ሪፖርት | ዐፄዎቹ ነጌሌ አርሲን ሲያሸንፉ ወልዋሎ እና ቡና አቻ ተለያይተዋል

ሪፖርት | ዐፄዎቹ ነጌሌ አርሲን ሲያሸንፉ ወልዋሎ እና ቡና አቻ ተለያይተዋል

በ10ኛ ሳምንት ሁለተኛ ቀን ጨዋታዎች ወልዋሎ ዓ/ዩ ከ ኢትዮጵያ ቡና 1ለ1 ሲለያዩ እጅግ ማራኪ በነበረው ጨዋታ ፋሲል ከነማ ነጌሌ አርሲን 1ለ0 አሸንፏል።

ወልዋሎ ዓ/ዩ ከ ኢትዮጵያ ቡና

7፡00 ሲል በኢንተርናሽናል ዋና ዳኛ ኤፍሬም ደበሌ መሪነት በተጀመረው ጨዋታ ቡናማዎቹ ገና በ10ኛው ደቂቃ ነበር በጨዋታው መምራት የጀመሩት። አቡበከር አዳሙ ከቀኝ መስመር ያሻገረውን ኳስ ያገኘው ዘላለም አባተ በግንባሩ በመግጨት ኳሱን መረቡ ላይ አሳርፎታል።

ግብ ከተቆጠረባቸው በኋላ መልስ ለመስጠት ያልዘገዩት ወልዋሎዎች 19ኛው ደቂቃ ላይ የአቻነት ግብ አስቆጥረዋል። ሙሉዓለም መስፍን ከረጅም ርቀት ከቅጣት ምት ወደ ሳጥን ያሻገረውን ኳስ በኮንኮኒ ሀፊዝ እና ፍቃዱ መኮንን ከተጨራረፈ በኋላ ያገኘው ኪሩቤል ወንድሙ ግብ አድርጎታል።

ቀስ በቀስ እየተቀዛቀዘ በሄደው ጨዋታ የኢትዮጵያ ቡናው አቡበከር አዳሙ 40ኛው ደቂቃ ላይ በደካማ እግሩ ሳይጠቀምበት ከቀረው ኳስ ውጪም ይህ ነው የሚባል የግብ ዕድል ሳይፈጠር ጨዋታው ወደ ዕረፍት አምርቷል።

ከዕረፍት መልስ በማጥቃት እንቅስቃሴው በኩል እየተዳከመ በሄደው ጨዋታ ቡናማዎቹ 50ኛው ደቂቃ ላይ በፍቃዱ ዓለማየሁ ከሳጥን ውጪ አክርሮ መቶት በግቡ አግዳሚ በኩል በወጣበት እንዲሁም 75ኛው ደቂቃ ላይ ዘላለም አባተ ከሳጥኑ የቀኝ ክፍል ከአቡበከር አዳሙ በተቀበለው ኳስ ሙከራ አድርጎ ሰመረ ሀፍተይ ተደርቦ ካገደበት ኳስ ውጪ ተጠቃሽ እንቅስቃሴዎች ሳይኖሩ ጨዋታው 1ለ1 ተጠናቋል።

ፋሲል ከነማ ከ ነጌሌ አርሲ

10፡00 ሲል በአዲሱ ኢንተርናሽናል ዋና ዳኛ ሄኖክ አበበ መሪነት የተካሄደው ጨዋታ ማራኪ ፉክክር የተደረገበት ነበር። ገና በ4ኛው ደቂቃ ምኞት ደበበ እና ሮሆቦት ሰላሎ መሃል በተገጨ እና ከሳጥን መስመር ማለፍ አለማለፉ አነጋጋሪ ሆኖ በግብ ጠባቂው ኢድሪሱ አብዱላሂ በተያዘው ዐፄዎቹን መሪ ለማድረግ ተቃርቦ በነበረው ኳስ ግለቱን የጀመረው ጨዋታ 9ኛው ደቂቃ ላይ ጎል ሊቆጠርበት እጅግ ተቃርቦ ነበር። ሮሆቦት ሰላሎ ለግብ ጠባቂው ለማቀበል ሲሞክር ያሬድ ብርሃኑ በመሃል ኳሱን አቋርጦ እየገፋ በመውሰድ ያደረገው ሙከራ የግቡን የግራ ቋሚ ገጭቶ ወጥቶበት ወርቃማውን ዕድል ሳይጠቀምበት ቀርቷል።

