ነው ቢባል የቃሉ ግነት እምብዛም ነው።

ቡድኑ በ2017 የውድድር ዓመት በጣምራ 43 ግቦች ያስቆጠሩ [ አሕመድ ሑሴን (13) ፣  አቡበከር ሳኒ (8) ፣ ቢንያም አይተን (8) ፣ ነቢል ኑሪ (9) ፣ ዳዋ ሆቴሳ (5) ] ያካተተ ጥራት ያላቸው የፊት መስመር ተጫዋቾች ቢኖሩትም በዘጠኝ ሳምንታት የሊጉ ጉዞ ያስቆጠረው የግብ መጠን 5 ብቻ ነው። ከተቆጠሩት 5 ግቦች ውስጥም በክፍት የጨዋታ እንቅስቃሴ የተቆጠሩ 2 ብቻ ናቸው። ነቢል ኑሪ ኢትዮጵያ ቡና ላይ አሕመድ ሑሴን ደግሞ ነገሌ አርሲ ላይ ያስቆጠሯቸው ግቦችም በክፍት የጨዋታ እንቅስቃሴ የተቆጠሩት ናቸው። የቡድኑ የፊት መስመር ተሰላፊዎች ጥራት ከግቦቹ መጠን እና የተቆጠረበት መንገድ አንፃር ሲታይም አፈፃፀሙ ዝቅተኛ መሆኑ ማሳያ ሲሆን ከሊጉ ጅማሮ በፊትም አዳማ ከተማ በዚህ ልክ ግቦችን ለማስቆጠር ይቸገራል ብሎ የገመተ አልነበረም።

በእስካሁን የሊጉ ጉዟቸው የተለያዩ የፊት መስመር ጥምረቶችን በመቀያየር የግብ ማስቆጠር ችግሩን ለመፍታት ጥረት ያደረጉት አሰልጣኝ ስዩም ከበደ ባለፈው ዓመት እናት ክለባቸውን ከመውረድ ለመታደግ የሞት ሽረት ትግል ባደረጉት ተስፈኞቹ ቢንያም አይተን እና ነቢል ኑሪ፤ የክለቦቻቸው ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪዎች የነበሩት አሕመድ ሔሴን እና ዳዋ ሆጤሳ እንዲሁም በቻምፕዮኑ መድን ሁለተኛ ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪ በነበረውን አቡበከር ሳኒ  ያለው ውህደት ወደ ላቀ ደረጃ ከፍ የማድረግ የቤት ስራም ይጠብቃቸዋል።

እንደ አለት የጠነከረ የማይደፈረው ተከላካይ ክፍል !

ዳግም በተወለደው አላዛር ማርቆስ፤ በአሳዳጊ ክለቡ ሂወት የተመቸው መናፍ ዐወል እና በሁለገቡ ሙጂብ ቃሲም የሚመራው እንዲሁም ዓብዱልከሪም መሐመድ፣ መድሃኔ ብርሃኔ፣ ሳሙኤል ዮሀንስ እና እዮብ ማቲያስን ያካተተው የአዳማ ከተማ የተከላካይ ክፍል በዚህ ደረጃ ጠንካራ እና የማይቀመስ ይሆናል ብሎ የገመት አልነበረም።

ጥምረቱ በሊጉ ካከናወናቸው 9 ጨዋታዎች ውስጥ በ 8ቱ መረቡን አስከብሮ 2 ግቦችን ብቻ አስተናግዷል፤ ቁጥሮችም ለጥንካሬው ምስክሮች ናቸው። የቡድኑ የተከላካይ ክፍል በሊጉ ምርጡ ጥምረት መሆኑ አለመመስከር ንፉግነት ነው፤ ሆኖም የሚገባውን ያክል ሙገሳ እና በቂ ሽፋን አላገኘም። መከላከል የቡድን ስራ መሆኑ ቢታመንም በዚህ የጋራ ውቅር ውስጥ የግለሰቦች ሚና ጎልቶ የሚወጣባቸው አጋጣሚዎች ይኖራሉ ፤ ታድያ ስለ አዳማ ከተማ የመከላከል ጥንካሬ ስናስብ የተከላካይ መስመራቸው እና ግብ ጠባቂያቸው አበርክቶ የላቀ መሆኑን መመልከት ይቻላል።

