መረጃዎች| የ14ኛው ሳምንት የመጨረሻ ቀን  ጨዋታዎች

መረጃዎች| የ14ኛው ሳምንት የመጨረሻ ቀን ጨዋታዎች

14ኛው ሳምንት የሲቢኢ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ዛሬ በሚደረጉ መርሐ-ግብሮች ይጠናቀቃል፤ ጨዋታዎቹን የተመለከቱ መረጃዎችም እንደሚከተለው አቅርበንላችኋል

መቻል ከ ባህርዳር ከተማ

20 ነጥቦች የሰበሰቡት መቻሎች በኢትዮጵያ ቡናና ነገሌ አርሲ ከገጠማቸው ሁለት ተከታታይ ሽንፈቶች ለማገገም ወደ ጨዋታው ይቀርባሉ። መቻሎች ለዋንጫ ከታጩት ቡድኖች ዝርዝር ውስጥ ትልቅ ግምት ተሰጧቸው ዓመቱን በተከታታይ አራት ድሎች ቢጀምሩም (በፎርፌ ያገኙትን ድል ጨምሮ) የኋላ ኋላ ተቀዛቅዘው በአሁኑ ወቅት ከመሪው ሲዳማ ቡና በዘጠኝ ነጥብ ርቀት ላይ ይገኛሉ። በዛሬው ዕለት ድል አድርገው ወደ ሰንጠረዡ አናት ለመጠጋትም ከመጨረሻዎቹ አራት ጨዋታዎች በሦስቱ ኳስና መረብ ማገናኘት የተሳነውና በወጥነት መዝለቅ ያልቻለውን የማጥቃት አጨዋወታቸው ማሻሻል ይኖርባቸዋል።

በ13 ሳምንታት ጉዞ 16 ነጥቦች የሰበሰቡት ባህርዳር ከተማዎች ከናፈቃቸው ድል ጋር ለመታረቅ መቻልን ይገጥማሉ። ድል ካደረጉ አምስት የጨዋታ ሳምንታት ያስቆጠሩት የጣና ሞገዶቹ በሊጉ በርካታ የአቻ ውጤቶች ካስመዘገቡ ክለቦች ይጠቀሳሉ። ካከናወኗቸው መርሐ ግብሮች ውስጥ 54% የአቻ ውጤቶች ያስመዘገቡትና በመጨረሻዎቹ አራት ጨዋታዎች በመደዳ ነጥብ የተጋሩት ባህርዳሮች ከዚህ ጨዋታዎችን በአቻ ውጤት የመፈፀም አባዜ ለመላቀቅ በአራት ጨዋታዎች ኳስና መረብ ማገናኘት የተሳነውን የፊት መስመራቸው በብዙ ረገድ ማሻሻል ግድ ይላቸዋል።

መቻል አሁንም በጉዳት ምክንያት የውብሸት ጭላሎ፤ አማኑኤል ዮሐንስ እና ኮሊንስ ኮፊ ግልጋሎት የማያገኝ ሲሆን ሀገሩን በአፍሪካ ዋንጫ ለመወከል ሞሮኮ የነበረው የግብ ዘቡ አሊዮንዜ ናፍያን በበኩሉ ዛሬ ወይም ነገ ወደ ኢትዮጵያ እንደሚመጣ ቢጠበቅም ለዛሬው ጨዋታ ግን እንደማይደርስ ተጠቁሟል። ባህርዳር ከተማዎች በበኩላቸው ማንያዘዋል ካሳና መሳይ አገኘሁን ከጉዳት መልስ ሲያገኙ አጥቂው አማኑኤል ገ/ሚካኤል ግን ግልጋሎት እንደማይሰጥ ተገልጿል።

ሁለቱ ቡድኖች 10 ጊዜ ተገናኝተው ሁለቱ በእኩሌታ 3 ጨዋታዎች ስያሸንፉ 4 ጨዋታዎች በአቻ ውጤት ተጠናቀዋል። ጦሩ 12፣ ሞገዱ 11 አስቆጥረዋል።

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከ ሀድያ ሆሳዕና

16 ነጥቦችን ሰብስበው 11ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡት ኢትዮጵያ ንግድ ባንኮች ዳግም ወደ ድል መንገድ ተመልሰው ሦስት ደረጃዎች ለማሻሻል ከነብሮቹ ጋር ይፋለማሉ። በሲዳማ ቡናና ወልዋሎ ከገጠማቸው ተከታታይ ሽንፈት በኋላ በተደረጉ ጨዋታዎች እጅ ያልሰጡት ሀምራዊ ለባሾቹ በቅርብ ሳምንታት የሚታይ መሻሻል አሳይተዋል። በተጠቀሱት አራት ጨዋታዎች ማግኘት ከሚገባው አስራ ሁለት ነጥብ ስምንቱን ያሳካው ቡድኑ ከሁሉም ነገር በላይ በአራት መርሐ ግብሮች ሰባት ግቦችን በማስቆጠር በድንቅ ብቃት የሚገኘውን የፊት መስመሩ ጥንካሬ ማስቀጠል ይኖርበታል።

