መረጃዎች | የ23ኛ ሳምንት የመጀመሪያ ቀን ጨዋታዎች

መረጃዎች | የ23ኛ ሳምንት የመጀመሪያ ቀን ጨዋታዎች

በጥሩ ፉክክር ታጅቦ የቀጠለው ፕሪሚየር ሊጉ ዛሬ በ23ኛ ሳምንት መርሐግብር ሲመለስ በዕለቱ ጨዋታዎች ዙሪያ ተከታዩን ቅድመ ጨዋታ መረጃ አዘጋጅተናል።

 

መቻል ከ ወልዋሎ ዓ/ዩ

በደረጃ ሰንጠረዡ ከላይ ወደ ታች እና ከታች ወደ ላይ 4ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡ ቡድኖችን የሚያገናኘው ጨዋታ የዕለቱ ቀዳሚ መርሐግብር
ነው።

ከአራት ጨዋታዎች በኋላ ባለፈው ሳምንት ኢትዮጵያ ንግድ ባንክን በማሸነፍ ወደ ድል የተመለሱት መቻሎች በዕለቱ የነበራቸው የጨዋታ አቀራረብ የሚያስደንቅ ነበር። በግብ ሙከራዎች በኩል ብልጫ ቢወሰድባቸውም ካገኟቸው ጥቂት የግብ ዕድሎች ሁለቱን አስቆጥረው ድል መቀዳጀታቸው እና ውጤቱን ማስጠበቃቸው ዘግይተውም ቢሆን ከፍተኛ ትኩረት ወደተሞላበት ሂደት እየገቡ እንደሆነ ጠቋሚ ሊሆን ይችላል።

ተከታታይ ሁለተኛ ድል ያሳኩት ወልዋሎዎች ባገኟቸው ስድስት ነጥቦች በፍጥነት የደረጃ መሻሻል አድርገው በግብ ልዩነት ተበልጠው 17ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡ ሲሆን በዛሬው ጨዋታ አንድ ነጥብ ብቻ ማሳካት ወደ 14ኛ ሦስት ነጥብ ማሳካት ደግሞ ወደ 12ኛ ደረጃ ከፍ ያደርጋቸዋል። ካለፉት 11 ጨዋታዎች በአንዱ ብቻ የተሸነፉት ቢጫዎቹ 7ቱን አቻ መለያየታቸው ከወራጅ ቀጠናው እንዳይወጡ አድርጓቸው ነበር። ሆኖም የአሸናፊነት መንፈሳቸውን ለማስቀጠል ዛሬ ጠንካራ ፍልሚያ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል።

በፕሪሚየር ሊጉ 7 ጊዜ የተገናኙት ሁለቱም ክለቦች መቻል 4 ጊዜ ድል ሲቀናው ወልዋሎ 2 ጊዜ አሸንፏል፤ በአንዱ ደሞ ነጥብ ተጋርተዋል።  በጨዋታዎቹም መቻል 8 ወልዋሎ ደግሞ 3 ግቦች አስቆጥረዋል።


ሸገር ከተማ ከ ቅዱስ ጊዮርጊስ

 

በአንድ ነጥብ ብቻ ተበላልጠው 16ኛ እና 13ኛ ደረጃ ላይ የሚገኙት ሸገር እና ቅዱስ ጊዮርጊስ ወደ ከራቃቸው ድል ጋር ለመታረቅ ወሳኝ ጨዋታ ያደርጋሉ።

ከመጨረሻ 10 ጨዋታዎች 9 አቻ ተለያይተው ከአዳማ እና ባህር ዳር እኩል ከፍተኛውን የአቻ ውጤት (12)  ያስመዘገቡት ሸገር ከተማዎች በበርካታ ጨዋታዎች ቀድመው ጎሎችን ቢያስቆጥሩም ውጤት ማስጠበቅ አለመቻላቸው በወራጅ ቀጠናው ዙሪያ እንዳይጠፉ አድርጓቸዋል። በስነልቦና ረገድ ቡድኑን ማዘጋጀት ደግሞ የአሰልጣኝ ቡድኑ ከፍ ያለ ኃላፊነት ነው።

ካለፉት 13 ጨዋታዎች በአንዱ ብቻ ያሸነፈው ቅዱስ ጊዮርጊስ ሜዳ ውስጥም ሆነ ከሜዳ ውጪ ፈተናው አይሎበታል። በከፍተኛ የፋይናንስ ችግር ምክንያት ከአቤል ያለው እና አፈወርቅ ኃይሉ እንዲሁም ባልታወቀ ምክንያት ከቢኒያም ፍቅሩ ጋር የተለያዩት ፈረሰኞቹ በዘመናቸው ካዩዋቸው ጥቂት ፈታኝ ጊዜዎች መካከል አንዱ በሆነው ወቅት ላይ እንደመገኘታቸው ይህንን በምን መንገድ ይሻገሩታል የሚለው የሚጠበቅ ነው።

