22ኛው ሳምንት የሲቢኢ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ዛሬ በሚደረጉ ሁለት ጨዋታዎች ይጠናቀቃል፤ ጨዋታዎቹን የተመለከቱ መረጃዎችም እንደሚከተለው አቅርበንላችኋል
መቐለ 70 እንደርታ ከ ድሬዳዋ ከተማ
ሀያ ሁለት ነጥቦች ሰብስበው 19ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡት መቐለ 70 እንደርታዎች ከወራጅ ቀጠናው ለመውጣት የሚያደርጉትን ጉዞ ለማሳለጥ በሦስት ነጥብ እና አራት ደረጃዎች ከፍ ብለው ከተቀመጡት ድሬዳዋ ከተማዎች ጋር ይፋለማሉ።
ሁለተኛውን ዙር ሽረ ምድረ ገነትን አንድ ለባዶ በማሸነፍ ጀምረው በመጨረሻው ጨዋታ ከመቻል ጋር ነጥብ የተጋሩት ምዓም አናብስት ዳግም ወደ ድል መንገድ ተመልሰው ከወራጅ ቀጠናው የሚወጡበትን ዕድል ለማመቻቸት በመከላከሉ ረገድ ያላቸውን ጥንካሬ ማስቀጠል እንዲሁም ከቅርብ ሳምንታት ወዲህ ውስን መቀዛቀዝ የሚታይበትን የማጥቃት አጨዋወት በብዙ ረገድ ማሻሻል ይኖርባቸዋል። ከዚህ ቀደም በጨዋታዎች ጥቂት የማይባሉ ዕድሎችን እየፈጠረ ሆኖም ከፍተኛ የሆነ የግብ አጋጣሚዎችን የመጠቀም ክፍተት የነበረበት ቡድኑ በቅርብ ሳምንታት ግን በተለይም ፍፁም ዓለሙ ባልተሰለፈባቸው ጨዋታዎች በቂ ዕድሎችን መፍጠር ተስኖታል። የተጠቀሰውን ችግር መቅረፍን የቡድኑ ቀዳሚ ስራ መሆን ይጠበቅበታል።
በሀያ አምስት ነጥቦች 13ኛ ደረጃ ላይ የሚገኙት ድሬዳዋ ከተማዎች ካሉበት አስጊ ቀጠና እፎይታ የሚሰጣቸውን ድል ለማግኘት በሦስት ነጥብ አንሶ ወራጅ ቀጠናው ላይ ከተቀመጠው መቐለ 70 እንደርታ ጋር ወሳኝ ጨዋታ ያከናውናሉ።
በመጨረሻው መርሐ ግብር በወላይታ ድቻ ሽንፈት ያስተናገዱትና በሁለተኛው ዙር ድል ማድረግ ያልቻሉት ብርቱካናማዎቹ በቅርብ ሳምንታት ባስመዘገቧቸው ተደጋጋሚ የአቻ ውጤቶች ደረጃቸው አሽቆልቁሎ ከወራጅ ቀጠናው አፋፍ ለመቀመጥ ተገደዋል። ከመጨረሻዎቹ 10 ጨዋታዎች ውስጥ 1 ድል አድርጎ 3 ሽንፈት እና 6 የአቻ ውጤቶች ያስመዘገበው ቡድኑ ከዚህ አካሄድ ለመውጣት በብዙ ረገድ መሻሻል ይኖርበታል። በተለይም ባለፉት 10 ጨዋታዎች ውስጥ በ 7ቱ ኳስና መረብ ሳያገናኝ የወጣው እና በቅርብ ሳምንታት መጠነኛ መሻሻል የታየበት የማጥቃት አጨዋወት ጥራት መጨመር የቡድኑ ቀዳሚ ስራ መሆን ይገባል።
