ቅድመ ጨዋታ መረጃዎች | የ16ኛ ሳምንት የሁለተኛ ቀን ጨዋታዎች

ቅድመ ጨዋታ መረጃዎች | የ16ኛ ሳምንት የሁለተኛ ቀን ጨዋታዎች

የ16ኛ ሳምንት የሲቢኢ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ጨዋታዎች ዛሬም ቀጥለው የሚካሄዱ ሲሆን ጨዋታዎቹን የተመለከቱ መረጃዎችንም እነሆ !

ወልዋሎ ዓ/ዩ ከ ሸገር ከተማ

በደረጃ ሰንጠረዡ በታችኛው ክፍል የሚገኙትን ክለቦች በሚያገናኘው ጨዋታ የዕለቱ መርሐግብር ጅማሮውን ያደርጋል።

ወልዋሎ ዓ/ዩዎች እስካሁን በውድድር አመቱ በሊጉ ካደረጓቸው አስራ አምስት ጨዋታዎች በሁለቱ ብቻ በማሸነፍ፣ በስድስቱ ነጥብ ተጋርተው ፤ ሰባት ሽንፈቶችን በማስተናገድ አስራ ሁለት ነጥቦችን ብቻ በመሰብሰብ በደረጃ ሰንጠረዡ አርባ ምንጭ ከተማን ብቻ በመብለጥ 19ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል። ለመጨረሻ ጊዜ ሶስት ነጥብ ካሳኩ 45 ቀናትን ያሳለፉት ቢጫ ለባሾቹ በተከታታይ አራት ጨዋታዎች ነጥብ መጋራት የቻሉ ሲሆን ከጊዜ ጊዜ መከላከል ላይ እያሳዩት ያለው ጥንካሬ እንደ መልካም አጋጣሚ የሚቆጠር ሲሆን ካለፉት ስድስት ጨዋታዎች ሁለት ግቦችን ብቻ ያስቆጠረው የአጥቂ ክፍላቸው ግን አሁንም ትልቅ የቤት ስራ የሚጠብቀው ይሆናል።

በአንጻሩ እንደ ተጋጣሚው ሁሉ ያለፉትን ስድስት ያህል ጨዋታዎች ከድል ጋር የተራራቁት ሸገር ከተማዎች ሶስት ድሎችን፣ ስድስት አቻዎችን እና ስድስት ሽንፈቶችን አስተናግደው አስራ አምስት ነጥብ በመያዝ ከተጋጣሚያቸው በሶስት ደረጃዎች ከፍ ብለው 16ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል። ወጥነት የጎደለው ጨዋታዎችን እያስመለከተን የሚገኘው ቡድኑ እንደ ደካማ ጎን ይቆጠር የነበረው የሚቆጥሩባቸው ግቦች መጠን ባለፉት ጨዋታዎች እየቀነሰ መምጣቱ ጥሩ ጎን ተደርጎ የሚቆጠር ሲሆን ባለፉት ሶስት ሳምንታት ያሳዩትን የአቻ ውጤት ግቦችን በማግኘት ወደ ድል ለመቀየር ከወልዋሎ ዓ/ዩ ጋር ብርቱ ፉክክር ይጠብቃቸዋል።

በወልዋሎዎች በኩል ሰመረ ሀፍታይ ከጉዳት አገግሞ ለዛሬው ጨዋታ ዝግጁ ሲሆን ሙሉዓለም መስፍን እና ስንታየሁ ታምራት ግን በጉዳት ምክንያት ከጨዋታው ውጭ ናቸው። እንዲሁም የያሬድ ከበደ መሰለፍ አጠራጣሪ ነው። በሸገር ከተማ በኩል ሁሉም የቡድን አባላት ለጨዋታው ዝግጁ ናቸው።

ሁለቱ ቡድኖች ለመጀመሪያ ጊዜ በሊጉ መድረክ ጨዋታቸውን የሚያደርጉ ይሆናል።

ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከ አዳማ ከተማ

ያለፉትን ሶስት ጨዋታዎች ከድል ጋር የተራራቁትን ክለቦች የሚያገናኘው መርሐ ግብር “ማን ድል ያደርጋል?” የሚለው ተጠባቂ ያደርገዋል።

በአሰልጣኝ በጸሎት ልዑልሰገድ የሚሰለጥኑት ባንኮች በአስራ ሁለተኛ ሳምንት ኢትዮጵያ መድንን ከመመራት ተነስተው ድል ካደረጉበት ጨዋታ በኋላ ሶስት ነጥብ ማሳካት የተሳናቸው ሲሆን እስካሁን በሊጉ ካደረጓቸው አስራ አምስት ጨዋታዎች ሶስት ድል አድርገው በስምንቱ ነጥብ በመጋራት፤ አራት ሽንፈቶችን አስተናግደው አስራ ሰባት ነጥቦችን በመሰብሰብ 13ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል። ቡድኑ ጋር እንደ ትልቅ ችግር ከሚቆጠሩት ውስጥ ዋነኛ የሆኑት ደካማ የሆነ መከላከል እና ተከታታይ ድሎችን የማያስመዘግብ ድክመት የታየባቸው ሲሆን፤ ጠንካራ በሆነው የአጥቂ ክፍላቸው ጎል የማስቆጠር ብቃታቸውን ተጠቅመው ለአዳማ ከተማ ፈተና እንደሚሆኑ ይጠበቃል።

