የሲቢኢ ኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 20ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ዛሬም ሲካሄዱ አርባምንጭ ከተማ ከ ነጌሌ አርሲ፣ ሸገር ከተማ ደግሞ ከ ኢትዮ ኤሌክትሪክ ነጥብ ተጋርተዋል።

አርባ ምንጭ ከተማ ከ ነገሌ አርሲ
ሁለቱን ቡድኖች ባገናኘው ጨዋታ የመጀመሪያው 45 ደቂቃ ላይ በኳስ ቁጥጥር ረገድ አርባ ምንጭ ከተማዎች የተሻሉ ነበሩ። ነገር ግን ነገሌ አርሲዎች በ18ኛው ደቂቃ ግብ ማስቆጠር ችለዋል። የአርባ ምንጩ ግብ ጠባቂ ጽዮን መርድ በአግባቡ ያላራቀውን ኳስ ያገኘው ዳዊት ተፈራ ድንቅ በሆነ አጨራረስ ወደ ግብነት ቀይሮ ነገሌ አርሲዎችን መሪ ማድረግ ችሏል። ከግቡ መቆጠር በኋላ የአቻነት ግብ ለማግኘት ጥረት ማድረግ የቀጠሉት አርባ ምንጭ ከተማዎች በኤፍሬም ታምራት እና በእንዳልካቸው መስፍን አማካኝነት የግብ ሙከራዎችን ማድረግ ቢችሉም ኢላማቸውን ሳይጠብቁ ለጥቂት ወጥቶባቸዋል።
ሁለተኛው አጋማሽ ላይ አርባ ምንጭ ከተማዎች የተጫዋች ቅያሪ በማድረግ ራሳቸውን አሻሽለው ወደ ሜዳ የተመለሱ ሲሆን፣ በ46ኛው ደቂቃ ተቀይሮ የገባው ይድነቃቸው ቃሲም አማካኝነት እጅግ ለግብ የቀረበ ሙከራ ማድረግ ችለው ነበር። በ49ኛው ደቂቃ ተቀይሮ የገባው ይድነቃቸው ቃሲም ያሻገረውን ኳስ በፍቅር ግዛቸው ወደ ግብ ቀይሮ አዞዎቹን አቻ ማድረግ ችሏል።

ነገሌ አርሲዎች ከግቡ መቆጠር በኋላ ጫናዎችን ፈጥረው መጫወት የቻሉ ሲሆን፣ በ60ኛው ደቂቃ እጅግ ለግብ የቀረበ ሙከራ በኢብሳ ፍቃዱና በዳዊት ተፈራ ተከታታይ ሙከራዎችን ማድረግ ቢችሉም፣ በግብ ጠባቂው ጥረት ሁለቱም ሙከራዎች ግብ ከመሆን ድነዋል። 64ኛው ደቂቃ የአርባ ምንጭ ከተማ ተጫዋች የሆነው አበበ ጥላሁን ዳዊት ተፈራ ላይ በሰራው ጥፋት ተከትሎ በቀጥታ ቀይ ካርድ ከሜዳ ተሰናብቷል።
አሁንም ጫናዎችን መፍጠራቸውን የቀጠሉት ነገሌ አርሲዎች በ64ኛው ደቂቃ በሮቦት ሰላሎ አግዳሚው በመለሰበት የግንባር ኳስና እንዲሁም በዘሩባቤል ፈለቀ የርቀት ሙከራ ግብ ለማግኘት ጥረት ቢያደርጉም ሳይሳካላቸው ቀርቶ 1-1 በሆነ አቻ ውጤት ጨዋታው ተጠናቋል።
ሸገር ከተማ ከ ኢትዮ ኤሌክትሪክ
በኳስ ቁጥጥሩ ረገድ ኢትዮ ኤሌክትሪኮች የተሻሉ በነበሩበት አጋማሽ ሁለቱም ቡድኖች ወደ ግብ ደርሰው ሙከራዎችን ማድረግ የቻሉ ሲሆን ኤሌክትሪክዎች አንዋር በድሩ ከርቀት ሞክሮት የግቡ አግዳሚ በመለሰበትና እንዲሁም አቤል ሀብታሙ ሳጥን ውስጥ ተቀብሎ ወደ ግብ የመታውን ኳስ ግብ ጠባቂው ባህሩ በመለሰባቸው አጋጣሚዎች ግብ ለማግኘት ተቃርበው ነበር።
ሸገር ከተማዎች በበኩላቸው በቡልቻ ሹራና በዳዊት ካሳው አማካኝነት እንደዚሁም ግብ ለማግኘት ሙከራዎችን ማድረግ የቻሉ ሲሆን ነገር ግን አጋማሹ ግብ ሳያስመልክተን 0-0 በሆነ አቻ ውጤት ተጠናቋል።

ሁለተኛው አጋማሽ ከመጀመሪያው አጋማሽ በባሰ መልኩ ረዘም ያሉ ደቂቃዎችን የግብ ሙከራዎችን ሳያስመልክተን የቆየ ሲሆን፣ በ72ኛው ደቂቃ ላይ የኤሌክትሪኩ ሀሰን ሁሴን በግንባሩ ከሞከረው ሙከራ ውጪ ምንም ለግብ የቀረበ ይሄ ነው የሚባል የግብ አደጋዎችን ሳንመለከት ጨዋታው 0-0 በሆነ አቻ ውጤት ተጠናቋል።