ከዛሬው ተጋጣሚያቸው በተመሳሳይ 16 ነጥቦችን መሰብሰብ የቻሉት ሀድያ ሆሳዕናዎች በታህሳስ ወር ጥሩ መሻሻል ካሳዩ ቡድኖች ውስጥ ይጠቀሳሉ። በ8ኛው እና 9ኛው ሳምንት ጨዋታዎች በኢትዮጵያ ቡናና ነገሌ አርሲ ከገጠማቸው ሽንፈት በኋላ ሦስት ተከታታይ ድሎች ማስመዝገብ የቻሉት ነብሮቹ በመጨረሻው መርሐ ግብር በመሪው ሲዳማ ቡና ሽንፈት ቢገጥማቸውም በቅርብ ሳምንታት ያሳዩት እንቅስቃሴ እና ያስመዘገቡት ውጤት ድንቅ ነበር። ደረጃቸውን ለማሻሻል በሚቀርቡበት የዛሬው ጨዋታም በመጨረሻው መርሐ ግብር የመጀመርያ ደቂቃዎች የተስተዋሉባቸው አለመረጋጋቶች ማረም እንዲሁም በሦስት ጨዋታዎች አምስት ግቦችን ካስቆጠረ በኋላ ኳስና መረብ ማገናኘት ያልቻለውን የፊት መስመራቸው የአፈፃፀም ብቃት ማሳደግ ይኖርባቸዋል።

በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በኩል ቢንያም ካሳሁን ከቅጣት ቢመለሰም በጉዳት ምክንያት የካሌብ አማንክዋህ፣ እንዳለ ዮሐንስ እና ዘላለም አበበ ግልጋሎት አያገኝም። በሀዲያ ሆሳዕና በኩል ወሳኙ አጥቂ ተመስገን ብርሃኑ በጉዳት ምክንያት ከዛሬው ጨዋታ ውጪ ነው።

ቡድኖቹ በሊጉ 6 ጊዜ ተገናኝተው ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ 3 አሸንፎ 4 ጎሎችን ማስቆጠር የቻለ ሲሆን ሀድያ ሆሳዕናም 2 ድልና 2 ግብ አስመዝግቦ በተቀረው አንድ ጨዋታ ነጥብ ተጋርተዋል።

ፋሲል ከነማ ከ ኢትዮጵያ ቡና

ከአሰልጣኝ ዮሐንስ ሳህሌ ጋር የተለያዩት ዐፄዎቹ በ25 ነጥቦች 3ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል። በ13ኛው ሳምንት መርሐ ግብር ከአዳማ ከተማ ጋር ነጥብ መጋራታቸውን ተከትሎ ከመሪው በሦስት ነጥቦች ለመራቅ የተገደዱት ዐፄዎቹ አሁን ግን መሪው ሲዳማ ቡና ነጥብ መጣሉን ተከትሎ ልዩነቱን የሚያጠቡበት ዕድል አግኝተዋል። ፋሲል ከነማ በሊጉ ለ13 ሳምንታት ሽንፈት ሳያስተናግድ መዝለቁ እንደ አወንታ የሚጠቀስለት ነጥብ ቢሆንም ተከታታይ ድሎችን ለማስመዝገብ እየተቸገረ ይገኛል። በውድድር ዓመቱ በአንድ አጋጣሚ ብቻ በመደዳ ሦስት ጨዋታዎችን መርታት የቻለው ቡድኑ በዋንጫ ፉክክሩ ለመዝለቅ በመጨረሻዎቹ አራት ጨዋታዎች መረቡ ያላስደፈረውን የተከላካይ ክፍል ጥንካሬ ማስቀጠል እንዲሁም በ13 ጨዋታዎች በአንድ መርሐ ግብር ብቻ ከአንድ ግብ በላይ ያስቆጠረውን የፊት መስመር ማሻሻል ይጠበቅበታል።

15 ነጥቦች በመሰብሰብ በአደገኛው ቀጠና ውስጥ የሚገኙት ኢትዮጵያ ቡናዎች ደረጃቸውን የሚያሻሽሉበት ወሳኝ ድል ፍለጋ ወደ ጨዋታው ይቀርባሉ። መቻል ላይ ከተቀዳጁት ጣፋጭ ድል በኋላ በሽረ ምድረ ገነት የሦስት ለአንድ ሽንፈት የገጠማቸው ቡናማዎቹ ዳግም ወደ ድል መንገድ ለመመለስ ዘርፈ ብዙ መሻሻሎችን ማድረግ ግድ ይላቸዋል። በተለይም በመጨረሻዎቹ አራት ጨዋታዎች ስድስት ግቦችን ያስተናገደውና በሽረ ምድረገነቱ ጨዋታ ይበልጥ ተጋልጦ የነበረው የመከላከል አደረጃጀታቸው አፋጣኝ መፍትሔ የሚሻ የቡድኑ ድክመት ነው። ከዚህ በተጨማሪም በፊት መስመሩ ላይ የሚስተዋለው ዕድሎችን የመጠቀም ድክመት ማረም ከአሰልጣኝ ሳምሶን አየለ ቡድን ይጠበቃል።