አዳማ ከተማዎች በበኩላቸው ጠንካራ የሆነ የመከላከል አደረጃጀት ካላቸው ቡድኖች አንዱ ቢሆኑም ፤ አሁን አሁን ግን ግቦችን ማስተናገድ የጀመሩ ሲሆን በውድድር አመቱ ከተቆጠሩባቸው አጠቃላይ ዘጠኝ ግቦች ውስጥ ስድስቱ የተቆጠሩት ባለፉት አምስት ጨዋታዎች ውስጥ ነው። ይህም ተጋጣሚያቸው በሊጉ አስፈሪ የአጥቂ መስመር ያለው ቡድን መሆኑ ለአዳማ መከላከል ላይ ትልቅ የቤት ስራ እንዳለባቸው ጠቋሚ ነው። ካደረጓቸው 15 ጨዋታዎች ሀያ ሰባት ነጥቦችን በመሰብሰብ ሰባተኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡት በአሰልጣኝ ስዩም ከበደ የሚመሩት አዳማዎች የዛሬውን ጨዋታ በደጋፊዎቻቸው ፊት ድል ማድረግ ከቻሉ ወደ መሪዎቹ መጠጋት የሚችሉበትን ዕድል የሚያገኙ ይሆናል።

በአዳማ ከተማ በኩል አምበሉ ሐይደር ሸረፋ በጉዳት ምክንያት የማይኖር ሲሆን ጉዳት ላይ የነበረው አላዛር ሽመልስ ለጨዋታው ዝግጁ መሆኑ ታውቋል።

ቡድኖቹ በሊጉ 35 ጊዜ የተገናኙ ሲሆን የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ 18 ጨዋታ በማሸነፍ ቀዳሚ ነው። አዳማ ከተማ 5 ጨዋታ ሲያሸንፍ በ12 ጨዋታዎች አቻ ተለያይተዋል። ባንክ 58 ጎሎች ሲያስቆጥር አዳማ 31 ጎሎች ማስቆጠር ችሏል።

ምድረ ገነት ሽረ ከ አርባምንጭ ከተማ

ምድረ ገነት ሽረዎች ወደ ሰንጠረዡ መሃል ለመጠጋት አርባምንጭ ከተማዎች ደግሞ የመጀመሪያ ድላቸውን ለማግኘት የሚያደርጉት ትንቅንቅ ተጠባቂ ነው፡፡

በአሰልጣኝ ዳንኤል ፀሐየ እየተመሩ ካደረጓቸው አስራ አምስት ጨዋታዎች አስራ ሰባት ነጥቦችን በመሰብሰብ 14ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡት ምድረ ገነት ሽረዎች በውጤት መዋዠቅ ውስጥ ሆነው የዛሬውን ጨዋታ ያደርጋሉ። ቡድኑ እንደ ኢትዮጵያ ቡና እና ሀዋሳ ከተማ  ያሉ ጠንካራ ክለቦችን ማሸነፍ ቢችልም፣ ቡድኑ ካለፉት አምስት የሊግ ጨዋታዎች ውስጥ በአራቱ ሽንፈት አስተናግዷል። የቡድኑ የአጥቂ መስመር ግቦችን በማስቆጠር ረገድ መሻሻሎችን ቢያሳይም፣ በመከላከል ረገድ የሚታዩ ክፍተቶችን በማረም ወደ አሸናፊነት ለመመለስና በደረጃ ሰንጠረዡ ግርጌ ላለመቀመጥ ይህ የዛሬው ጨዋታ ለሰሜኑ ክለብ የሞት ሽረት ፍልሚያ እንደሚሆን ይጠበቃል።

አርባ ምንጭ ከተማ በአሁኑ ወቅት በሊጉ የደረጃ ሰንጠረዥ ግርጌ ላይ ተቀምጦ የሚገኝ ሲሆን፣ ካደረጋቸው 15 ጨዋታዎች ውስጥ አንድም ድል ባለማስመዝገቡ ከፍተኛ ጫና ውስጥ ይገኛል። ክለቡ በውድድር ዓመቱ 8 ነጥቦችን ብቻ የሰበሰበ ሲሆን፣ በተለይም ግብ በማስቆጠር ረገድ በ15 ጨዋታዎች 5 ግቦችን ብቻ በማስቆጠር በሊጉ ደካማው የአጥቂ መስመር ባለቤት ሆኖ ተመዝግቧል። ካለፉት አምስት የሊግ ጨዋታዎች ውስጥ በሦስቱ ሽንፈት ያስተናገደ ሲሆን፣ የመጀመሪያውን የውድድር ዓመት ድል ለመቀዳጀት እና ከወራጅ ቀጠናው የሚወጣበትን ተስፋ ለማለምለም ቀላል የማይባል ፈተና ከምድረገነት ሽረ ጋር ይጠብቀዋል።

