በ25ኛ ሳምንት የመጨረሻ ቀን የሚደረጉ ሁለት ጨዋታዎችን የተመለከቱ መረጃዎች እንደሚከተለው አዘጋጅተናል

አዳማ ከተማ ከ ነጌሌ አርሲ
ካለፉት 8 ጨዋታዎች አንዱን ብቻ በማሸነፋቸው አሰልጣኝ ሥዩም ከበደን ከኃላፊነት ያነሱት አዳማ ከተማዎች በተለይም ከመጨረሻ 4 ጨዋታዎች በሦስቱ ቀድመው ግብ አስቆጥረው ጨዋታውም መምራት ቢችሉም የኋላ ኋላ በሚቆጠርባቸው ግብ ሁለቱን ሲሸነፉ በሁለቱ አቻ ተለያይተዋል። ከሊጉ መሪ ሲዳማ ቡና በ15 ነጥቦች የራቀው ቡድኑ የራቀውን የመከላከል አደረጃጀት ጥንካሬ መልሶ በማግኘት እና ነጥቦችን በመሰበሰብ ወደ መሪዎቹ ካልተጠጋ በደረጃው ወገብ ላይ ባለው ጠንካራ ፉክክርም ቦታውን ሊያጣ ይችላል። ረዳት አሰልጣኞች የነበሩት ዳዊት ሐብታሙ እና ዳዊት ታደለ በኃላፊነት በሚመሩት የመጀመሪያ ጨዋታ የሚቀርቡበት የጨዋታ መንገድም የሚጠበቅ ነው።
ቀስ በቀስ ያልተጠበቁ ውጤቶችን በማስመዝገብ በዋንጫ ፉክክሩ ለመቆየት ፈተና የገጠማቸው ነጌሌ አርሲዎች ከመጨረሻ 5 ጨዋታዎች ምንም ጨዋታ ማሸነፍ አልቻሉም። ይባስ ብሎም በመጨረሻ 4 ጨዋታዎች አንድም ግብ አለማስቆጠራቸው ትልቁ ድክመታቸው ነው። ሲዳማ ትናንት በማሸነፉ ልዩነትን ወደ 10 ነጥቦች ማስፋት የቻለ ሲሆን ሰጎኖቹ ወደ ድል ተመልሰው ፍልሚያውን ካላስቀጠሉ በዋንጫ ፉክክሩ የመቆየታቸው ነገር አጠራጣሪ ይሆናል። አሰልጣኝ ቱሉ ደስታ ይታወቁበት የነበረው የፈጣን ሽግግር አጨዋወት በመጠኑ እየተቀዛቀዘ መምጣቱ እና የነ ከቤ ብዙነህ ውጤት ቀያሪ እንቅስቃሴዎች እየቀነሱ መምጣት ፈጣን መሻሻሎችን ይሻሉ።
ነጌሌ አርሲዎች በ24ኛው ሳምንት በቀይ ካርድ ከሜዳ የወጣውን ተከላካዩ ዴሲሬ ፓስካል በቅጣት ምክንያት በዛሬው ጨዋታ አያሰልፉም። በአዳማ ከተማ በኩል የቡድን ዜናዎችን ለማግኘት ያደረግነው ተደጋጋሚ ጥረት አልተሳካም።
በመጀመሪያ ዙር ግንኙነታቸው ነጌሌ አርሲ በመጨረሻ ደቂቃ ግቦች 2ለ1 ማሸነፉ ይታወሳል።
ሀዋሳ ከተማ ከ ወልዋሎ ዓ/ዩ
ሊጉ ከመቋረጡ በፊት በንግድ ባንክ 4ለ2 የተሸነፉት ሀዋሳዎች ከመጨረሻ 5 ጨዋታዎች በአንዱ ብቻ ማሸነፋቸው ያልተጠበቀ ነበር። ከመሪው ሲዳማ ጋ ያላቸው ልዩነት ወደ ስምንት ከፍ ያለባቸው ሐይቆቹ በዋንጫ ፉክክሩ ለመቆየት ይህንን ጨዋታ ማሸነፍ ብቸኛ አማራጫቸው ነው። የዛሬው ተጋጣሚያቸው ከወራጅ ቀጠናው ለመውጣት ጠንካራ ተጋድሎ እያደረገ ያለው ወልዋሎ እንደመሆኑ ደግሞ የዕለቱ ጨዋታ ለተመልካች ሳቢ የሆነ ፉክክር እንደሚያስመለክተን ይጠበቃል።
ከመጨረሻ 4 ጨዋታዎች በሦስቱ ድል የተቀዳጁት ወልዋሎዎች በተለይም በመጨረሻ 3 ጨዋታዎች ምንም ግብ አለማስተናገዳቸው ጠንካራ ጎናቸው ነው። በዛሬው ጨዋታ አንድ ነጥብ ማግኘት ከወራጅ ቀጠናው የሚያወጣቸው እና ሦስት ነጥብ ማግኘት ወደ ደረጃው ወገብ የሚያደርሳቸው ወልዋሎዎች በቀጣይ ተከታታይ ሳምንታት በወራጅ ቀጠናው ከሚገኙ ቡድኖች ጋ የሚገናኙ ሲሆን በተሻለ የራስ መተማመን ለመቅረብ በዛሬው ጨዋታ ጠንካራ ፉክክር ያደርጋሉ ተብሎ ይጠበቃል።
በሀዋሳ ከተማ በኩል ሁሉም የቡድኑ አባላት ለጨዋታው ዝግጁ ሲሆኑ ወልዋሎዎች በዛሬው ጨዋታ ሱልጣን በርኸ እና ናሆም ኃ/ማርያም በጉዳት ስምዖን ማሩ እና ሙታክብዋ ጆኤል ደግሞ በቅጣትም ምክንያት አያሰልፉም።
ሁለቱ ቡድኖች ሰባት ጊዜ ተገናኝተው ሀዋሳ ሦስት ወልዋሎ ደግሞ ሁለት ጊዜ ሲያሸፉ በሁለት ጨዋታዎች አቻ ተለያይተዋል። በጨዋታዎቹ 9 ጎሎች ሲቆጠሩ ወልዋሎ 3፤ ሀዋሳ 6 አስቆጥረዋል። (የተሰረዘው የ2012 ጨዋታ አልተካተተም)