ፋሲል ከነማ ምኞት ደበበን በቅጣት ፤ አምሳሉ ጥላሁን፣ በረከት ግዛው እና ቢኒያም ጌታቸውን ደግሞ በጉዳት በዛሬው ጨዋታ አያገኝም። በኢትዮጵያ ቡና በኩል የቡድን ዜና ለማግኘት ያደረግነው ጥረት አልተሳካም።

ሁለቱ ክለቦች በሊጉ እስካሁን 17 ጊዜ የእርስ በእርስ ጨዋታዎች ያደረጉ ሲሆን ሁለቱም ቡድኖች በእኩሌታ አምስት አምስት ድሎች ሲያሳኩ ቀሪዎቹ ሰባት ጨዋታዎች ነጥብ በመጋራት ተጠናቀዋል። ፋሲል ከነማዎች በእነዚህ ጨዋታዎች 15 ግቦችን ሲያስቆጥሩ ኢትዮጵያ ቡናዎች በተመሳሳይ 15 ግቦችን ማስቆጠር ችለዋል። (የተሰረዘው የ2012 የውድድር ዓመት አልተካተተም)

ወላይታ ድቻ ከ ኢትዮጵያ መድን

12 እንዲሁም 13 ነጥቦች የሰበሰቡት ወላይታ ድቻ እና ኢትዮጵያ መድን የሚያደርጉት የ14ኛው ሳምንት የመጨረሻ ጨዋታ በሁለቱም ቡድኖች መካከል ባለው የነጥብ መቀራረብ ብርቱ ፉክክር ይደረግበታል ተብሎ ይጠበቃል።

ከአርባምንጭ ከተማ እንዲሁም ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር ባደረጓቸው ጨዋታዎች በመደዳ ነጥብ ተጋርተው መውጣት የቻሉት ወላይታ ድቻዎች ካሉበት የስጋት ቀጠና ለመውጣት ዳግም ወደ ድል መመለስ ይኖርባቸዋል። ከመጨረሻዎቹ ሦስት ጨዋታዎች ማግኘት ከሚገባቸው ዘጠኝ ነጥቦች ሁለቱን ብቻ ያሳኩት የጦና ንቦቹ በቅርብ ሳምንታት ካሳዩት የተቀዛቀዘ ብቃት በማገገም ሸገር ከተማን ሦስት ለአንድ ባሸነፉበት የ10ኛው ሳምንት ጨዋታ ላይ ያሳዩትን ድንቅ እንቅስቃሴ መድገም ግድ ይላቸዋል ።

አስራ ሦስት ነጥቦች ሰብስበው በወራጅ ቀጠናው አፋፍ የተቀመጡት ኢትዮጵያ መድኖች ከስጋት ቀጠናው ለመራቅ ዛሬ ወሳኝ ጨዋታ ያከናውናሉ። ኢትዮጵያ መድኖች በመጨረሻዎቹ ሁለት ጨዋታዎች ተከታታይ ሽንፈት ቀምሰዋል፤ ቡድኑ በሜዳ ላይ የሚያሳየው እንቅስቃሴ ለክፉ የሚሰጥ ባይሆንም መሪነቱን ማስጠበቅ ላይ ያለው ስር የሰደደ ድክመት ዋጋ እያስከፈለው ይገኛል። ከ ዘጠነኛ እስከ አስራ ሁለተኛ ሳምንት ድረስ በተከናወኑ አራት ተከታታይ ጨዋታዎች ላይ መሪነቱን ማስጠበቅ ተስኖት ነጥብ ለመጣል የተገደደው ቡድኑ በቀጣይ የተጠቀሰውን ድክመቱን ማረም እንዲሁም በመጨረሻው መርሐ ግብር ላይ የጨዋታውን ውጤት መቀየር የሚችሉ አጋጣሚዎችን ያመከነው የፊት መስመሩ የአፈፃፀም ብቃት ማሻሻል ይጠበቅበታል።

በወላይታ ድቻ በኩል የጉዳት ዜና የሌለ ሲሆን የናትናኤል ናሴሮ እና በተለይ የካርሎስ ዳምጠው ከጉዳት መመለስ ለቡድኑ ትልቁ ዜና ነው። ኢትዮጵያ መድን በበኩሉ አሁንም የቡድን ዜና ለመስጠት ፍቃደኛ አለመሆኑ እና ለመረጃዎች በሩን መዝጋቱ አስገርሟል።

ኢትዮጵያ መድን እና ወላይታ ድቻ ከዚህ ቀደም 8 ጊዜ ተገናኝተዋል፤ ወላይታ ድቻ 3 ሲያሸነፍ ኢትዮጵያ መድን ደግሞ 2 አሸንፎ በ 3 አቻ ተለያይተዋል። ወላይታ ድቻ 10፣ መድን 7 ግቦች በግንኙነታቸው አስቆጥረዋል።