ምድረ ገነት ሽረዎች አዲሱ ተስፋዬን በቅጣት ፍርያት ጣሰውን ደግሞ በጉዳት አያሰልፉም። አርባምንጭ ከተማ ሳሙኤል አስፈሪን ፣አሸናፊ ፊዳን እና በፍቅር ግዛቸውን በጉዳት ሲያጣ ይገዙ ቦጋለ በአምስት ቢጫ ካርድ ከዛሬው ጨዋታ ውጭ ሆኗል።

ሁለቱ ቡድኖች ሁለት ያክል ጊዜ የተገናኙ ሲሆን አዞዎቹ አንድ ጊዜ ሲያሸንፉ በአንዱ ነጥብ ተጋርተዋል። በግንኙነታቸው አርባ ምንጭ 1 ግብ ሲያስቆጥሩ መረባቸውንም አላስደፈሩም።

ሀዋሳ ከተማ ከ ነጌሌ አርሲ

በሊጉ የደረጃ ሰንጠረዥ የላይኛው ክፍል ላይ የሚገኙትን ሁለቱን ቡድኖች የሚያገናኘው የሳምንቱ ተጠባቂ ጨዋታ ነው፡፡

ሀዋሳ ከተማ በአሁኑ ወቅት በ15 ጨዋታዎች 25 ነጥቦችን በመሰብሰብ በደረጃ ሰንጠረዡ 4ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጦ የሚገኝ ሲሆን ክለቡ ካለፉት አምስት የሊግ ጨዋታዎች ውስጥ ሁለቱን በማሸነፍ፣ በሁለቱ አቻ በመውጣት እና በአንዱ ብቻ በመሸነፍ በአንጻራዊነት ጥሩ የሚባል ወቅታዊ አቋም ላይ ይገኛል። ቡድኑ እስካሁን 16 ግቦችን አስቆጥሮ 10 ግቦች ብቻ የተቆጠሩበት በመሆኑ፣ ጠንካራ የመከላከል እና ውጤታማ የማጥቃት መስመር እንዳለው ከውጤቶቹ መረዳት ይቻላል። ይህንን የዛሬውን የስድስት ነጥብ ያክል የሚቆጠረውን ተጠባቂ ጨዋታ ካሸነፈ የደረጃ ለውጥ በማምጣት ከመሪው ጋር ያለውን የነጥብ ልዩነት ለማጥበብ እና የዋንጫ ተፎካካሪነቱን ለማጠናከር ትልቅ እድል ይኖረዋል።

ነገሌ አርሲ በዘንድሮው ሲቢኢ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ አስገራሚ ጉዞ እያደረገ የሚገኝ ክለብ ሲሆን፣ ባደረጋቸው 15 ጨዋታዎች 26 ነጥቦችን በመሰብሰብ በደረጃ ሰንጠረዡ 2ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል። ቡድኑ በተለይ ካለፉት አምስት የሊግ ጨዋታዎች አራቱን በማሸነፍ እና በአንዱ አቻ በመውጣት እጅግ ጠንካራ ወቅታዊ ብቃት ላይ ይገኛል። ክለቡ እስካሁን 17 ግቦችን አስቆጥሮ 10 ግቦች ብቻ የተቆጠሩበት ሲሆን፣ ይህም ከመሪው ሲዳማ ቡና እና መቻል በመቀጠል ጠንካራ የማጥቃት ብቃት ካላቸው ክለቦች አንዱ ያደርገዋል። ነገሌ አርሲ የዛሬውን ጨዋታ የሚያደርገው ካለፉት ሳምንታት ተከታታይ ድሎች በኋላ በመሆኑ ይህንኑ ግስጋሴ በመቀጠል ከሊጉ መሪ ጋር ነጥቡ ለማጥበብ አልሞ እንደሚገባ ይጠበቃል።

በሀዋሳ ከተማ በኩል ሁሉም የቡድን አባላት ለጨዋታው ዝግጁ ሲሆኑ በነጌሌ አርሲ በኩልም በቅርቡ ቀዶ ጥገና ካደረገው አብዱልባሲጥ ከማል ውጪ ሌሎቹ የቡድን አባላት ለጨዋታው ዝግጁ ናቸው።

ሁለቱ ቡድኖች ለመጀመሪያ ጊዜ የሚገናኙ ይሆናል።