ከዓመታት በፊት ከሀዋሳ ከተማ የዕድሜ እርከን ቡድኖች ወደ ዋናው በማደግ ሊጉ በአስደናቂ ግብ አጠባበቅ ተዋውቆ የነበረው አላዛር ማርቆስ ወደ  ባህርዳር ከተማ ካመራ ወዲህ ግን እድገቱ የተገታ ይመስል ነበር ታድያ ዘንድሮ በአዳማ ከተማ ዳግም የእግር ኳስ ህይወቱን እያነቃቃ ይገኛል። ቁመቱ መለሎው የግብ ዘብ በአዳማ ከተማ መከላከል ውስጥ ያለው አበርክቶ ለመረዳት በተለይ በቆሙ ኳሶች ጊዜ በሳጥን ውስጥ የተሻሙ ኳሶችን ከተጋጣሚ ተጫዋቾች ቀድሞ የሚይዝበት ቅልጥፍና (Cross Engagement) አስደናቂ ነው።

ከአላዛር ፊት ያሉት ሁለቱ የመሀል ተከላካዮች ጥምረት ሌላው አድናቆት የሚቸረው ነው ፤ በመናፍ ዓወል እና ሙጂብ ቃሲም የሚመራው የተከላካይ መስመር ለተጋጣሚዎች እጅግ ፈታኝ ሆኖ እያስተዋልን እንገኛለን። አዳማ ከተማን ለቆ በፋሲል ከነማ፣ ባህርዳር ከተማ እና በመቐለ 70 እንደርታ ቆይታ የነበረው መናፍ ዓወል ጉዳት በተፈለገው ልክ እንዳያገለግል አግዶት በ2017 በመቐለ መለያ 3 ጨዋታዎች ላይ ብቻ ቢሳተፍም አሁን ላይ ወደ እናት ክለቡ ከተመለሰ ወዲህ ከጉዳት ነፃ ሲሆን ምን ማድረግ እንደሚችል በሚገባ እያሳየን ይገኛል።

የመናፍ አጣማሪ የሆነው እና ላለፉት ዓመታት በተለያዩ ሚናዎች የምናውቀው ሙጂብ ቃሲም ዘንድሮ ወደ ኃላ በመመለስ የአዳማ ከተማ መከላከል ቁልፍ ሰው ሆኖ ተገኝቷል ፤ በዘጠኙም ጨዋታዎች ተሳትፎ ያደረጉት ሁለቱ ተጫዋቾች በተመጋጋቢ ክህሎታቸው የአዳማ ከተማን መከላከል እንደ አለት የጠነከረ አድርገውታል። በተጨማሪነት በቀኝ መስመር እና በግራ መስመር እየተፈራረቁ ያገለገሉት ተከላካዮቹ ዓብዱልከሪም መሐመድ እና መድሃኔ ብርሃኔ እንዲሁም ሳሙኤል ዮሀንስ እና እዮብ ማቲያስ ያደረጉት አበርክቶም አስደናቂ  ነው።

የቡድን ግንባታ መሰረት መከላከል እንደሆነ ይታመናል አሁን አዳማ ከተማ ያንን ጠንካራ የመከላከል ደጀን ያገኝ ይመስላል፤ ታድያ ቀጣዩ የቤት ስራ የሚሆነው ዕድሎችን መፍጠር እና ግቦችን ቀጣይነት ባለው መልኩ የማግኘት ጉዳይ ይሆናል። በ2017 ውድድር ዓመት የሊጉን ዋንጫ ያሳካው ኢትዮጵያ መድን በመጀመሪያው ዙር በተከናወኑ 17 ጨዋታዎች 5 ግቦች ብቻ በማስተናገድ በ 12 ጨዋታዎች መረቡን ሳያስደፍር መውጣት ችሎ ነበር፤ የተከላካይ ክፍሉ በቡድኑ የቻምፕዮንነት ጉዞ የነበረው ሚናም አይተኬ ነበር። አዳማ ከተማዎችም በመከላከሉ ያላቸው ጥንካሬን ማስቀጠል የሚችሉ ከሆነ ፊት መስመር ላይ ካላቸው ሰፊ አማራጭ አንፃር በሊጉ ተፎካካሪ ሆነው ሊቀጥሉ የሚችሉበት ዕድል ሰፊ ይመስላል።

በቡድኑ የዘጠኝ ሳምንታት ጉዞ ውስጥ የፊት መስመሩ  በግብ አስቆጣሪነታቸው የሚታወቁ ተጫዋቾች ይዞ በሚጠበቀው ልክ  የተጋጣሚን መረብ ለመድፈር መቸገሩ፤ የኋላ ክፍሉ ደግሞ ሳይገመት የሊጉ ምርጥ ጥምረት በመሆን መረቡን አስከብሮ መውጣት ዕለታዊ ተግባሩ መሆኑም ትኩረት የሚስበው ጉዳይ ነው። የአዳማ ከተማ የመከላከል ጥንካሬ የቡድኑን የውድድር ዘመን ጉዞ ያቃና ይሆን ? የሚለው ጥያቄም ተጠባቂ ነው !