ሪፖርት| ነገሌ አርሲ ተከታታይ ድል ሲቀዳጅ ሽረ ምድረ ገነትም ወደ ድል ተመልሷል

ሪፖርት| ነገሌ አርሲ ተከታታይ ድል ሲቀዳጅ ሽረ ምድረ ገነትም ወደ ድል ተመልሷል

አዲስ አበባ ስታዲየም በተደረጉ ጨዋታዎች ነጌሌ አርሲ መቻልን 2ለ0 ሲያሸንፍ አራት ግቦች በተቆጠሩበት ጨዋታም ሽረ ምድረ ገነት ኢትዮጵያ ቡናን 3ለ1 ረቷል።

ነጌሌ አርሲ ከ መቻል

ነጌሌ አርሲ እና መቻል ያገናኘው የዕለቱ ቀዳሚ ጨዋታ በመጀመርያው አጋማሽ ብርቱ ፉክክር የተደረገበት ነበር።

በጨዋታው መቻሎች አብዱልከሪም ወርቁ በአራተኛው ደቂቃ ላይ ባደረጋት ሙከራ ወደ ግብ መድረስ ቢችሉም ግብ በማስቆጠሩ ረገድ ቀዳሚ የነበሩት ግን ነገሌ አርሲዎች ነበሩ። 11ኛው ደቂቃ ላይ ዳዊት ተፈራ ከሳጥኑ ቅርብ ርቀት የተገኘችውን የቅጣት ምት በቀጥታ መቶ በግሩም ሁኔታ  ያስቆጠራት ግብም ሰገኖቹን መሪ ማድረግ ችላለች። ፈጣኑ ከቤ ብዙነህን ዒላማ ባደረጉ ረዣዥም ኳሶች ዕድሎችን ለመፍጠር ጥረት ያደረጉትና በሦስተኛው የሜዳ ክፍል የተሻለ ብልጫ የነበራቸው ሰጎኖቹ 31ኛው ደቂቃ ላይም መሪነታቸውን ያጠናከሩበት ግብ አስቆጥረዋል። ግሩም ሀጎስ ሳጥን ውስጥ ከቤ ብዙነህ ላይ  የሰራውን ጥፋት ተከትሎ የተገኘውን ፍፁም ቅጣት ምት አሸብር ውሮ መቶት ግብ ጠባቂው ምንታምር መለሰ ካዳነው በኋላ አለኝታ ማርቆስ የተመለሰችውን ኳስ ተጠቅሞ ወደ ግብነት በመቀየር የቡድኑን መሪነት ከፍ ማድረግ ችሏል።

በኳስ ቁጥጥር የተሻሉ የነበሩት መቻሎች በአጋማሹ
ግሩም ሀጎስ ከርቀት አክርሮ ካደረጋት ሙከራ ውጭ
ለግብ የቀረቡ አጋጣሚዎች መፍጠር አልቻሉም።
ሰገኖቹ ግን ሀቢብ ከማል በሁለት አጋጣሚዎች ባደረጋቸው ሙከራዎች ግብ ለማስቆጠር ተቃርበው ነበር። ተጫዋቹ በ33ኛው ደቂቃ ላይ ያደረጋት ዒላማዋን ያልጠበቀች ሙከራ እንዲሁም አጋማሹ ሊጠናቀቅ ደቂቃዎች ሲቀሩት ከሳጥን ውስጥ ያገኛትን ኳስ መቶ የግቡን አግዳሚ የመለሰበት ሙከራም የቡድኑን መሪነት ለማስፋት የተቃረቡ ወርቃማ አጋጣሚዎች ነበሩ።

ሁለተኛው አጋማሽ መቻል ወደ ጨዋታው ለመመለስ በርከት ያሉ ጥረቶችን ያደረገበት፤ ነገሌ አርሲዎች ደግሞ ውጤቱን ለማስጠበቅ አፈግፍገው የተጫወቱበት ነበር። ይህ ነው የሚባል የጠራ የግብ ሙከራ ባልታየበት አጋማሽ መቻሎች የግብ ዕድሎችን ለመፍጠር ጥረት ማድረግ ቢችሉም የሰጎኖቹን ወደ ራሱ ሳጥን የተጠጋ የጥብቅ መከላከል አቀራረብ አልፈው ሙከራዎች ማድረግ ሳይችሉ ቀርተው ጨዋታው በመጀመሪያው አጋማሽ በተቆጠሩ ግቦች በነጌሌ አርሲ 2ለ0 አሸናፊነት ተቋጭቷል።

