በ25ኛው ሳምንት የሁለተኛ ቀን ጨዋታዎች ወላይታ ድቻ እና ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ 0ለ0 ሲለያዩ ሲዳማ ቡና በአቤል ያለው ብቸኛ ግብ መቐለ 70 እንደርታን አሸንፏል።

ወላይታ ድቻ ከ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ
በጥሩ ወቅታዊ ብቃት የሚገኙ ቡድኖችን ያገናኘው ጨዋታ በመጀመሪያው አጋማሽ ላይ ጥሩ ፉክክር የተደረገበት ቢሆንም በሙከራዎች የታጀበ አልነበረም። በአጋማሹም በመልሶ ማጥቃት ዕድሎችን ለመፍጠር ጥረት ያደረጉት ወላይታ ድቻዎች የተሻሉ ሙከራዎች ማድረግ ችለዋል። ዮናታን ኤልያስ አመቻችቷት በሳጥኑ ቀኝ ክፍል የነበረው ኪዳኔ አሰፋ በደረቱ አብርዶ ያደረጋት ሙከራ እንዲሁም ሳሊፉ ኢብራሂም በንግድ ባንክ ተጫዋች ስህተት አግኝቶ ለካርሎስ ዳምጠው ካቀበለው በኋላ አጥቂው አመቻችቷት ኪዳኔ አሰፋ ያደረጋት እና በግብ ጠባቂው ጥረት ወደ ውጭ የወጣችው ሙከራ በአጋማሹ የተደረጉ የተሻሉ ሙከራዎች ናቸው። ንግድ ባንኮች በአጋማሹ የተሻለ የኳስ ቁጥጥር ድርሻ ቢኖራቸውም ይህ ነው የሚባል ለግብ የቀረበ ሙከራ ሳያደርጉ አንድ ዒላማውን የጠበቀ ሙከራ ብቻ የተደረገበት አጋማሽ ተገባዷል።

በከፍተኛ ዝናብ ታጅቦ የተካሄደው ሁለተኛው አጋማሽ ከመጀመሪያው የጨዋታ ምዕራፍ የተሻሉ ሙከራዎች የተደረጉበት ሲሆን የጦና ንቦቹ በዚህኛው አጋማሽም ሙከራዎች በማድረግ ረገድ የተሻሉ ነበሩ። ኪዳኔ አሰፋ ከሳጥኑ ጠርዝ መቶት ግብ ጠባቂው ያዳነው እንዲሁም አማካዩ በድጋሜ በሌላ አጋጣሚ አክርሮ መቶት ለጥቂት የወጣው ሙከራም ለግብ የቀረቡ ሙከራዎች ነበሩ። በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በኩልም ሳምሶን ቹቹ ከሳጥን ውጭ በግሩም ሁኔታ አክርሮ መቶት ግብ ጠባቂው በጥሩ ብቃት ያወጣው ድንቅ ሙከራ ይጠቀሳል።

በሁለቱም አጋማሾች ከተጋጣሚያቸው በተሻለ አኳኋን የግብ አጋጣሚዎች የፈጠሩት ወላይታ ድቻዎች ቸርነት ኡፋይሳ ከርቀት አክርሮ በመምታት ባደረገው ሙከራ እንዲሁም በጨዋታው መገባደጃ ላይ ብሩክ ኤልያስ ከመስመር የተሻገረለትን ኳስ ተጠቅሞ በሞከረው ዒላማውን ያልጠበቀ ሙከራ ግብ ለማስቆጠር ጥረት አድርገዋል። ጥሩ ፉክክር የተደረገበት ጨዋታም ግብ ሳይቆጠርበት በአቻ ውጤት ተጠናቋል።
መቐለ 70 እንደርታ ከ ሲዳማ ቡና
በሊጉ አናት የተቀመጠ እና በወራጅ ቀጠናው የሚገኝ ቡድን ያፋለመው የዕለቱ ሁለተኛ ጨዋታ በመጀመሪያው አጋማሽ ሲዳማ ቡናዎች ፍፁም የበላይነት የወሰዱበት ነበር። በአጋማሹ በሁሉም መለኪያዎች ብልጫ የወሰዱትና ጫና ፈጥረው በርከት ያሉ የግብ ዕድሎች የፈጠሩት ሲዳማ ቡናዎች ሱራፌል ዳኛቸው ከርቀት አክርሮ ሞክሮት ሶፎንያስ ሰይፈ ካዳነው ሙከራ በኋላ በ25ኛው ደቂቃ ላይ ጨዋታውን መምራት ጀምረዋል። አቤል ያለው ከፍቅረየሱስ ተ/ብርሀን ጋር አንድ ሁለት ተቀባብሎ በጥሩ አጨራረስ ወደ ግብነት የቀየራት ኳስም ቡድኑን መሪ ያደረገች ግብ ነች።

ከግቡ በኋላም ጫና መፍጠራቸውን የቀጠሉት ሲዳማ ቡናዎች እንደ ነበራችው ብልጫ በርከት ያሉ ግልፅ የግብ ማግባት አጋጣሚዎች ባይፈጥሩም አቤል ያለው አሻግሯት ብርሃኑ በቀለ በደረቱ አብርዶ በሞከራት እና ፍቅረየሱስ ተ/ብርሀን ከርቀት አክርሮ ባደረጋት ሙከራ ተጨማሪ ግብ ለማስቆጠር ጥረት አድርገዋል።
ከመጀመሪያው አጋማሽ የተለየ መልክ የነበረው ሁለተኛው የጨዋታ ምዕራፍ የተጫዋቾች ቅያሪ አድርገው የተመለሱት መቐለ 70 እንደርታዎች ተሻሽለው የቀረቡበት ነበር።

ሲዳማ ቡናዎች በአጋማሹ ጅማሮ ላይ ጫና ፈጥረው በርከት ያሉ ወደ ሙከራነት ያልተቀየሩ አጋጣሚዎች የፈጠሩ ሲሆን ያሬድ ባየህ ከመአዝን ተሻግራ ተከላካዮች የመለሷትን ኳስ ተጠቅሞ መቷት ሶፎንያስ ሰይፈ እንደምንም ባዳናት ሙከራ መሪነታቸውን ለማጠናከርም ተቃርበው ነበር። በሁለተኛው አጋማሽ የተሻለ እንቅስቃሴ ያደረጉት መቐለ 70 እንደርታዎችም በ75ኛው ደቂቃ ላይ አሰጋኸኝ ጴጥሮስ ከቆመ ኳስ አሻምቷት ተከላካዮች ከጨረፏት በኋላ ብርሀኑ አዳሙ መቷት መስፍን ሙዜ ጨርፏት የግቡን ቋሚ በመለሳት ኳስ የአቻነት ግብ ለማስቆጠር ተቃርበው ነበር። ከዚህ በተጨማሪ ብርሀኑ አዳሙ ከሳጥኑ ጠርዝ ሞክሯት መስፍን ሙዜ ያዳናት ሙከራም ለግብ የቀረበች ነበረች። በመጀመሪያው አጋማሽ ሲዳማ ቡናዎች በሁለተኛው አጋማሽ ደግሞ መቐለ 70 እንደርታዎች የተሻለ በተንቀሳቀሱበት ጨዋታዎች ሲዳማ ቡናዎች በአቤል ያለው ብቸኛ ግብ ባለ ድል ሆነዋል።

