ሪፖርት | ባሕር ዳር ከተማ እና አዳማ ከተማ ድል ተቀዳጅተዋል

ሪፖርት | ባሕር ዳር ከተማ እና አዳማ ከተማ ድል ተቀዳጅተዋል

በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም በተካሄዱ ጨዋታዎች የጣና ሞገዶቹ ነብሮቹን አዳማ ደግሞ መድንን በተመሳሳይ 1ለ0 አሸንፈዋል

ሀዲያ ሆሳዕና ከ ባሕር ዳር ከተማ

በሀዋሳ በተደረገ የሁለተኛ ዙር የመጀመሪያ ጨዋታ በተለይም በማጥቃት እንቅስቃሴው በኩል ባህር ዳር ከተማዎች ከፍተኛ ብልጫ የወሰዱበት ነበር። ገና በ4ኛው ደቂቃ መሳይ አገኘሁ ከቀኝ መስመር አሻግሮት ብሩክ ሰሙ በግንባር ገጭቶት ግብ ጠባቂው በያዘው ኳስ ሙከራቸውን የጀመሩት የጣና ሞገዶቹ 14ኛው ደቂቃ ላይም ወንድወሰን በለጠ እና ዮሐንስ ደረጄ አከታትለው ባደረጓቸው ሙከራዎች የተጋጣሚን ሳጥን መፈተን ችለው ነበር።

19ኛው ደቂቃ ላይ ደስታ ዋሚሾ ካደረገው ዒላማውን ያልጠበቀ ሙከራ ውጪ ወደ ተጋጣሚ ሳጥን ለመድረስ የተቸገሩት ሀዲያዎች 32ኛ ደቂቃ ላይ በአንተነህ ተፈራ ከተደረገባቸው ሙከራ በኋላ 36ኛው ደቂቃ ላይ ሙሴ ካቤላ ሳጥን ውስጥ ኳስ በእጁ በመንካቱ የፍጹም ቅጣት ምት ሲያስተናግዱ ግርማ ዲሳሳም አጋጣሚውን ተጠቅሞ ባህር ዳሮችን መሪ አድርጓል።

ከዕረፍት መልስ በሙከራዎች ረገድ በመጠኑ ተቀዛቅዞ በቀጠለው ጨዋታ በጣና ሞገዶቹ በኩል ተቀይሮ የገባው አናንያ ጌታቸው ከቀኝ መስመር በተሻገረ ኳስ በግንባር ገጭቶ ያደረገው ሙከራ ዒላማውን ሳይጠብቅ ቀርቶበታል።

በጥር የዝውውር መስኮት ፈርሞ የጣና ሞገዶቹን ተቀላቅሎ የመጀመሪያ ጨዋታውን ያደረገው አንተነህ ተፈራ 67ኛ ደቂቃ ላይ ያለቀለት የግብ ዕድል አግኝቶ ሳይጠቀምበት ቀርቷል። ዮሐንስ ደረጄ በግሩም ዕይታ ያመቻቸለትን ኳስ ተጠቅሞ ከሳጥኑ የግራ ክፍል ላይ ሆኖ ያደረገው ሙከራ የግቡን የግራ ቋሚ ታክኮ ወጥቶበታል። ይህም የጨዋታው የተሻለ የመጨረሻ ሙከራ ሆኖ ጨዋታው በባሕር ዳር ከተማ 1ለ0 አሸናፊነት ተጠናቋል።

 

ኢትዮጵያ መድን ከ አዳማ ከተማ

 

ሁለቱን ቡድኖች ባገናኘው ጨዋታ በኳስ እንቅስቃሴ አዳማ ከተማዎች በተሻሉበት የመጀመሪያ አጋማሽ ኢላማውን የጠበቀ ሙከራ በማድረግ ረገድ ኢትዮጵያ መድኖች ቀዳሚ ነበሩ። 13ኛው ደቂቃ ላይ ወገኔ ገዛኸኝ ከቅጣት ምት የሞከረውን ኳስ ግብ ጠባቂው አላዛር ማርቆስ ሲያስወጣበት በአዳማ ከተማ በኩል በአህመድ ሁሴን የግንባር ኳስ እና በአቡበከር ሳኒ የርቀት ምት የግብ ሙከራ ቢያደርጉም ኳሶቹ ኢላማቸውን ሳይጠብቁ ቀርተዋል። በአጋማሹ ይሄ ነው የሚባል ለግብ የቀረቡ ሙከራዎችን ሳንመለከት የመጀመሪያው አጋማሽ ተጠናቋል።

ከዕረፍት መልስ ወደ ሜዳ ሲመለሱ ጥረታቸውን አጠናክረው የቀጠሉት አዳማ ከተማዎች 61ኛው ደቂቃ ላይ የመድኑ ግብ ጠባቂ አቡበከር ኑራ የአዳማው አቡበከር ሳኒ ላይ የሰራውን ጥፋት ተከትሎ ያገኙትን የፍፁም ቅጣት ምት ቢኒያም ዐይተን ወደ ግብ ቀይሮ ቡድኑን መሪ ማድረግ ችሏል።

ከግቡ መቆጠር በኋላ መድኖች ወደ ጨዋታ ሚመልሳቸውን ግብ ለማግኘት ጫናዎችን ፈጥረው መጫወት የቻሉ ሲሆን 62ኛው ደቂቃ ከቀኝ የሜዳ ክፍል ዳዊት አውላቸው ያሻማውን ኳስ አለን ካይዋ ፍፁም ነፃ ሁኖ ቢገጨውም ኢላማውን ሳይጠብቅ ወጥቷል። አዳማ ከተማዎች 68ኛው ደቂቃ ላይ ብዙአየሁ ሰይፈ ከርቀት ሞክሮ ግብ ጠባቂው በመለሰበት እንዲሁም 81ኛው ደቂቃ በመልሶ ማጥቃት ያገኙትን እና ቢንያም ዐይተን ሞክሮ በግቡ ቋሚ በወጣበት አጋጣሚ ለግብ የቀረበ ሙከራዎችን ቢያደርጉም ተጨማሪ ግቦችን ሳንመለከት ጨዋታው በአዳማ 1-0 አሸናፊነት ተጠናቋል።