በሲቢኢ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 13ኛ ሳምንት በመጀመሪያ ቀን የሚደረጉ ጨዋታዎችን የተመለከቱ መረጃዎች እንደሚከተለው አሰናድተናል።

አዳማ ከተማ ከ ፋሲል ከነማ
የሳምንቱ የመጀመሪያ የሆነው እና ከተጠባቂዎቹ መካከል የሆነው መርሐግብር 07፡00 ሲል በአዲስ አበባ ስታዲየም ይካሄዳል።
በመቻል ካስተናገዱት ሽንፈት አገግመው ሸረ ምድረገነትን በመጨረሻ ደቂቃ የቢኒያም ዐይተን ግብ 1ለ0 ያሸነፉት አዳማዎች ነጥባቸውን 20 አድርሰው በግብ ልዩነት 5ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል። ካደረጋቸው 12 ጨዋታዎች በዘጠኙ ግቡን ሳያስደፍር የወጣው ቡድኑ ቀስ በቀስ የማጥቃት ኃይሉን እንቅስቃሴ እያነቃቃ ቢመጣም አሁንም ግን በተለይም እንደዛሬው ዓይነት ጠንካራ የመከላከል አደረጃጀት ያለው ቡድን ጋር ሲጫወት የሚታይበትን የአጨራረስ ችግር ማስተካከል የአሰልጣኝ ስዩም ከበደ ተቀዳሚ የዛሬ ጨዋታ ዓላማ እንደሚሆን ይጠበቃል።
በጠንካራው መርሐግብር ኤሌክትሪክን 1ለ0 ረተው የመጡት ዐፄዎቹ ከመሪው ሲዳማ ቡና በአንድ ነጥብ አንሰው በ24 ነጥቦች 2ኛ ደረጃ ላይ ይገኛሉ። በአማካይ በየአራት ጨዋታዎች አንድ ጎል ብቻ የሚያስተናግደው ቡድኑ ብዙዎች ከጠበቁት በላይ በጥንካሬ እየገሰገሰ ሲሆን እንደዛሬው ዓይነት በተለይም በመከላከሉ ረገድ ጠንካራ ተጋጣሚ ሲያገኝ ከሚታይበት የሦስተኛ ክፍል ውጤታማነት ችግር በምን መልኩ መፍትሔ ያገኛል የሚለው የሚጠበቅ ነው።
በአዳማ ከተማ በኩል ዳዋ ሆቴሳ እና ኢዮብ ማቲያስ በጉዳት ምክንያት አይኖሩም። በፋሲል ከነማ በኩል ቃልኪዳን ዘላለም ከቅጣት ናትናኤል ገብረጊዮርጊስ እና ብሩክ አማኑኤል ደግሞ ከጉዳት የተመለሱ ሲሆን ምኞት ደበበ በቅጣት አምሳሉ ጥላሁን ደግሞ በጉዳት ከዛሬው ጨዋታ ውጪ ናቸው።
ቡድኖቹ በሊጉ 17 ጊዜ ተገናኝተዋል፤ በግንኙነታቸውም ያለፉትን አራት ተከታታይ ጨዋታዎች ጨምሮ 10 ጊዜ አቻ ሲለያዩ 5 ጊዜ ፋሲል 2 ጊዜ ደግሞ አዳማ አሸንፏል። ዐፄዎቹ 19 ግቦችን ሲያስቆጥሩ አዳማዎች ደግሞ 12 አግብተዋል።
ቅዱስ ጊዮርጊስ ከ ወላይታ ድቻ
ሁለት ከአቻ ውጤት የተመለሱ ቡድኖች የሚያደርጉት ጨዋታ በአ/ሳ/ቴ/ዩ ስታዲየም 9 ሰዓት ሲል ይደረጋል።
