ባህር ዳር ከተማ እና መቐለ 70 እንደርታ ያገናኘው ጨዋታ ግብ ሳይቆጠርበት በአቻ ውጤት ተጠናቋል።

በአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ስታዲዮም በተካሄደ የዕለቱ ብቸኛ ጨዋታ በመጀመሪያው አጋማሽ መቐለ 70 እንደርታዎች የተሻለ እንቅስቃሴ ያደረጉበት ነበር።
በኳስ ቁጥጥርም ሆነ ጫናዎችን በመፍጠር ረገድ ብልጫ የነበራቸው ምዓም አናብስት በአጋማሹ ከተጋጣሚያቸው የተሻለ የማጥቃት እንቅስቃሴም አድርገዋል። ኪቲካ ጅማ በረዥሙ ተሻግሮ ብርሃኑ አዳሙ ያመቻቸውን ኳስ ተጠቅሞ ያደረገው ሙከራ እንዲሁም አሸናፊ ሀፍቱ ከብርሀኑ አዳሙ የተቀበለውን ኳስ ተጠቅሞ ያደረገው እጅግ ለግብ የቀረበ ሙከራም የተሻሉ ለግብ የቀረቡ አጋጣሚዎች ነበሩ። የተሻለ አጀማመር ማድረግ ቢችሉም የኋላ ኋላ መጠነኛ መቀዛቀዝ የተስተዋለባቸው ባህርዳር ከተማዎች በአጋማሹ መገባደጃ ደቂቃዎች ላይ ወርቃማ ዕድል መፍጠር ችለዋል። ሄኖክ ይበልጣል በግሉ ጥረት ያገኛትን ኳስ አክርሮ መቶ የግቡ ቋሚ የመለሰበት አጋጣሚ እንዲሁም ክዋቤና ቧቲንግ የተመለሰችውን ኳስ ተጠቅሞ ያደረጋት ሙከራም የጣና ሞገዶቹን መሪ ለማድረግ የተቃረቡ አጋጣሚዎች ነበሩ።

ባህርዳር ከተማዎች የተሻለ እንቅስቃሴ ያደረጉበት ሁለተኛው አጋማሽ በርከት ባሉ ጥፋቶች ታጅቦ የተካሄደ ነበር።
በአጋማሹ ተሻሽለው በመቅረብ ከተጋጣሚያቸው የተሻለ ጫና የፈጠሩት የጣና ሞገዶቹ ለግብ የቀረቡ ሙከራዎችም ማድረግ ችለዋል። ሄኖክ ይበልጣል በጥሩ መንገድ ወደ ሳጥን ገብቶ አሻግሯት ደስታ ዮሐንስ እንደምንም የመለሳት ኳስ፤ ወንድወሰን በለጠ በሳጥን ውስጥ ሆኖ ያደረጋት ዒላማዋን ያልጠበቀች ሙከራ እንዲሁም ተቀይሮ የገባው ሰቲህ ኦሴ ከሳጥኑ የግራ ክፍል አክርሮ መቷት ለጥቂት የወጣችው ሙከራም የተሻሉ ለግብ የቀረቡ ሙከራዎች ነበሩ። የመጀመሪያው አጋማሽ እንቅስቃሴያቸው ለማስቀጠል የተቸገሩት ምዓም አናብስትም ፍፁም ዓለሙ ከማዕዝን አሻምቷት ደስታ ዮሐንስ በቀጥታ መቶ ፔፔ ሴይዶ በመለሰበት ሙከራ ግብ ለማስቆጠር ተቃርበው ነበር። ጊት ጋትኮች በክዋቤና ቧቲንግ በቡጢ ተመትቶ በዓይኑ አካባቢ በደረሰበት ጉዳት ተቀይሮ መውጣቱ እና ክዋቤና በቢጫ ካርድ ብቻ መታለፉ በሁለተኛው አጋማሽ ትኩረት ከሳቡ አጋጣሚዎች ነበር።

ሁለቱም ቡድኖች እየተፈራረቁ ብልጫ የወሰዱበት ጨዋታም ግብ ሳይቆጠርበት በአቻ ውጤት ተጠናቋል።

