ሪፖርት|  መቻል እና ወልዋሎ ድል አድርገዋል

ሪፖርት|  መቻል እና ወልዋሎ ድል አድርገዋል

በአዳማ በተካሄዱ ጨዋታዎች መቻል ኢትዮጵያ ንግድ ባንክን ሁለት ለባዶ ሲያሸንፍ ወልዋሎ ሽረ ምድረ ገነትን አንድ ለባዶ ረቷል

ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከ መቻል

ከስጋት ቀጠናው ለመራቅ እና ወደ መሪዎቹ ለመጠጋት የሚያልሙ ቡድኖችን ያገናኘው የዕለቱ ቀዳሚ ጨዋታ በመጀመሪያው አጋማሽ ሁለቱም ቡድኖች እየተፈራረቁ ብልጫ የወሰዱበት ሲሆን በሙከራዎች ግን የታጀበ አልነበረም። በ14 ኛው ደቂቃ ላይም መቻል አለምብርሀን ይግዛው አመቻችቷት ቻርለስ ሙሴጌ በጥሩ አጨራረስ ባስቆጠራት ግብ መሪ ሆኗል። ከግቡ መቆጠር በኋላ ባንኮች መጠነኛ ብልጫ መውሰድ ቢችሉም የጠሩ የግብ አጋጣሚዎች አልፈጠሩም።

ኢትዮጵያ ንግድ ባንኮች የተሻለ ብልጫ የወሰዱበት ሁለተኛው አጋማሽ የተሻሉ የግብ ሙከራዎች የተደረጉበት ሲሆን ሳይመን ፒተር ከቆመ ኳስ ተሻምታ ግሩም ሐጎስ የመለሳትን ኳስ አግኝቶ መቷት ለጥቂት የወጣችው እንዲሁም ሳይመን ፒተር አመቻችቷት ሳምሶን ቹቹ ከሳጥን ውጭ አክርሮ መቷት በተመሳሳይ ለጥቂት ወደ ውጭ የወጣችው ሙከራም የኢትዮጵያ ንግድ ባንክን አቻ ለማድረግ የተቃረቡ አጋጣሚዎች ናቸው። በሁለተኛው አጋማሽ መጠነኛ ብልጫ የተወሰደባቸው መቻሎችም ኮሊንስ ኮፊ በአዲሱ መገርሳ ስህተት አግኝቶ ካመከናት አጋጣሚ በኋላ በ83ኛው ደቂቃ ላይ አለምብርሀን ይግዛው በ ‘ቮሊ’ ባስቆጠራት ግሩም ግብ መሪነታቸውን አጠናክረዋል። ጨዋታውም ከግቡ በኋላ ለግብ የቀረቡ ሙከራዎች ሳይደረጉበት በመቻል 2 ለ 0 አሸናፊነት ተጠናቋል።

ወልዋሎ ዓ/ዩ ከ ሽረ ምድረ ገነት

ወልዋሎ እና ሽረ ምድረ ገነት ያገናኘው የዕለቱ ሁለተኛ ጨዋታ በመጀመሪያው አጋማሽ ላይ ብርቱ ፉክክር የተደረገበት እና ወልዋሎዎች የተሻለ ብልጫ የወሰዱበት ነበር። ወልዋሎዎች በጨዋታው ጅማሮ ላይ ፍሬው ሰለሞን ከመስመር ተሻምታ ኮንኮኒ ሐፍዝ የጨረፋትን ኳስ መቶ ግብ ጠባቂው በመለሳት ኳስ ሙከራ ካደረጉ በኋላ በ  በ18ኛው ደቂቃ ጨዋታውን መምራት ጀምረዋል። በሽረ ምድረ ገነት ሳጥን ውስጥ ኳስ በእጅ መነካቱን ተከትሎ  የተሰጠውን ፍፁም ቅጣት ምት ኮንኮኒ ሐፍዝ መቶት ሬችሞንድ አይ ከመለሰው በኋላ ጌትነት ተስፋየ የተመለሰውን ኳስ ተጠቅሞ ያስቆጠረው ግብም ቢጫዎቹን መሪ ማድረግ የቻለ ግብ ነው። ከግቡ በኋለ በወልዋሎ በኩል ስምዖንማሩ በግራ መስመር በኩል ዳዊት ገብሩ ያሻገራትን ኳስ ተጠቅሞ መቷት ሪችሞንድ አይ የመለሳት ኳስ በሽረ ምድረ ገነት በኩል ደግሞ አፍቅሮት ሰለሞን አሻምቶት ቢንያም ላንቃሞ በግንባር ከገጨው በኋላ ሙታክብዋ ጆኤል ያዳነው ኳስ ለግብ የቀረቡ ነበሩ።

ሁለተኛው አጋማሽ ሽረ ምድረ ገነቶች የአቻነት ግብ ለማስቆጠር ጫና ፈጥረው የተጫወቱበት እና ይህ ነው የሚባል ለግብ የቀረበ ሙከራ ያልተደረገበት ነበር። ሽረዎች በአጋማሹ ከተጋጣሚያቸው በብዙ ረገድ የተሻለ የማጥቃት እንቅስቃሴ አድርገው በርከት ያሉ የግብ ዕድሎች መፍጠር ቢችሉም ወደ ሙከራነት የተቀየሩት ግን ጥቂት ናቸው። በ60 ኛው ደቂቃ ላይ ግብ ጠባቂያቸው ሪችሞንድ አይ በኮንኮኒ ሀፊዝ ላይ በሰራው ጥፋት በቀጥታ በቀይ ካርድ ከሜዳ ከወጣ በኋላም የቀደመው ብልጫቸው ማስቀጠል አቅቷቸው በሁለቱም ቡድኖች በኩል ይህ ነው የሚባል የጠራ ለግብ የቀረበ ሙከራ ሳይደረግ ጨዋታው በወልዋሎ 1 ለ 0 አሸናፊነት ተጠናቋል።