የመጨረሻዎቹን ሦስት ተከታታይ ጨዋታዎች በተመሳሳይ የ1-1 ውጤት ያጠናቀቁት ፈረሰኞቹ በተለይም ከንግድ ባንክ እና መቐለ ጋር ባደረጓቸው ጨዋታዎች ቀድመው ጎል የማስቆጠር ዕድሉን አግኝተው አለመጠቀማቸው አስቆጪው ትውስታቸው ነው። ከተጫወታቸው ጨዋታዎች (12) ያነሰ የጎል የመጠን (10) ያስቆጠረው ቡድኑ አቤል ያለውን ከቅጣት መልስ ቢያገኝም አሁንም ግን በተለይ የግብ ዕድሎችን በመጨረሱ በኩል ፈጣን መሻሻል ያስፈልገዋል።
ከአሰልጣኝ ለውጥ በኋላ በተሻለ መነሳሳት ውጤታማ የነበሩት የጦና ንቦቹ በመጨረሻዎቹ ሁለት ጨዋታዎች ግን ጥሩ ትውስታ የላቸውም። በሀዲያ 2ለ1 ሲሸነፉ ከአርባምንጭ ጋር ያለ ግብ ተለያይተዋል። ከመቐለ 70 እንደርታ እና ከወልዋሎ ዓ/ዩ በመቀጠል ከፍተኛውን የጎል መጠን (15) ያስተናገደው ቡድኑ በመጨረሻው ጨዋታ በውድድር ዓመቱ ለመጀመሪያ ጊዜ ጎል ሳይቆጠርበት ቢወጣም ደካማ የነበረውን የማጥቃት እንቅስቃሴ በዛሬው ጨዋታ ማነሳሳት የአሰልጣኝ መሳይ የትኩረት ማዕከል ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል።
ፈረሰኞቹ ቢኒያም ፍቅሩን በቅጣት መሳፍንት ጳውሎስን ደግሞ በጉዳት ሲያጣ የፀጋ ከድር መሰለፍ አጠራጣሪ ነው።
ሁለቱ ቡድኖች 22 ጊዜ ተገናኝተው ቅዱስ ጊዮርጊስ 10 ወላይታ ድቻ 7 ድሎችን አሳክተዋል። አምስት ጊዜ ነጥብ ሲጋሩ በጨዋታዎቹ ቅዱስ ጊዮርጊስ 28 ወላይታ ድቻ ደግሞ 17 ጎሎች አስቆጥረዋል።
ኢትዮ ኤሌክትሪክ ከ ወልዋሎ ዓ/ዩ
ሁለቱ በደረጃው ተቃራኒ አቅጣጫ የተቀመጡ ቡድኖች የሚያደርጉት ጨዋታ 10፡00 ሲል በአ/አ ስታዲየም ይደረጋል።
ሽረ ምድረገነት ላይ ወሳኝ ድል ካሳኩ በኋላ ባሳለፍነው ሳምንት በፋሲል ከነማ 1ለ0 የተሸነፉት ኤሌክትሪኮች ከዚሁ ተጋጣሚያቸው ፋሲል (3) በመቀጠል በሊጉ ዝቅተኛው የጎል መጠን (5) የተቆጠረበት ጠንካራ የመከላከል አደረጃጀት አላቸው። ነገር ግን ከደረጃው ግርጌ አካባቢ የሚገኙ ቡድኖች የሚመርጡትን ወደ ራስ ሜዳ ተጠግቶ የመጫወት እንቅስቃሴ ለማስከፈት ባለፉት 8 ጨዋታዎች 3 ጎሎችን ብቻ ያስቆጠረው የማጥቃት ኃይል አፋጣኝ መሻሻልን ይሻል።
መቐለ እና ንግድ ባንክ ላይ ድል ተቀዳጅተው በጥሩ መነሳሳት ላይ የነበሩት ቢጫዎቹ ባለፉት ሦስት ጨዋታዎች ግን ከኢትዮጵያ ቡና እና ከባህር ዳር ከተማ ጋር አቻ ተለያይተው በነጌሌ አርሲ ሽንፈት በማሰተናገዳቸው የለውጥ እንቅስቃሴያቸው ላይ ውሃ ተቸልሷል። ከመቀለ ቀጥሎ ከፍተኛው የጎል መጠን (16) የተቆጠረበት ቡድኑ የኋላ መስመሩ ላይ መጠነኛ መሻሻል ቢታይበትም ከአርባምንጭ (5) ቀጥሎ ዝቅተኛውን የጎል መጠን (7) ያስቆጠረውን የማጥቃት ኃይል ማስተካከል ይጠበቅበታል።
