ሪፖርት | ሁለቱ የመዲናዋ ክለቦች ድል ቀንቷቸዋል

ሪፖርት | ሁለቱ የመዲናዋ ክለቦች ድል ቀንቷቸዋል

ፈረሰኞቹ በሁለቱም አጋማሾች ጭማሪ ደቂቃዎች ባስቆጠሯቸው ግቦች ሀዲያ ሆሳዕናን ሲያሸንፉ ቡናማዎቹ በቢኒያም ጌታቸው ድንቅ ግብ ኢትዮጵያ መድንን ድል አድርገዋል።

ሀዲያ ሆሳዕና ከ ቅዱስ ጊዮርጊስ

ቅዱስ ጊዮርጊሶች ጅጉን በልጫ በወሰዱበት እና ስምንት ያክል ኢላማቸውን የጠበቁ የግብ ሙከራዎችን ባደረጉበት የመጀመሪያ አጋማሽ 11ኛው ደቂቃ ላይ በፍፁም ጥላሁን እንዲሁም 27ኛው ደቂቃ ላይ በፀጋ ከድር አማካኝነት ለግብ የቀረቡ ሙከራዎችን ቢያደርጉም በግብ ጠባቂው ኦውሱ እንድሪውስ እና በግቡ ቋሚ ትብብር ግብ ከመሆን ታድጓቸዋል።

የአጋማሹ መደበኛ የጨዋታ ሰዓት ተጠናቆ በተሰጡት ተጨማሪ ደቂቃዎች 45+3 ላይ የተጋጣሚን የግብ ክልል በተደጋጋሚ ሲያንኳኩ የነበሩት ቅዱስ ጊዮርጊሶች 45+3 ላይ በጥሩ ቅብብል ወደ ሳጥን ይዘውት የገቡትን እና ሀብታሙ ጉልላት ያቀበለውን ኳስ የአብስራ ጎሳዬ የሳጥኑ ጠርዝ ላይ በመሆን የመታውን ኳስ ወደ ግብነት ቀይሮ ቡድኑን መሪ በማድረግ ወደ መልበሻ ክፍል አምርተዋል።

ሁለተኛው አጋማሽ ላይ ቅዱስ ጊዮርጊሶች በፀጋ ከድር እና በተገኑ ተሾመ የግብ ሙከራዎችን ያደረጉ ቢሆንም 63ኛው ደቂቃ ላይ የሀድያ ተጫዋቾች በአንድ ሁለት ቅብብል ይዘውት በመግባት ተመስገን ብርሃኑ ያሻገረውን ኳስ  የአብስራ ጎሳየ ለማውጣት ሲሞክር ወደራሱ ግብ አስቆጥሮ  ሀዲያ ሆሳዕናን አቻ አድርጓል። ይህም በአንድ ጨዋታ ለራሱ ክለብ እንዲሁም ለተጋጣሚ በአንድ ጊዜ ግብ ያስቆጠረ ተጫዋች ያደርገዋል።

መደበኛው የጨዋታ ሰዓት ተጠናቆ በተሰጡት የባከኑ ጭማሪ ደቂቃዎች ቅዱስ ጊዮርጊሶች ቀይረው ባስገቧቸው ተጫዋቾች ሚና ጎል ማስቆጠር ችለዋል። 90+3 ላይ ብሩክ አለማየሁ አመቻችቶ ያቀበለውን ኳስ ፉአድ አብደላ ድንቅ በሆነ ብቃት ተጫዋቾችን አታሎ በማለፍ ግብ አስቆጥሮ ቡድኑን የማታ ማታ አሸናፊ ማድረግ ችሏል። ይህንንም ተከትሎ ቅዱስ ጊዮርጊስ በሁለቱም አጋማሾች ተጨማሪ ደቂቃዎች ላይ ባስቆጠሯቸው ግቦች 2-1 በሆነ ውጤት በማሸነፍ ከዘጠኝ ሳምንታት በኋላ ከናፈቃቸው ድል ጋር ታርቀዋል።

ኢትዮጵያ መድን ከ ኢትዮጵያ ቡና

በኳስ ቁጥጥር ረገድ ሁለቱም ቡድኖች ተመጣጣኝ የሆነ ብልጫን ባስመለከቱበት የመጀመሪያው አጋማሽ ኢትዮጵያ ቡናዎች ወደ ሜዳው ሶስተኛ ክፍል በመድረስ የግብ እድሎችን በመፍጠር ረገድ የተሻሉ ነበሩ ነገር ግን ጥራት ያላቸውን የግብ እድሎች ፈጥረው ይሄ ነው የሚባል ለግብ የቀረበ ሙከራን ማስመመልከት እምብዛም አልነበሩም። በተቃራኒው ኢትዮጵያ መድኖች መከላከልን ምርጫቸው በማድረግ ከመስመር የሚነሱ ኳሶችን እንደማጥቃት ኢላማ ሲጠቀሙ ተስተውለናል ነገር ግን አጋማሹ በሁለቱም ቡድኖች በኩል ግብ ሳያስመለክተን ዜሮ ለዜሮ በሆነ ውጤት ተጠናቋል።

ሁለተኛው አጋማሽ እንደተጀመረ 47ኛው ደቂቃ ላይ ኢትዮጵያ ቡናዎች መሪ መሆን የቻሉበትን ግብ አስቆጥረዋል። ኤርምያስ ሹምበዛ ያቀበለውን ኳስ ቢንያም ጌታቸው ከግቡ ርቀት ላይ ሆኖ አክርሮ የመታው ኳስ ድንቅ በሆነ አጨራረስ መረብ ጋር ተገናኝቶ ቡናማዎቹን መሪ መሆን ችሏል።

ከዕረፍት መልስ በሙከራዎች የታጀበ በነበረው ጨዋታ የኢትዮጵያ ቡናው አቡበከር አዳሙ ያሻማውን ኳስ የመድን ተከላካይ የሆነው ንጋቱ ገ/ ስላሴ ለማውጣት ሲሞክር ወደራሱ ግብ ሞክሮት እንደምንም ብሎ ግብ ጠባቂው አቡበከር ኑራ በጥሩ ቅልጥፍና መልሶታል።

የአቻነት ግባቸውን ለማግኘት እጅግ ጫናዎችን ፈጥረው መጫወት የቀጠሉት ኢትዮጵያ መድኖች 65ኛው ደቂቃ ላይ በብሩክ በላቸው እንዲሁም 75ኛው ደቂቃ ላይ በአለን ካይዋ በኩል እንዲሁም 78ኛው ደቂቃ ላይ በአልፍሬድ ኩሩንዚዛ እና በ80ኛው ደቂቃ ላይ በበረከት ካሌብ አማካኝነት እጅግ ለግብ የቀረቡ ሙከራዎችን ማድረግ ቢችሉም በ ግብ ጠባቂው እንዲሁም በግቡ ቋሚ ከልካይነት ግብ እንዳያገኙ መሰናክል ሆኖባቸዋል። ጨዋታውም በኢትዮጵያ ቡና 1 ለ 0 አሸናፊነት ተጠናቋል።