ሪፖርት| ሲዳማ ቡና ድል ሲቀዳጅ ተከታዩ ሀዋሳ ከተማ ነጥብ ጥሏል

ሪፖርት| ሲዳማ ቡና ድል ሲቀዳጅ ተከታዩ ሀዋሳ ከተማ ነጥብ ጥሏል

በአዳማ በተደረጉ ጨዋታዎች ሲዳማ ቡና ፋሲል ከነማን 1 ለ 0 ሲረታ ወላይታ ድቻ እና ሀዋሳ ከተማ 1 ለ 1 ተለያይተዋል

ሲዳማ ቡና ከ ፋሲል ከነማ

 

በዕለቱ ቀዳሚ ጨዋታ ዐፄዎቹ በ14ኛው ደቂቃ ላይ ግብ ለማስቆጠር እጅግ ተቃርበው ታምራት ኢያሱ ሳይጠቀምበት ቀርቷል። በረከት ግዛው ከመሃል የሰነጠቀውን ኳስ ያገኘው አጥቂው ከግብ ጠባቂ ጋር ቢገናኝም ግብ ጠባቂው ኢማኑኤል ካል መልሶበታል። ሲዳማዎች የጨዋታውን የመጀመሪያ ለግብ የቀረበ ሙከራ 26ኛው ደቂቃ ላይ ሲያደርጉ ብለስ ናጎ የግብ ጠባቂውን መውጣት ተመልክቶ ከመሃል ሜዳ በረጅም የሞከረው ኳስ ለጥቂት ወጥቶበታል። 38ኛው ደቂቃ ላይ የሲዳማው ፍቅረኢየሱስ ከሴኮንዶች በኋላ ደግሞ የፋሲሉ በረከት ግዛው ካደረጓቸው ዒላማቸውን ያልጠበቁ ሙከራዎች በኋላ ጨዋታው ወደ ዕረፍት አምርቷል።

ከዕረፍት መልስም በተመሳሳይ ፈጣን አጀማመር ያደረጉት ፋሲሎች 49ኛው ደቂቃ ላይ የተሻለ የግብ ዕድል ፈጥረው ቃልኪዳን ዘላለም ከግራ መስመር ያሻገረውን ኳስ ያገኘው ታምራት ኢያሱ በግንባሩ ጨርፎ ያደረገውን ሙከራ የግቡ የላይ አግዳሚ መልሶበታል። በጋለ የጨዋታ ስሜት ተደጋጋሚ ማጥቃት የቀጠሉት ዐፄዎቹ 52ኛው ደቂቃ ላይ ተጨማሪ ዕድል ፈጥረው ታምራት ኢያሱ ከቀኝ መስመር የቀነሰውን ኳስ ያገኘው በረከት ግዛው ያደረገውን ሙከራ ግብ ጠባቂው ኢማኑኤል ካል አስወጥቶበታል።

ቀስ በቀስ ወደ ጨዋታው የመጡት ሲዳማዎች 63ኛው ደቂቃ ላይ ለግብ የቀረበ ሙከራ ሲያደርጉ ፍቅረኢየሱስ ተወልደብርሃን ከቅጣት ምት ያደረገውን ግሩም ሙከራ ሞይስ ፖዎቲ አስወጥቶበታል። ጨዋታው ሊጠናቀቅ አራት ደቂቃዎች ተጨምረው 90+2ኛው ደቂቃ ላይ ሲዳማዎች የማሸነፊያ ግብ አግኝተዋል። መስፍን ታፈሰ ከግራ መስመር ያሻገረውን ኳስ ብለሥ ናጎ መረብ ላይ አሳርፎታል።

ወላይታ ድቻ ከ ሀዋሳ ከተማ

 

በምሽቱ ጨዋታ ሐይቆቹ 18ኛው ደቂቃ ላይ የመጀመሪያውን ንጽህ የግብ ዕድል ፈጥረው ከግብ ጠባቂው ሰይድ ሀብታሙ የተነሳውን ኳስ ተባረክ ሄፋሞ ከቀኝ መስመር ወደ ውስጥ ሲቀንሰው ኳሱን ያገኘው ጌታነህ ከበደ በግራ እግሩ ያደረገው ሙከራ ለጥቂት በግቡ የግራ ቋሚ በኩል ወጥቶበታል።
ግብ በማስቆጠሩ ረገድ የጦና ንቦቹ ቀዳሚ ነበሩ። 34ኛው ደቂቃ ላይ ቴዎድሮስ ኃይለማርያም ከሳጥኑ የግራ ክፍል ወደ ውስጥ የቀነሰውን ኳስ ያገኘው ቴዎድሮስ ታፈሰ ግብ አድርጎታል። ጨዋታው በድቻ መሪነት ወደ ዕረፍት ሊያመራ ተቃርቦ የነበር ቢሆንም 45+1ኛው ደቂቃ ላይ ሽመልስ በቀለ ከማዕዘን ያሻማውን ኳስ ብሩክ ታደለ መረብ ላይ አሳርፎታ ሐይቆቹን ወደ አቻነት መልሷል።

ከዕረፍት መልስ የተሻለውን የመጀመሪያ የግብ ሙከራ ሀዋሳዎች ሲያደርጉ 62ኛው ደቂቃ ላይ ሽመልስ በቀለ ከሳጥን አጠገብ የመታውን ኳስ ግብ ጠባቂው አስወጥቶበታል። 68ኛው ደቂቃ ላይ በተመሳሳይ የሀዋሳው ብሩክ ታደለ የግብ ጠባቂውን መውጣት ተመልክቶ ከርቀት ያደረገውኝ ሙከራ ራሱ ግብ ጠባቂው መልሶበታል። ከዚህ ሙከራ በኋላ ተጠቃሽ ለግብ የቀረበ ሙከራ ሳይደረግ ጨዋታው 1-1 ተጠናቋል።