ኤሌክትሪኮች አብዱላሂ አላዩ እና አብነት ተስፋየን በጉዳት ምክንያት የሚያጡ ሲሆን ወልዋሎዎች መጠነኛ ጉዳት የገጠመው ፍቃዱ መኮንን እና በመጨረሻው ጨዋታ በሁለት ቢጫ ከሜዳ የወጣውን ሱልጣን በርኸ አያሰልፉም።
ሁለቱ ቡድኖች በሊጉ 4 ጊዜ ተገናኝተው ወልዋሎ 1 ጊዜ ድል ሲቀናው 3 ጨዋታዎች በአቻ ውጤት ተጠናቀዋል። ወልዋሎ 5 ግቦችን ሲያስቆጥር ኤሌክትሪክ 3 ግቦች ማስቆጠር ችሏል።
አርባምንጭ ከተማ ከ ከሀዋሳ ከተማ
የደረጃው ግርጌ ላይ ያሉት አዞዎቹ ነፍስ ለመዝራት 3ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡት ሐይቆቹ ደግሞ ወደ ደረጃው መሪ የበለጠ ለመጠጋት የሚያደርጉት ተጠባቂ ጨዋታ ምሽት 12፡00 በአ/ሳ/ቴ/ዩ ይካሄዳል።
አሰልጣኝ በረከት ደሙን በማሰናበት የቀድሞውን ኮከብ አበባው ቡጣቆ ከሾሙ በኋላ በመቐለ 2ለ0 ተሸንፈው የነበሩት አርባምንጮች በመጨረሻው የድቻ ጨዋታ ግን ያለ ግብ ተለያይተው በውድድሩ 5ኛውን የአቻ ውጤት አስመዝግበዋል። አዲሱ አሰልጣኝ በቅድሚያ ለመከላከሉ ትኩረት እንደሚሰጥ በተለያየ መንገድ ቢጠቁምም በ12 ጨዋታዎች አምስት ጎሎችን ብቻ ያስቆጠረው የማጥቃት ኃይል ጎሎችን በማስቆጠር በራስ መተማመኑን መልሶ ማግኘት ይኖርበታል።
ኢትዮጵያ መድን እና ሸገር ከተማን ከመመራት ተነስተው ያሸነፉት ሀዋሳዎች ባለፈው የጨዋታ ሳምንት ግን በሀዲያ ሆሳዕና 1ለ0 ተሸንፈዋል። ሜዳ ላይ ማራኪ የሆነ እንቅስቃሴ ከሚያደርጉ ቡድኖች መካከል የሚጠቀሱት ሐይቆቹ ከመሪው ሲዳማ ቡና በአምስት ነጥቦች ዝቅ ብለው በ20 ነጥቦች 3ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡ ሲሆን የዛሬ ተጋጣሚያቸው ከውጤት ጋር ለመታረቅ ፈታኝ ተጋጣሚ ሆኖ እንደሚቀርብ ስለሚጠበቅ ይህንን ጨዋታ ማሸነፍ ዋጋው ቀላል አይደለም።
ሁለቱ ቡድኖች እስካሁን በሊጉ 20 ጊዜ የመገናኘት ታሪክ አላቸው። ከዚህ ውስጥ 8 ጨዋታዎች በአቻ ውጤት ሲጠናቀቁ ሀዋሳ ከተማ 7 ጊዜ አርባምንጭ ደግሞ 5 ጊዜ ድል ቀንቷቸዋል። በጨዋታዎቹ ከተቆጠሩ 36 ግቦች 20ዎቹ የሀዋሳ፤ 16ቱ ደግሞ የአርባምንጭ ሆነው ተመዝግበዋል።
በአርባምንጭ ከተማ በኩል የመስመር ተከላካዩ ሳሙኤል አስፈሪ ለረጅም ጊዜ ከሜዳ እንደሚርቅ ሲታወቅ ከጉዳት አገግሞ ድጋሚ ጉዳት አስተናግዶ የነበረው አንዱዓለም አስናቀ ለጨዋታው ዝግጁ መሆኑ ተመላክቷል። በሀዋሳ ከተማ በኩል ሁሉም የቡድኑ አባላት ለጨዋታው ዝግጁ ናቸው።

