ሪፖርት | ኢትዮ ኤሌክትሪክ እና ወላይታ ድቻ ነጥብ ተጋርተዋል

ሪፖርት | ኢትዮ ኤሌክትሪክ እና ወላይታ ድቻ ነጥብ ተጋርተዋል

አዳማ ላይ በተደረገ ብቸኛ ጨዋታ ኢትዮ ኤሌክትሪክ እና ወላይታ ድቻ ያለግብ ተለያይተዋል።

ኢትዮ ኤሌክትሪክ ከ ወላይታ ድቻ

ኢትዮ ኤሌክትሪክን ከወላይታ ድቻ ያገናኘው ብቸኛው የአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርስቲ ሜዳ ጨዋታ ሁለቱ ቡድኖች የግብ ማስቆጠር ፍላጎት ገና ከጅምሩ ያስመለከተን ቢሆንም ቡድኖቹ ወደ ሶስተኛው ሜዳ ክፍል ላይ ሲደርሱ ጠንከር ያለ ሙከራ ለማድረግ ሲቸገሩ አስተውለናል።

ኢትዮ ኤሌክትሪክ የኳስ ቁጥጥር ብልጫ ወስደው በአንድ ለአንድ ቅብብል የተሻሉበትን የመጀመሪያ አጋማሽ ያሳለፉ ሲሆን እምብዛም የጠራ ሙከራ አላደርጉም። ሆኖም ግን ጨዋታው 8ኛ ደቂቃ ላይ ሲደርስ ሀሰን ሁሴን እና አቤል ሀብታሙ ባደረጉት ጥሩ ቅብብል ያገኙትን ኳስ ወደግብነት ቀይረው የነበረ ቢሆንም ከጨዋታው ውጪ ተብሎ የተሻረባቸው እንዲሁም 23 ኛው ደቂቃ ላይ አሸናፊ ጥሩነህ በመስመር በኩል ሳጥን ውስጥ ይዞ ገብቶ ያሻገራትን ኳስ ቢኒያም ገነቱ ላይ ተጨርፋ ወደ ግብነት ሊትቀየር ጥቂት ሲቀራት አዛሪያስ አቤል ከመስመር የመለሳት ፍፁም ለግብ የቀረበች አጋጣሚ ተጠቃሽ ነበሩ።

የጨዋታ ብልጫ የተወሰደባቸው የጦና ንቦች በአጋማሹ ወደ ግብ በመድረስ ሙከራዎችን በማድረግ ረገድ የተሻሉ ነበሩ። 6ኛው ደቂቃ ያሬድ ዳርዛ ሙከራ ድርጎ ዒላማውን ሳይጠብቅ የቀረው ሙከራ፣ ኪዳኔ አሰፋ ከሳጥን ውጪ ሆኖ መትቶ ግብ ጠባቂው በቀላሉ ያዳነበት ሌላኛው ዒላማውን የጠበቀ ሙከራ እና ካርሎስ በሁለት አጋጣሚዎች ያደረጋቸው ሙከራዎች ሲጠቀሱ የቆመ ኳስ መሬት ለመሬት ተጀምሮ የተሻማውን ኳስ በመቀመስ ምት ወደ ግብ አሻግሮ ዒላማውን ያልጠበቀው እንዲሁም የግብ ጠባቂውን መውጣት ተመልክቶ ከራሳቸው ሜዳ ክፍል በረጅሙ መትቶ በግቡ አናት ያለፈባቸው ሌላኛው ሙከራ ነበር። የኢትዮ ኤሌክትሪክን የኳስ ንክኪ ብልጫ እና የወላይታ ድቻን የማጥቃት ፍላጎት የተሻለ እንቅስቃሴ የተመለከትንበት አጋማሹ ግብ ሳይቆጠርበት ተገባዶ ለእረፍት ገብተዋል።

የተሻለ ፉክክር የተደረገበት ሁለተኛው አጋማሽ የጦና ንቦቹ ብልጫ የወሰዱበት ሲሆን በአጋማሹም ከተጋጣሚያቸው የተሻሉ የግብ ዕድሎች ፈጥረዋል።

በተለይም መሳይ ሰለሞን ተቀይሮ ከገባው ቸርነት ኡፋይሳ የተቀበላት በፈጣን ሽግግር ሳጥን የደረሰች ኳስ መቶ የግቡ ቋሚ የመለሰለት ሙከራ እና ቸርነት ኡፋይሳ የተመለሰችውን ኳስ መቶ አሸናፊ ጥላሁን ከመስመር የመለሳት የጦና ንቦቹን ቀዳሚ ለማድረግ የተቃረቡ ሙከራዎች ሲሆኑ ዋና አሰልጣኝ መሳይ ተፈሪ ጨምሮ ሌሎች የቡድኑ አባላት በዚህ ሂደት ላይ ኳስ ሳጥን ውስጥ በእጅ ተነክቷል በሚል ያቀረቡት ቅሬታ እና በዛ ቅፅበት የተፈጠሩ ኩነቶችም የሁለተኛው አጋማሽ ትኩረት ሳቢ ከነበሩ ጉዳዮች አንዱ ነው። ከመጀመሪያው አጋማሽ አንፃር ተቀዛቅዘው የተመለሱት ኢትዮ ኤሌክትሪኮች ግልፅ የግብ ዕድሎች ባልፈጠሩበት አጋማሽ ላይ ወላይታ ድቻዎች ዮናታን ኤልያስ ከቆመ ኳስ ባደረጋት ለግብ የቀረበች ሙከራ እና መልካሙ ቦጋለ በግንባሩ ገጭቶ ባደረገው ሙከራ ግብ ለማስቆጠር ጥረት ቢያደርጉም ጨዋታው ግብ ሳይቆጠርበት ተጠናቋል።