በሸገር ከተማ በኩል ሁሉም የቡድኑ አባላት ለጨዋታው ዝግጁ ሲሆኑ በጊዮርጊስ በኩል ጳውሎስ ከንቲባ እና አዲሱ አቱላ በጉዳት ምክንያት የማይኖሩ ሲሆን በለቀቁ ተጫዋቾች ምትክ እንየው ስለሺ ፣ ብሩክ እና አሚር ከታችኛው ቡድን እንዲያድጉ ተደርገዋል።

* በመጀመሪያው ዙር ባደረጉት ጨዋታ ሸገር ከተማ 1ለ0 ማሸነፉ ይታወሳል።

 

ኢትዮ ኤሌክትሪክ ከ ኢትዮጵያ ቡና

 

በሁለት ነጥቦች ተበላልጠው 7ኛ እና 8ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡት ኤሌክትሪክ እና ኢትዮጵያ ቡና ድላቸውን ለማስቀጠል እርስበርስ ይፋለማሉ።

ከስድስት ጨዋታዎች በኋላ አርባምንጭ ከተማን 4ለ1 በማሸነፍ ወደ ድል የተመለሱት ኤሌክትሪኮች ለአምስት ጨዋታዎች ምንም ግብ ባለማስቆጠር በራስ መተማመኑን አጥቶ የነበረው የቡድኑ የማጥቃት ኃይል በውድድር ዓመቱ ለመጀመሪያ ጊዜ በአንድ ጨዋታ አራት ግቦችን ማስቆጠር መቻሉ የሚፈጥርለት መነሳሳት ትልቅ ነው። ሆኖም ተጋጣሚያቸው በመጨረሻ ሦስት ጨዋታዎች ግብ ያላስተናገደ መሆኑ ጠንካራ ፉክክር እንዲጠብቃቸው ሊያደርግ ይችላል።

ተከታታይ ሦስት ጨዋታዎችን ያሸነፉት ኢትዮጵያ ቡናዎች በጥሩ ወቅታዊ ብቃት ላይ ይገኛሉ። ምንም ግብ ሳይቆጠርባቸው ሦስቱንም ፈታኝ ጨዋታዎች በድል መወጣታቸው በሁለተኛው ዙር ኮስታራ ተፎካካሪ ሆነው እንደቀረቡ ማሳያ ነው። በመጀመሪያው ዙር ውጥረት ላይ በነበሩበት ወቅት በዛሬ ተጋጣሚያቸው የተሸፉት ቡናማዎቹ ያንን መጥፎ ትውስታ ዛሬ አራተኛ ተከታታይ ድል አሳክቶ ለመርሳት ብርቱ ፉክክር ያደርጋሉ ተብሎ ይጠበቃል።

ሁለቱ ቡድኖች በሊጉ ለ45 ጊዜያት ተገናኝተው ቡና 24 በማሸነፍ ከፍተኛ የበላይነት ይዟል። 11 ጨዋታ ኤሌክትሪክ ሲያሸንፍ 10 ጊዜ አቻ ተለያይተዋል። ቡና 74 ሲያስቆጥር ኤሌክትሪክ 46 አስቆጥሯል።
 

ወላይታ ድቻ ከ ሲዳማ ቡና

 

ከ9 ድል አልባ ሳምንታት በኋላ ተከታታይ ሁለት ድሎችን አሳክተው የነበሩት የጦና ንቦቹ በመጨረሻው ሳምንት ከሀዋሳ ጋር ነጥብ ተጋርተዋል። ከሊጉ መሪዎች ጋር በተከታታይ መፋለም ግድ የሆነባለው ድቻዎች በዛሬው ጨዋታ የሊጉ መሪ ላይ የሚያስመዘግበው ውጤት የሚፈጥርለት በራስ መተማመን ቀላል አይደለም።

ከአራት ጨዋታዎች በኋላ ተከታታይ ሁለት ድሎችን ያሳኩት ሲዳማዎች ከተደጋጋሚ ማመንታት በኋላ በስተመጨረሻም አጋጣሚያቸውን ተጠቅመው ሊጉን በአምስት ነጥቦች ልዩነት መምራት ጀምረዋል። በጨዋታዎቹ በተሻለ ዝግጅት የሚቀርቡት ሲዳማዎች ሱራፌል ዳኛቸው እና አቤል ያለውን በአጋማሹ የዝውውር መስኮት ማስፈረማቸው በተለይም ሦስተኛው የሜዳ ክፍል ላይ ላሉበት ክፍተቶች ዋነኛ መፍትሔ ይሆናሉ ተብሎ ይጠበቃል።