የሊጉን መሪ ሲዳማ እና የደረጃው ግርጌ ላይ ያለውን አርባምንጭ ያገናኘው በአ/ሳ/ቴ/ዩ የተደረገው ብቸኛ ጨዋታ ያለ ግብ ተጠናቋል።

ሁለት በደረጃ ሰንጠረዡ አናት እና ግርጌ ላይ ያሉትን ሲዳማ ቡናን ከአርባምንጭ ከተማ ያገናኘው ብቸኛው ጨዋታ በመጀመሪያ አጋማሽ የአዞዎቹን አንፃራዊ የኳስ ቁጥጥርም ሆነ የግብ ፍለጋ በላይነት ያየንበት ነበር። እድሎችን በመፍጠር ረገድ የተሻሉ የነበሩት አዞዎቹ ዒላማውን የጠበቀ ጠንካራ ሙከራ ማድረግ ባይችሉም የተጋጣሚያቸውን ተከላካይ መስመር በመስመሮች እየገቡ አጋጣሚዎቹን ለመጠቀም ሲጥሩ አስተውለናል።
በኳስ ንክኪ ብልጫም ሆነ በሙከራዎች ብልጫ የተወሰደባቸው የወቅቱ የሊጉ መሪ ሲዳማ ቡናዎች በአጋማሹ እምብዛም ወደፊት ሄደው እድል ሲፈጥሩ ያልተመለከትን ቢሆንም አንድ ዒላማውን የጠበቀ ሙከራ በማድረግ ቀዳሚ የነበሩ ሲሆን ተመስገን መንገሻ ከግራ መስመር ያሻገረውን ኳስ ሀብታሙ ታደሰ አግኝቶ ያደረገውን የተሻለውን ሙከራ ግብ ጠባቂው ከተቆጣጠረባቸው በኋላ ዘለግ ላለ ደቂቃ ሌላ ለግብ የቀረበ ሙከራ ሳንመለከት ጨዋታው ተጠናቆ ወደ እረፍት ሊያመሩ ደቂቃዎች ሲቀሩት 44ኛው ደቂቃ ላይ ዒላማውን ባይጠብቅም ዮሴፍ ዮሐንስ ከሳጥን ውጪ ሆኖ አክርሮ መትቶ ያደረገው ጠንካራው ሙከራ ሲጠቀስ አጋማሹም ያለግብ ተገባዷል።

ሳቢ የጨዋታ እንቅስቃሴ ሳያስመልክት በተመለሰው በሁለተኛ አጋማሽ ሲዳማ ቡና የመጀመሪያወቹን ደቂቃዎች ጫና ፈጥረው ለመጫወት ጥረት ያደረጉበት ቢሆንም የጠራ የግብ ማግባት ሙከራ ማድረግ አልቻሉም። አዞዎች በበኩላቸው የመጀመሪያውን አጨዋወታቸው ይዘው የቀጠሉ ሲሆን ልክ እንደ አንደኛው አጋማሽ የተቃራኒ ቡድን ሜዳ ክፍል እየደረሱ ግቦችን ለማስቆጠር ጥረት ያደረጉ ሲሆን ይገዙ ቦጋለ በመሰመር በኩል ኳስ ይዞ ገብቶ ብቻውን ለነበረው በፍቅር ግዛቸው ያቃበለውን ያለቀ ኳስ ዮሴፍ ዮሐንስ ከእግሩ ስር ከነጠቀው ከአስቆጪው አጋጣሚ በኋላ ተቀይሮ ወደ ሜዳ የገባው በኃይሉ ተስፋየ በሲዳማ ቡና ተከላካዮች ስህተት መነሻ የተገኘውን ኳስ የሳጥኑ ጠርዝ ላይ ሆኖ ያመከነበት እጅግ አስቆጪው ሌላኛው ሙከራ ይጠቀስ እንጂ ጨዋታው በሁለተኛው አጋማሽ ሳቢ ሆኖ መቀጠል ሳይችል ቀርቶ ቀዝቃዛው ጨዋታ ያለግብ ተጠናቋል።