መቐለ 70 እንደርታዎች በዛሬው ጨዋታ በጉዳትም ሆነ በቅጣት የሚያጡት ተጫዋች የለም። ድሬዳዋ ከተማ ያሬድ ታደሠ፣ ሬድዋን ሸረፋ፣ መሐመድኑር ናስር፣ አድናን መኪ እና አያልኔ እንድሪስን በጉዳት አስቻለው ታመነ እና ድልአዲስ ገብሬን ደግሞ በቅጣት ምክንያት ዛሬ አያገኝም።
ሁለቱ ቡድኖች በሊጉ እስከ አሁን 8 ጊዜ ሲገናኙ ምዓም አናብስት 4 ጊዜ በማሸነፍ ብልጫውን ሲይዙ ብርቱካናማዎቹ በአንፃሩ 3 ድል አድርገው አንድ ጨዋታ ነጥብ ተጋርተዋል።በግንኙነታቸውም ሞዓም አናብስቱ 11 ብርቱካናማዎቹ በበኩላቸው 9 ጎሎችን መረብ ላይ አሳርፈዋል።

ሀዲያ ሆሳዕና ከ አዳማ ከተማ
በሀያ ሰባት ነጥቦች 10ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡት ሀድያ ሆሳዕናዎች የሁለት ደረጃዎች መሻሻል የሚያስገኝላቸውን ድል ለማግኘት ከአዳማ ከተማ ጋር ይፋለማሉ። ከአስራ ሰባተኛ እስከ አስራ ዘጠነኛው ሳምንት ድረስ በተካሄዱ ሦስት ጨዋታዎች ሁለት ሽንፈቶች እና አንድ የአቻ ውጤት በማስመዝገብ ማግኘት ከሚገባቸው ዘጠኝ ነጥቦች አንዱን ብቻ በማሳካት ደካማ ጉዞ ካደረጉ በኋላ ከመጨረሻዎቹ ሦስት ጨዋታዎች ሁለት አሸንፈው በአንዱ ሽንፈት ያስተናገዱት ነብሮቹ ከስምንት የጨዋታ ሳምንታት በኋላ ሁለት ተከታታይ ድል ለማግኘት ወደ ሜዳ ይገባሉ። ከጠንካራ ተጋጣሚ ጋር በሚፋለሙበት የዛሬው ጨዋታ ሙሉ ነጥብ ይዞ ለመውጣትም ባለፉት ስድስት ጨዋታዎች ስድስት ግቦችን ያስተናገደው የኋላ ክፍላቸውን ማጠናከር ይጠበቅባቸዋል።
በሰላሣ ሁለት ነጥብ 6ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡት አዳማ ከተማዎች ሁለት ደረጃዎችን አሻሽለው 4ኛ ደረጃን ለመቆናጠጥ ወደ ጨዋታው ይቀርባሉ።
በድራማዊ ክስተቶች ታጅቦ በተካሄደው እና ስድስት ግቦች በተቆጠሩበት የመጨረሻው ሳምንት መርሐ ግብር ላይ ከሸገር ከተማ ጋር ነጥብ የተጋሩት አዳማዎች በቅርብ ሳምንታት ተከታታይ የአቻ ውጤቶችን ማስመዝገባቸው ተከትሎ ደረጃቸውን ማሻሻል አልቻሉም። ከመጨረሻዎቹ አምስት ጨዋታዎች በሦስቱ ነጥብ ተጋርቶ የወጣው ቡድኑ ከዚህ አካሄዱ ለመላቀቅ ባለፉት ሦስት ጨዋታዎች አምስት ግቦችን ያስተናገደውና በወትሮ ጥንካሬው የማይገኘውን የተከላካይ ክፍሉ ማሻሻል ይጠበቅበታል።
ሁለቱ ቡድኖች ከዚህ ቀደም 13 ጊዜ ተገናኝተው ሀዲያ ሆሳዕና 5 ጊዜ፤ አዳማ ከተማ ደግሞ 4 ጊዜ ሲያሸነፉ 4 ጨዋታዎች አቻ ተጠናቀዋል። አዳማ 12 ሀዲያ ደግሞ 14 ግቦችን አስቆጥረዋል።