ኢትዮጵያ ቡና ከ ሽረ ምድረ ገነት

ቀዝቀዝ ባለ እንቅስቃሴ ቢጀምርም የኋላ ኋላ
ብርቱ ፉክክር የተደረገበት ኢትዮጵያ ቡና ከ ሽረ ምድረ ገነት  ያገናኘው የዕለቱ ሁለተኛ ጨዋታ በመጀመርያው አጋማሽ በፈጣን ሽግግሮች የታጀበ ነበር።

ጨዋታው 15ኛው ደቂቃ ላይ ስደርስም ሽረዎች መሪ የሆኑበትን ግብ አስቆጥረዋል። ዳንኤል ዳርጌ  ወደ ተከላካይ ጀርባ በረዥሙ የተሻገረችውን ኳስ ተጠቅሞ  በጥሩ አጨራረስ ወደ ግብነት የቀየራት ኳስም ቡድኑን መሪ ማድረግ ችላለች። በአጋማሹ ረዣዥም ኳሶች ዕድሎችን ለመፍጠር ጥረት ያደረጉት ሽረዎች ከአስራ አንድ ደቂቃዎች በኋላም ጥረታቸው ሰምሮ ሁለተኛውን ግብ አስቆጥረዋል። በ26′ ደቂቃ ላይ ክፍሎም ገብረህይወት በጥሩ እይታ በተከላካዮች መካከል አሾልኳት ሽመክት ጉግሳ እግኝቶ ከመረቡ ጋር ያዋሀዳት ኳስም የቡድኑን መሪነት ወደ ሁለት ከፍ ማድረግ ችላለች።

ምንም እንኳን የግብ ብልጫ ቢወስድባቸውም ወደ ጨዋታው ለመመለስ ጫና ፈጥረው የተንቀሳቀሱት ቡናማዎቹ አማኑኤል አድማሱ እና ኦካይ ጁል ካደረጓቸው አስቆጪ ሙከራዎች በኋላ መደበኛ ደቂቃ ተጠናቆ በተሰጠው ጭማሪ ደቂቃ ግብ አስቆጥረዋል።  አዲሱ ተስፋዬ አቡበከር አዳሙ ላይ የሰራውን ጥፋት ተከትሎ የተገኘችውን ፍፁም ቅጣት ምት ራሱ አቡበከር አዳሙ ወደ ግብነት ቀይሮ የግቡን ልዩነት ማጥበብ ችሏል።

እንደ መጀመርያው አጋማሽ ሁሉ ብርቱ ፉክክር የተደረገበት ሁለተኛው ምዕራፍ ቡናማዎቹ የአቻነት ግብ ለማግኘት ባደረጉት ጫና ነበር የጀመረው።

ዘላለም አባተ ካደረጋት ሙከራ ጥቂት ደቂቃዎች በኋላም አቡበከር አዳሙ ከግቡ ቅርብ ርቀት ያገኛትን ኳስ መቶ ሪችሞንድ አይ በድንቅ ብቃት ወደ ውጭ አውጥቶበታል። በዛ ሂደት ውስጥ ግብ ጠባቂው ከማዕዘን ምት የተሻማውን ኳስ ተቆጣጥሮ ያስጀመራትን ኳስም በመልሳ ማጥቃት ሂደት ሽመክት ጉግሳ እና አቤል ማሙሽ ካደረጉት ቅብብል በኋላ ሽመክት ወደ ግብነት ቀይሮ የቡድኑን መሪነት ወደ ሦስት ከፍ ማድረግ ችሏል። እስከመጨረሻው ደቂቃ ድረስ የግብ ማግባት ፍላጎቶች በተስተዋለበት ጨዋታም ሽረ ምድረ ገነቶች በብሩክ ሐድሽ እና ቢንያም ላንቃሞ አማካኝነት ካደረጓቸው ሙከራዎች በኋላ
አራት ግቦችን አስመልክቶን በሽረ ምድረ ገነት 3ለ1 አሸናፊነት ተጠናቋል።