በማጥቃት እንቅስቃሴው በኩል ብልጫ የነበራቸው ፋሲሎች 32ኛው ደቂቃ ላይም ተጨማሪ ዕድል ፈጥረው በረጅም የተሻማውን ኳስ ያሬድ ብርሃኑ ከገጨው በኋላ ያገኘው ዳግም አወቀ በግንባር ገጭቶ ያደረገው ሙከራ በግቡ አግዳሚ በኩል ዒላማውን ሳይጠብቅ ወጥቶበታል።

ቀስ በቀስ ወደ ጨዋታው ለመመለስ ጥረት ያደረጉት ነጌሌዎች የጨዋታውን ለጎል የቀረበ ሙከራቸውን 45ኛው ደቂቃ ላይ ሲያደርጉ ከቤ ብዙነህ ራሱ ላይ በተሠራ ጥፋት የተሰጠውን የቅጣት ምት በድንቅ ሁኔታ ሞክሮት ግብ ጠባቂው ሞይስ ፖዎቲ በድንቅ ቅልጥፍና አስወጥቶበታል።

ከዕረፍት መልስ የተሻለውን የመጀመሪያ ያለቀለት የግብ ዕድል የፈጠሩት ሰጎኖቹ ነበሩ። 56ኛው ደቂቃ ላይ ሀቢብ ከማል ከከቤ ብዙነህ በተቀበለው ኳስ ያደረገውን ሙከራ ግብ ጠባቂው ሞይስ ፖዎቲ መልሶበታል።

እንደ መጀመሪያው አጋማሽ ሁሉ 58ኛው ደቂቃ ላይም ሮሆቦት ሰላሎ ኳስ ለማራቅ ሲሞክር ተደርቦ ኳሱን በማግኘት ወርቃማ ዕድል ያገኘው ያሬድ ብርሃኑ በደካማ ሙከራ ኳሱን ሳይጠቀምበት ቀርቷል።

ተደጋጋሚ ሙከራዎችን ሲያደርግ የነበረው ያሬድ ብርሃኑ 66ኛው ደቂቃ ላይ ጎል አስቆጥሮ ዐፄዎቹን መሪ አድርጓል። አቤኔዘር ዮሐንስ ከማዕዘን አሻምቶት ዴዚሬ ፓስካል በግንባር ለማራቅ ሞክሮት ምኞት ደበበ ከመታው በኋላ ያንኑ ኳስ አቅጣጫ አስቀይሮ ነው አጥቂው መረብ ላይ ያሳረፈው።

እጅግ ማራኪ ፉክክር እየተደረገበት በቀጠለው ጨዋታ 75ኛው ደቂቃ ላይ የነጌሌው ዴዚሬ ፓስካል ናትናኤል ማስረሻ ላይ ጊዜውን ባልጠበቀ የዓየር ላይ ኳስ ሽሚያ በጭንቅላቱ ናትናኤልን ፊቱን በመምታቱ በሁለት ቢጫ ከሜዳ ሲወጣ ከሦስት ደቂቃዎች በኋላ እጅግ አነጋጋሪ የሆነ ሌላ ቀይ ካርድ ተመዟል። የነጌሌው ግብ ጠባቂ ኢድሪሱ አብዱላሂ በረጅም ያሻገረውን ኳስ ሀቢብ ከማል ሳይደርስበት ቀርቶ ግብ ጠባቂው ሞይስ ፖዎቲ ቢቆጣጠረውም የዕለቱ ዳኛ ሄኖክ አበበ ሀቢብ ኳሱን እንዳያገኘው ጥፋት ሠርተሃል በሚል አሳማኝ ባልሆነ ሁኔታ ምኞት ደበበን በቀይ ካርድ ከሜዳ አስወጥቶታል።

86ኛው ደቂቃ ላይ ከቤ ብዙነህ በግራ እግሩ ጠንካራ ሙከራ አድርጎ ግብ ጠባቂው ሞይስ ፖዎቲ በድንቅ ቅልጥፍና ያስወጣበት ኳስ የጨዋታው የተሻለ የመጨረሻ ሙከራ ሆኖ ጨዋታው በፋሲል ከነማ 1ለ0 አሸናፊነት ተጠናቋል።